"ደብተራ ማን ነው?" ጸረ ደብተራ ንቅናቄ በሊቀ ጠበብት በዶክተር ዘሪሁን ሙላቱ
"ደብተራ ማን ነው?" በዶክተር ዘሪሁን ሙላቱ
#ደብተራ ማን ነው??
ክፍል አንድ
“#ደብተራ” ማለት ቃሉ ሁለት ዓይነት ምንጭ አለው ፤ አንዱ ከግእዝ ሲሆን፤ ሁለተኛው ከግሪክኛ ነው ፤ በግሪክኛው ምንጫችን “ደብተራ” ማለት “ጸሐፊ" ማለት ነው ፤ በግእዙ ቋንቋ “ደብተራ” ማለት “ድንኳን” ማለት ሲሆን በውስጡ ያሉ አገልጋዮች ካህናተ ደብተራ ይባላሉ ፡፡ ካህናተ ደብተራ የሚለውን ስያሜ በከፊል ስም ደብተራ ብሎ ጠርቶ ካህናተ ደብተራን ለመጥራት ነው ደብተራ የሚለው አገላለጽ የመጣው የሚሉ አሉ ፤ በዚህ ምክንያት ማኅሌታይ ሲጠራ ደብተራ ተብሎ መጠራት እንደተጀመረ ይነገራል ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጻፈው በደብተራ ኦሪት (በድንኳን) ውስጥ ያለው የመዘምራን የዜማ አገልግሎት የደብተራ ታሪካዊ መነሻው እንደሆነ የሚጽፉ አሉ ፡፡
#ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ማኅሌታውያኑን ሲጠቅስ "ደብተራ" ብሎ አይጠራቸውም ፤ መዘምር ወይም መዘምራን እያለ ይጠራቸዋል ፡፡ በመጽሐፈ ነገሥት እንደተጻፈው በንጉሥ ዳዊት ፊት በድንኳን ውስጥ የሚያገለግሉ መዘምራን ናቸው ፡፡ ንጉሥ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን አሰርቶ ከጨረሰ በኋላ ከድንኳን ወደ ቤተ መቅደስ አገልግሎቱ ሲሸጋገር የድንኳኑ የደብተራ አገልግሎት በንጉሡ ፊት ቀጥሏል ፡፡ ሥርዐቱም በቤተ እስራኤልም በቤተ ክርስቲያንም ዛሬ ድረስ አለ ፡፡
#ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ (አቡነ መልከጼዴቅ) የቤተ ክርስቲያን ማኅሌታውያን የሆኑ መዘምራን ላይ #ደብተራ የሚለው መጠርያ ከጊዜ በኋላ የመጣ መሆኑን ጽፈዋል ፡፡ በዚህ መሠረት ይመስላል ማኅሌታውያን አገልጋዮች ደብተራ ተብለው እንደሚታወቁ ደስታ ተክለ ወልድና ፕ/ር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ በመዛግብተ ቃላቸው ስለ ደብተራ ሲተነትኑ ማኅሌታይ ሲሆን ሕዝባዊ ዕውቀት ያለው የዜማ ሰው መሆኑን በደብተራ ፍች አስቀምጠዋል ፡፡
#በቤተ እስራኤልም ይሁን በቤተ ክርስቲያን ማኅሌታዊ ሥርዐት ውስጥ በተወሰኑ አከባቢዎች ደብተራ በካህንና በዲያቆን እንዲሁም በማኅሌታውያኑ መካከል ያለ ክህነቱን ያፈረሰ አገልጋይ እንደሆነ በትውፊት ቢታወቅም እንኳን አሁን ግን አወዳሽ ወይም መዘምር ይባላል እንጂ “ደብተራ” እንደማይባል በአጽንኦት የሚናገሩ ምሁራን አሉ፡፡ ይህንን የሚሉበት ምክንያት አብዛኛውን በደብተራ ስም ያለ ሰው በጥንቆላ ስራ ተሰማርቶ ስለሚኖር ነው ይላሉ ፡፡ በዚህ ምክንያት ደብተራነት የጠንቋይነት መጠርያ እየሆነ መጥቷል ፡፡ ይኸው ደብተራ ነው-በኢመደበኛ መንገድ ጥንቆላና ሟርት እያጠና ከቤተ ክርስቲያን ውጭ በጥንቆላ ስራ የሚሰማራው ፡፡ በዚህ መንገድ ላይ የተሰማራ ደብተራም ክህነት ሊኖረውም ላይኖረውም ይችላል ፡፡ ቢኖረው እንኳን አብዛኛውን ደብተራ ከዲቁና በላይ ሥልጣነ ክህነት አይኖረውም ፤ በቤተ ክህነትም ከቤተ ክህነትም ውጭ ሊያገለግል ግን ይችላል ሲሉ በደብተራ ማንነት ላይ የተሰሩ ጥናታዊ ጽሑፉች ያብራራሉ።
#በርግጥ አንዳንድ ሰዎች የደብተራን ማንነት ግብሩን አይተው ነቅፈው ጽፈዋል ፤፤ የተወሰኑ የቤተ ክርስቲያን ልሂቃን ደግሞ በአንጻሩ ደብተራን በተመለከተ ስለ ዕቅበተ ደብተራ ጽፈዋል ፤ የደብተራ አስፈላጊነትን አጉልተዋል፡፤ የደብተራን በጎነት ካጎሉት መካከል የበአማን ነጸረ ጽሑፍ ተጠቃሽ ነው ፡፡ በአማን ነጸረ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ስለ ደብተራ ተቆርቁሮ የጻፈውን የዕቅበተ ደብተራ ጽሑፉን አነብቤ ተማርኬበታለሁ፡፡
#የበአማን የአጻጻፍ ስልቱ ይመስጣል ፤፤ የደብተራ ፍቺን ሲያስቀምጥ ግን ማኅሌታዩን ከጥፈት አዋቂው ደብተራ ጋር አዛንቆ ማተቱ ደብተራ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ አላስቀመጠም ። ወይም በአማን ነጸረ ስለደብተራ በጎነት መጻፍ አላማው ስለሆነ ደብተራ መባልን ከአዕምሮ ምጥቀት ጋር ብቻ እንጂ ደብተራን (ደብተራ) ከጥንቆላና ከተረት ጋር የተገናኘበትን ሂደት አንባቢ እንዲረዳው አላደረገም ፡፡ ሆኖም በእኔ እይታ የበአማን ነጸረ የመረጃ አጠቃቀሱ፤ የመጻሕፍት አጠቃቀሙ የደብተራን ጽሑፍ ለመመርመር የሚያስፈልጉ ሳይንሶችን እየተጠቀመ መሆኑን ስለተረዳሁ አደንቄዋለሁ ፡፡ የደብተራን ክፍተት ሳይሆን የደብተራን ምልዐት ብቻ እየጠቀሰ የደብተራን በጎ አስተዋጽኦ ሰው መገንዘብ እንዲችል ስለደብተራ አስፈላጊነት ክርክር ያለው ጹሑፍ አበርክቷል ፡፡
#ሌላው ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” በሚል በጻፉት መጽሐፍ ላይ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ትችት ሲያቀርብባቸው “የደብተራ ተንኮል” ሲሉ ዲያቆኑን ሊያነውሩት ሞክረዋል ፡፡ የደብተራ ተንኮል ማለት ደብተራ ጸያፍ ማለት ከሆነ ፕሩሮፌሰሩ ማለት የፈለጉት የሚመሰገን ገጽ እያለኝ እንዴት ለትችት ብቻ ተነሣብኝ ለማለት ፈልገው ይመስላል ፡፡ የደብተራ ተንኮል ማለት የደብተራ ጸያፍ ማለት ሊሆን ይችላል ፡፡ የቃሉ አጠቃቀም ስሕተት ብቻ ፈላጊነትን (Fault Finder) ያሳያል ፤
በአብነቱ የቅኔ ትምህርት የሚታለፍ ስሕተት ነገር ግን ስሕተቱ እንደ ስሕተት የማይቆጠር ከሆነ "ደብተራ ጸያፍ" ይባላል፡፡
#ዲ/ን ዳንኤል ክብረትም ለፕ/ር መስፍን ምላሽ ለመስጠት በሚመስል መልኩ ስለደብተራነት “ኑ ሀገሬን እናዋልዳት” በሚለው መጽሐፉ በጻፈው ሐተታ ገድለ ፊሊጶስን ምስክር አድርጎ ታሪካዊ ዳራውን ከካህናተ ደብተራ ይጀምርና
ደብተራ ማለት አሁን ባለንበት ዘመን "ጸያፍ የትርጉም ለውጥ" እንዳመጣ ለማሳየት "ሐኪም" የሚለውን ቃል ቀድሞ "ጠቢብ" የሚል ፍች እንደነበረው አሁን ግን ባህላዊ መድኃኒት አዋቂ መባሉን በማነጻጸርያነት አቅርቧል ፣ ልክ እንደዚሁ "ደብተራ" የሚለው ስያሜ በአሁኑ ጊዜ ጸያፍ የትርጉም ለውጥ (Semantic Change) አጋጥሞታል ሲል ጽፎልናል ፡፡
#በአንጻሩ ግን ደብተራ ማለት ዳንኤል እንደሚለው በጊዜ ሂደት ጸያፍ የትርጉም ለውጥ የመጣበት ስያሜ ሳይሆን በመነሻው የጠንቋዮች መጠርያ መሆኑንም ሊያመለክት እንደሚችል ጥንታዊ የግእዝ መዛግብት ያስረዳሉ ፡፡ እንደእነ ተዋነይ ያሉ ደብተሮች በዚህ ዘርፍ ሊጠቀሱ ይችላሉ ፡፡ #በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የተጻፈው የአለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራ "የኢትዮጵያ ታሪክ" (በሚል በሥርግው ገላው የተሰናዳው መጽሐፍ) ላይም ተዋነይ የሚባል የጎንጅ ደብተራ አጼ በካፋን ክፉ ምክር እየመከረ ሲያስተው እንደነበር ተጽፏል ፡፡ ቃል በቃል እንዲህ ይላል፣ “ዐፄ በካፋ በዘመኑ ከክፉ ሥራ በቀር አንድ ቀን በጎነት ሥራ አልሠራም። ያን ግዜ ተዋነይ የሚባል የጎንጅ ደብተራ ጠንቋይ ነበረው። ሙያው ከርሱ ጋራ ነበረ። በካፋም ዘጠኝ ዓመት ነግሦ [በ1723] በክፉ ሞት ሞተ።" ይለናል ፡፡ ለማሳያነት የዚህ በተዋነይ ድብትርና፤ ጥንቆላና ክፉ ምክር የሚያሳየው አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ነን የሚሉ ግለሰቦች በራሳቸው ተነሣሽነት ክፋትና ጥንቆላ ተምረው ሕዝበ ክርስቲያንን ማጭበርበራቸውንና ነጋሥያንን ሳይቀር በክፉ ምክራቸው ማሳታቸውን ነው ፡፡
#በርግጥ ቤተ ክርስቲያን ወንበር ዘርግታ በወንበር ጥንቆላን አታስተምርም፤ ነገር ግን በዛሬ ዘመንም ቢሆን እንደ ተዋነይ ያሉ አንዳንድ ግለሰቦች የእርስ በእርስ የአስማት ልውውጥ በማድረግ ኢመደበኛ በሆነ መንገድ አስማት የሚለውን ቀል በመተው ጥበብ በሚል የውስጠ ዘ ስም ጥንቆላን ይለማመዳሉ፤ ይማራሉ ፤፤
ከዚህም የተነሣ እገሌ መስተፋቅር አለው/ያውቃል ፤ እገሌ መስተባርር(የሚያሰድድ) አለው ፤ እገሌ መስተአብድ(የሚያሳብድ) አለው ፤ እገሌ መስተጻልእ(የሚያጣላ) አለው እየተባለ የሚነገርላቸው ዛሬም የሚፈሩና የሚያስፈራሩ ደብተሮች እንዳሉ እሙን ነው ፡፡ በዚህ አንጻር የደብተራ ፍቺ ሲደመደም ፤ ደብተራ በአንድ በኩል አገልጋይ ነኝ ይበል(ይምሰል እንጅ) እንጂ በሌላ በኩል ጀጀጀ፤ ቀቀቀ፤ ጠጠጠጠ እያለ ሕዝብን በጥንቆላ የሚያስት አጭበርባሪ ፤ ንጉሥን የሚያስት ሐሰተኛ መካሪ ማለት ነው ፡፡
ክፍል ሁለት
ይቀጥላል !!!
#ገለቶማ !!!
#የደብተራ_ሥራ
#ክፍል ሁለት
#በክፍል አንድ ጽሑፍ፤ ደብተራ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የግእዝ ቋንቋን ምስክር አድርገን አይተናል ፡፡ አሁን ደግሞ ደብተራ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከግእዝ ምንጫችን ባሻገር የደብተራ ሥራንና ደብተራ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በዚህኛው ክፍል እናያለን ፡፡ ዋነኛውና መሠረታዊ የግሪክኛው ምንጫችንን ስንፈትሽ ደብተራ ማለት ጸሐፊ ወይም ከታቢ " ማለት ነው ፤ ይህኛው ፍቺ በክፍል አንድ ሐተታ ከሰጠንበት ደብተራ ለሚለው ቃል ከተሰጠው ፍቺ ይለያል ፡፡ በግሪክኛ ደብተራ ማለት ጸሐፊ ማለት ነው ስንል ደብተር የሚለው ቃልም ከዚህ የተገኘ ነው። ደብተር ማለት "መመዝገቢያ፣ መጻፊያ" እንደማለት ነው ። ይህኛው ደብተራ ግእዝ አዋቂውና ጸሐፊው ደብተራ ሊባል ይችላል፡፡ አይጽፍ ደብተራ ክንፍ የሌለው አሞራ እያለ ደጋሚውን ደብተራ የሚተቸው ጸሐፊው ደብተራ ይህኛው ነው ፡፡
#ክታብ የሚያዘጋጀውና የሚጽፈው ይህ ደብተራ ከሕጸንነቱ ጀምሮ የቁም ጽሕፈት ይማራል ፡፡ ይህ ደብተራ ጠልሳሚ ወይም ክታብ አዘጋጅ ይባላል ፤ ፈረንጆች ከታቢ ደብተሮችን በሁለት ከፍለው ያዩአቸዋል ፤ ክታብ የሚያዘጋጀውን ጠልሳሚ ሲሉት ከመጽሐፍ ወደ ሌላ መጽሐፍ የሚጽፈውን ግእዝ አዋቂውን ሰው ደብተራ ይሉታል ፡፡ አሁን ክታብ አዘጋጅና ጠልሳሚው ደብተራ ላይ እናተኩር !!
#በየሰፈሩ ያሉ ሕጻናትን አንገት ላይ የሚታሰር ክታብ የሚያድሉት እነዚህ አስማተኛ ደብተሮች ክታብ ጠልሳሚዎች ናቸው ፡፡ እነዚህ ደብተሮች ልዩ ልዩ ሥነ ሰይጣንና (Demonology) ተምረው መናፍስትን ለመሳብ መልክዐ ሳጥናኤልን የሚደግሙና የሰይጣንን መንፈስ በየጅረቱ የሚዛመዱ /የሚዋረሱም/ ናቸው ፡፡
#እንደዚህ ዓይነቶቹ ደብተሮች በየመንደሩ እየዞሩ ዐውደ ነገሥታቸውን ሸክፈው ወይም በቃላቸው አጥንተው መኑ ስምኪ እያሉ ኮከብ የሚቆጥሩ ፤ ባልና ሚስት የሚያገናኙ፤ የሚያፋቱና በክርስትና አስተምህሮ የማይፈቀደውን ሁሉ የሚሠሩ ሕግ አፍራሾችም ናቸው ፡፡
#እንደዚህ ዓይነት ጠልሳሚ ደብተሮች በየዘመኑ አሉ ፡፡ ለምሳሌ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ክታብ አዘጋጆች አስማተኛ ደብተሮች “መጽሐፈ አስማት” የሚባል ሁለት ሰው ቢሸከመው ሊያነሳው የማይችል መጽሐፍ ነበራቸው ፤ አጼ ይስሐቅን አታለው ረሃብና ቸነፈር ሲሆን ጥጋብ እንዲሆን ሕዝብ እየሰማው መደገም አለበት ብለው ከቤተ መንግሥት አጼ ይስሐቅ ቀለብ ሰፍሮላቸው ነበር ፤፤ አጼ ይስሐቅን ቢያሳሱትትም ከርሱ ቀጥሎ የነገሠውን አጼ ዘርዐ ያዕቆብን ማሳሳት ግን አልተቻላቸውም ፤፤
#በዚህ በእነሱ “መጽሐፈ አስማት” ምክንያት የቤተክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍት ዝርዝር በፍትሐ ነገሥት ምንጭነት 81 እንዲሆኑ አጼ ዘርዐ ያዕቆብ በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በኩል እንዲወሰን አደርጓል ፤፤ የቅዱሳት መጻሕፍት ዝርዝር ከታወቀና ከተወሰነ በኋላ ደብተሮች የሚያታልሉበት ትልቁ የ”አስማት መጽሐፍ”ና ልዩ ልዩ ምዕመናንን ማደናገርያ የነበረ “የጥንቆላ ጠልሰሞችና ክታቦች” በአደባባይ ተቃጥለዋል ፡፡
#በርግጥም አጼ ዘርዐ ያዕቆብ ይህን ማድረጉ ከፍትሕ መንፈሳዊ ፤ ከሃይማኖተ አበው ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ አግኝቶ ክርስትናውን ለማጽናትና ቤተ ክርስቲያንን ከትችት ለመጠበቅ መሆኑንም ለሕዝቡና ለክርስቲያኖቹ ተናግሯል ፡፡
ይሁንና ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስተቹ ደብተሮች ባለመጥፋታቸው አንዳንድ ደብተሮች አሁንም ቢሆን በድብቅ የሚጠቀሙባቸው የድጋምና የአስማቶ ክታቦች (underground Litrature) መኖራቸው የአደባባይ ሐቅ ነው ፡፡
#እንደዚህ ዓይነቶችን ሰዎች ከእንደዚህ ዓይነት አስማታዊ ግብራቸው እንዲመለሱ መምከር ፤ ማስተማርና መገሠጽ እንጅ የሌለ ምናባዊ ሊቅነት እየሰጡና በውዳሴ ከንቱ እየጠለፉ ነፍሳትን ወደ ሲዖል ማጋዝ ማንንም አይጠቅምም ፡፡ የውጭ ሀገር ተመራማሪዎች እንኳን ክታብ አዘጋጆችንና መናፍስት እንስባለን የሚሉ ሐሰተኞችን ስለሚተቿቸው “ደብተራ” ብለው እንኳን አይጠሯቸውም ፡፡
#ከላይ እንደተጠቀሰው ፈረንጆች ደብተራ የሚሉት የግእዝ ዕውቀት ያለውና የግእዝ ሥነ ጽሑፍ የሚመረምረውን ሰው ብቻ መሆኑን ዶ/ር ኃይሉ ሀብቱ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር መጽሔት በጻፉበት ጥናታዊ ጽሑፍ ገልጸዋል ፡፡ ፈረንጆች በተጨማሪም ግእዝ አዋቂዎችን “ደብተራ” ሲሏቸው ግእዝ የማያውቁትን የዜማ ምሁራንን ደግሞ “አለቃ” እያሉ እንደሚጠሯቸውም በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ለፈረንጆቹ ደብተራ ማለት የግእዝ መዛግብትን የሚያሰናዳና የሚጽፍ ማለት ነው ፡፡ ለዚህም ማሳያነት “ደብተራ” አሰጋኸኝ፤ ደብተራ ዘነብ የመሳሰሉትን ይጠቀሳሉ ፤
#ደብተራ ማለት ከክታብ አዘጋጅነትና ጠልሳሚነት ለይተን ጸሐፊ ማለት ነው ስንል የራሱ ችግር የለበትም ማለት ግን አይደለም ፡፡ ጸሐፊ ደብተራ የሚያስመሰግነው የጥንት የብራና መጻሕፍትን በመገልበጡና በማባዛቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያስተላልፍ መጽሐፍ ገልባጭ በመሆኑ ነው ፡፡ በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ደብተሮች እየተደራጁ ከዚህ ከሚያስመሰግናቸው መጻሕፍትን የማባዛት ሥራ እየወጡ በየዘመኑ ለሚነሡ ነገሥታት ፍላጎትና ርዕዮተ ዓለም ማደር መጀመራቸው ይታወቃል ፡ የነገሥታትን የገዢነት አስተሳሰብ መሠረት በማድረግ የጠሉትን ሕዝብ የሚያሳንሱበት ፤ የወደዱትን ሕዝብ ነጋሥያን የሚያደርጉበት የሥነ ጽሑፍ ዘዴ ነበራቸው፡፡
#ሆኖም የጥንታዊ የግእዝ ሥነ ጽሑፍ ለማዘጋጀት በየዘመኑ ለነገሥታት ያደሩ ደብተሮች ከሁሉም ኅብረተ ሰብእ የሚመነጩ በመሆናቸው በታሪክ ላይ መጠነኛ ሊባል በሚችል መልኩ ጉዳት ሊያስከትል ችሏል፤ የደብተራ አመጣጥ ከአንድ ብሔር ወገን ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ በሃይማኖት መጻሕፍት ላይ ተጽእኖ ማሳደር እንደተቻለው በዜና መዋዕል መጻሕፍት ላይም ከፍተኛ ተጽእኖ ባሳደረ ነበረ ፡፡ ዜና መዋዕልን በመጻፍ ረገድ ደብተሮች ከየትኛውም ብሔር ተሰባስበዋል ፡፡
#የኢትዮጵያን ታሪክ በመጻፍ ረገድ ደብተራን ከአንድ ብሔር በተለይም ከአማራ ጋር ብቻ የሚያያይዘው መለስ ዜናዊ ብቻ ነው ፡፡ ይህ ደግሞ ፈጽሞ ስሕተት ነው ፡፡ በተለይም የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ ባለቤትና ግሥ እየቀየሩ ለነገሥታት እየሰጡ ዜና መዋዕል መጻፍ የተጀመረው ለነገሥታት ባደሩ ደብተሮች ዘመን ነው ፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን ይህ መጽሐፍ ገልባጭና ተመስጋኙ ጸሐፊ-ደብተራም ለነገሥታት ርእዮት ከማደሩም በላይ ሁሉን ዐዋቂ ነኝ በሚል ምናብ በኩሸት አጻጻፍ (በምናባዊ ግነት) ታሪክን ተረት እያደረገ የሚጽፍ ወገኛ ሆነ ፡፡ በዚህም ምክንያት ደብተራነት እንደጸሐፊነት መጠራቱ ቀርቶ በአሉታዊ አገላለጽ እንደ ተረት ዐዋቂ መጠራት ጀመረ፡፡ የደብተራን አነጋገር አንባቢ በየመጻሕፍቱ ሲያገኘው ይሄ እንኳን ቃለ ደብተራ ነው ማለት ጀመረ ፤ ሐሰትና ግነት ነው ለማለት መሆኑ ነው ፡፡፡፡
ይቀጥላል !!!
#ገለቶማ !!!
#ደብተራ እንደ ኮረና !!! (δίφθερα- diphtheria)
#ኮረና_መሰል በሽታ ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተከስቶ እንደነበር ያውቃሉ??? ስያሜውም “ደብተራ” ይባል እንደነበር ሰምተዋል ??? እንግዲያውስ ቢሰሙም፤ ባይሰሙም፤ ቢያውቁም፤ ባያውቁም፤ ይህቺን አጭር ጽሑፍ ያንብቡ !!! ስለደብተራ የጀመርኩትን ተከታታይ ጽሑፍ መቀጠሌ ነው።....+++
#ክፍል ሦስት
#የሚገርመው !!! “ደብተራ” የሚለው ቃልን በማሞካሸት በኢትዮጵያ ቆዳ ፋቂዎችና ክታብ አዘጋጆች እንዲሁም “ተረት ተረት” አዋቂዎች ደብተራነትን ለማለምለም ቢታትሩም የሚሳካ አይደለም ፤ ይልቁንም በሌላው ዓለም “ደብተራ” የሚለው ቃል ግብሩም ፤ ስም አጠራሩም ከመጥፋቱ ባሻገር ወደ በሽታ ስምነትም ተቀይሯል ፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋም ሳይቀር በሕክምና ሳይንስ የበሽታ ስያሜ መዘርዝር ውስጥ “ደብተራ” (Diphtheria) የበሽታ ስም ተደርጓል ፡፡
#በሀገራችን የሰው ስም አርጅቶ የበሽታ ስም ለመሆን የዳዳው “አልማዝ” የሚለው ስም ነው፤ እርሱም ቢሆን ባለጭራ የሚል ቅጽል ተጨምሮበት ነው ፡፡ "ደብተራ" የሚለው መጠርያ ግን ጥንት በግሪክ ሀገርና ቋንቋ የበሽታ መጠርያ ሲሆን ባለበት በቁሙ ነው ፡፡ “#ከጥንት ጀምሮ የመተንፈስ ሥርዐትን የሚያስተጓጉል ወይም መተንፈስን የሚከለክልና ጉሮሮን የሚቆስል ብሎም የሚያንቅና የማያስውጥ በሽታ ሲጠራ “ደብተራ” ተብሏል ፡፡ በምንጩ በግሪክ ቋንቋ “ደብተራ”(δίφθερα- diphtheria) ማለት በመጨባበጥ ፤ በማስነጠስና በማሳል የሚተላለፍው የዛሬው “ኮረና” ዓይነት መጠርያ ሆኖ በሺዎች ክፍልፋይ የሚሆኑ ዘመናትን አስቆጥሯል ፤
#በሌላ አገላለጽ ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለክታብ ሥራ፣ ቆዳ ሲፋቅና ድንኳን ለመሥራት ቆዳን ከመወጠር ጋር በተያያዘ ከሚመጣው ሽታና ከሚፈጠረው ባክቴርያ ( ተዋኅስያን) ጋር ተገናኝቶ በግሪክ ሀገር ኮረና መሰል በሽታ ተከስቶ ስለነበር “ደብተራ” የሚል ስያሜን አግኝቷል ፤ ይህንን በሽታና ስያሜውን በማግኘት ረገድ ማብራርያ የሰጠበት በዘመኑ የነበረው ሂፖቅሪጠስ (Hippocrates) የተባለው የግሪክ ፈላስፋ ነው ፡፡ ይኸውም በሽታውና የደብተራነት ስያሜው ከ2,500 ዓመታት በፊት ኤፒዴሚክስ በሚባለው የሂፖቅሪጠስ የሥነ ጽሑፍ ሥራው ( Epidemics III) ውስጥ ተገልጿል ፡፡ ከዚያም ከዓመተ ምሕረት በኋላ ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወዲህ በተለያየ ስም በዓለም ታውቋል ፤ ተስቦ ፤ ስፓኒሽ ፍሉ ፤ ወረርሽኝ፤ የቆዳ በሽታ ፤ቴታነስ እና በሌሎችም ስያሜም ተጠርቷል ፡፡ የበሽታው መደበኛና መነሻ ስሙ ግን “ደብተራ” ነው ፡፡
“#ደብተራ” (δίφθερα- diphtheria) ማለት በምንጩ በግሪክ ቋንቋ መተንፈስ የሚከለክልና ጉሮሮን የሚቆልፍ ወይም በተለምዶ መንጋጋ ቆልፍ የሚባለው ዓይነት በሽታ ሲሆን ከኮረና ጋር አንድ ለማድረግ “ደብተራ” መደበኛው የኮረናው ስም ሲሆን “ኮረና” የሚለው ስያሜ አሁን የመጣ የፖለቲካ ስሙ ነው የሚሉ ምሁራን አሉ ፡፡ ለማንኛውም የሚከተለው የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላታዊ ፍቺን እንግሊዝኛው ሲያብራራው “What is the root of the word Diphtheria in Greek ? In Greek, the word Diphtheria means "leather," a reference to the leathery coating the disease can cause in the throat. እያለ ሐተታውን ይቀጥላል ፤ እንግሊዝኛውን የምትችሉና ሙሉ ማብራርያውን ማወቅ የፈለጋችሁ የሚከተለውን መጠቁም ተጭናችሁ አንብቡት ፡፡( https://www.vocabulary.com/dictionary/diphtheria)
#የበሽታው ዓይነት ምንም ይሁን ምን ደብተራ የሚለው ቃል የበሽታ ስም መጠርያ የሆነበት ታሪካዊና ሥነ ልሳናዊ ሐተታው ግልጽ ነው ። ይኸውም ደብተራ ማለት በግሪክም ሆነ በሌሎች ቋንቋ የቃሉ ምንጭ ቆዳ ፋቂና ብራና ወጣሪ ከማለት የመጣ እና በኋላ ዘመን ከቆዳ መፋቅ ጋር በተያያዘ የበሽታ ስያሜን ያገኘ መሆኑን ብቻ ያረጋግጣል ፤ ይህም ድሮ ድሮ ደብተራ ማለት ምሁር ወይም ሊቅ የሚል ፍቺ ነበረው ለሚለው ትርክት ማስረጃ አለመኖሩን ያሳያል ፤
#ይህ ማለት ደብተራነትን ከምሁርነት ጋር ተጃምሎ ሲነገር አልሰማንም ማለት ግን አይደለም ፤ የሰማነውም ቢሆን ምንጭ አልባ ስለሆነ በራሱ የደብተራ ፊቺ ይባላል እንጂ ተቀባይነት አይኖረውም ፤ በርግጥ በሐዲስ ኪዳን እንደተገለጹት እንደ ደቂቀ አስቄዋ ጥንቆላውም፤ ክታቡም ፤ መንፈሳዊነቱም አይቅርብን የሚሉ በካህናት ስም የሚያታልሉና ክታብ የሚጽፉ ደብተሮች የሉም ማለቴም ግን አይደለም ፤ እነርሱም ቢሆን እግዚአብሔር እስኪቀስፋቸው ድረስ ቢቆዩ እንጂ ዕድሜ የላቸውም ፡፡
#በተለይ አሁን ባለንበት ዘመን የማተምያ ማሽን እያለ ከጽሑፍ ጋር በተያያዘ ቆዳ የሚፍቅና የሚወጥር ፤ ለጽሑፍ የሚሆን ብራናን የሚያለሰልስ ካለ ለክታባዊው ጥንቆላው ካልሆነ በስተቀር ሌላ ዓላማ የለውም ፡ ስለዚህ ደብተራ ብሎ ጠንቋይ እንጅ የእግዚአብሔር አገልጋይ የለም ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጻፈው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በስብከትና በተአምራት በሚያገለግልበት ሰዓት፣ ከቅዱስ ጳውሎስ እኩል ብዙ ሕዝብ እንዲከተላቸውና እንዲያከብራቸው ብሎም እንዲያደንቃቸው የፈለጉ አንዳንድ ካህናት ተብዬዎች የድብትርና ሥራ ውስጥ ገብተው፣ ተቀስፈዋል ፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ላይ ምዕራፍ ዐሥራ ዘጠኝ ከቁጥር ዐሥራ ዐራት እስከ ሃያ ( ሐዋ.19፡14-20) ድረስ በጻፈው ታሪክ ስለለእነዚህ አስማተኛ ደብተሮች እንዲህ ይላል፦
#እግዚአብሔር በጳውሎስ እጅ እጅግ የሚያስደንቅ ተአምራትን ያደርግ ነበር፤ ከልብሱ ዘርፍ ወይም ከመጠምጠምያው ወይም ሰውነቱን የነካ ጨርቅ እንኳ ወደ ሕመምተኞች ሲወስዱ በሽታው ይለቃቸው ነበር ፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ የልብስ ጨርቅ እራፊ በሽተኞችን ሲነካቸው ርኩሳን መናፍስትም ከበሽተኞቹ ይወጡ ነበር ፡፡ በአንጻሩ የቅዱስ ጳውሎስን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማጠልሸት የአይሁድ ካህናት ነን በሚልና የሊቀ ካህናቱ የአስቄዋም ልጆች ነን የሚሉ ሰባት ደብተሮች (ወእሉ ከመዝ ይገብሩ አይሁድ እሙንቱ ደቂቀ ሊቀ ካህናት ዘስሙ አስቄዋ ፡፡ ወሰብአቱ እሙንቱ ) ሰፈር ለሰፈር እየዞሩ አስማት እናውቃለን ይሉ ነበር ፡፡
#እነዚህ ደብተሮቹ አስማት እናውቃለን በሚል አጋንንት እናስወጣለን የሚሉት፣ ከፊሎች ደብተሮቹ በአስማት አጋንንትን እየተጠሩ ወደ ሰው ለማስገባት ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ የገቡትን አጋንንትን ለማስወጣት በጋራ ሆነው ሥራ ተከፋፍለውና በመናፍስት አሠራር ተስማምተው የሚያጠምቁ መሆናቸውን የቅዱስ ሉቃስ አጻጻፍ ያስረዳል፤ እነዚህ ደብተሮች በአንድ በኩል አጋንንትን አስገቢውም እነርሱ ሆነው፤ በሌላ በኩል አጋንንትን አስወጭውም እነርሱ ሆነው እየሠሩ መሆኑ ይታወቃል ፤ ነገር ግን የተለያዩ ቡድኖች ቢመስሉም አንድ ወገን ሆነው ሰውን በአጋንት የሚያሰቃዩ የአጋንት አስመጭና ላኪዎች ናቸው ፡፡
#ወንጌላዊው ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ እንደጻፈለን በጳውሎስ ተአምራዊ አገልግሎት የቀኑት እነዚህ የሊቀ ካህናቱ የአስቄዋ ልጆች ሰባቱ ደብተሮች እንደ ጳውሎስ ለመሆን ፈልገው “ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ ስም” እንድትወጡ እናዛችኋለን እያሉ የጌታን የኢየሱስን ስም ርኩሳን መናፍስት የያዘዋቸው ሰዎች ላይ መጥራት ጀመሩ ፡፡ ነገር ግን ደብተሮቹ እንደሁልግዜው አልቀናቸውም፤ ርኩስ መንፈሱ ሲመልስላቸው ጳውሎስን አውቀዋለሁ ፤ ኢየሱስንም አምነዋለሁ ፤፤ እናንተ ግን ከማን ወገን ናችሁ ብሎ ርኩስ መንፈሱ እንደካዱት ስላወቀ አሾፈባቸው ፡፡
#ከዚያም ልብሳቸውን አስወልቆ ረገጣቸው፤ እነርሱም ቤቱን ጥለው ራቁታቸውን ሸሹ፡፡ ለደብተሮቹ የአስቄዋ ልጆች በኃጢአታቸው ንስሐ ባለመግባታቸው እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ለብዙ ዘመን ዕድሜ ለንስሐ ሰጥቶ ቢታገሳቸውም ፤ ብዙ ዘመን የታመኑለት ሰይጣን ግን ለአንዲት ቀን እንኳን ሳይታገሣቸው በዚህች ቀን ተካድኩ ብሎ ረገጣቸው፤ ይህም ደብተራ በእግዚአብሔር ስምና አገልግሎት ቢያሾፍም ይዘገይ ይሆናል እንጂ መቀሰፉ እንደማይቀር ያረጋግጣል ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በመሐሪነቱ የንስሐ ዕድሜ ቢሰጠውና ቢታገሠውም ሰይጣን ግን ዕድል አይሰጠውም ፡፡
#እውነት ነው!!! በየትም ይሁን በየት “ካህነ ነኝ” “መነኩሴ ነኝ” ወይም “ከሊቃነ ካህናቱ ወገን ነኝ” እያለ ወይም “ከተመረጠው ዘር ነኝ” እያለ በእግዚአብሔር አገልጋይነት ስም የሚያጭበረብር የደብተራ መጨረሻው በሰይጣን መረገጥና ገሃነም መውረድ ነው ፡፡
#ይቀጥላል !!!
ሚያዝያ 21 ቀን 2014 ዓ/ም
ከምሽቱ 5:05 ሰዓት ተጻፈ
#የሲዖል ዜና መዋዕል ጸሐፊ"
#በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ "ደብተራ" አለ ፤ በሙስሊም ውስጥ "ቃልቻ" የደብተራ ክንፍ ነው ፤ በአይሁድ ሃይማኖት ውስጥም "ጸሐፍት" የተባሉት ወገኖች የደብተራ ክንፎች ናቸው ፡፡ የትኞቹም ደብተሮች ሃይማኖት ሳይኖራቸው ሃይማኖት የሚያከሩ ናቸው ፡፡
#ስለ መጀመርያው ደብተራ የጻፈልን ከአዳም ሰባተኛ ትውልድ የሆነው ርእሰ ነቢያት ሄኖክ ነው ፤ መጽሐፈ ሄኖክ የመጀመርያው ደብተራ ማን እንደሆነ ያብራራልናል፤ ትውልድኑም ይዘረዝርልናል ፡፡ የመጀመርያውን ደብተራ መጠርያ ስሙንም በግልጽ ይነግረናል ፡፡ ክፍል ዐራት በእንተ ደብተራ ተከታታዩን ጽሑፍ መቀጠሌ ነው ፡፡
#በመጀመርያ በመጽሐፈ ሄኖክ ምዕራፍ ሁለት ከቁጥር ዐሥራ ዘጠኝ እና ምእራፍ ዐሥራ ዘጠኝ ከቁጥር ዐሥራ አምስት እስከ ሃያ ዘጠኝ (ሄኖክ 2 ፡19እና ሄኖክ 19፡15-29) ያለውን ሄኖክ ራሱ የጻፈልንን የደብተራ ሥራና ትውልድ ደግመው ደጋግመው እንዲያነቡት አሳስባለሁ ፡፡
#በሄኖክ ምእራፎችና ቁጥር ውስጥ የተዘረዘሩት የሁለት መቶው የአስማት ቡድን የሆኑት የደብተራ አባላትና የሃያ አለቆቻቸው ስሞች ናቸው ፡፡ እነርሱም የአጋንንትን አሠራር የተዛመዱና የተዋረሱ የሰው ዘሮች (ደቂቀ ሴት) ናቸው ፤ ዝምድናቸው ከቃኤል ልጆች ጋር በጋብቻም በደብተራ ትምህርትም ስለሚጀምር የቃኤል ልጆች ወይም የቃኤል ትውልዶች ይባላሉ ፡፡ ከሃያው የደብተራ አለቆች ተራ መካከል በዐራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ማለትም የግእዙ ንባብ “ወራብዕ ስሙ ፔንሙዕ” ፡፡ ይለዋል ፡፡ “የአራተኛው አስማተኛ ስም 'ፔንሙዕ' ይባላል” ማለቱ ነው ፡፡፡
#ፔንሙዕ ፤ ማለት የቃሉ መገኛ ዕብራይስጥ ነው ፡፡ በዕብራይስጥ፦ פְּנִימִי, “ፔንሙዕ” ተብሎ የሚነበብ ሲሆን ፊደላዊ ፍቺው “ስውሩ” ማለት ነው ፡፡ በብዕር ውስጥ ተሰውሮ ያለ መጻፍያ ቀለም ማለት ነው ፤ ይኸውም ቀዳሚው "ጽሕፈት ጀማሪና ተረት ጸሐፊ" ነው። "ፔንሙዕ" በመጀመርያ ብዕር መቅረጽን ፤ ቀለም መበጥበጥን ለሰዎች ያስተማረ እርሱ ነው። ሥነ ጽሕፈትን ለመጀመርያ ጊዜ ለሰው ልጆች ያስተማረ እርሱ ፔንሙዕ ነው ። እርሱ ለሰው ልጆች ባስተማረው ሥነ ጽሕፈትም አንዱ በሌላው ላይ በሚጽፉት አሉባልታና ትርክት ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲገዳደሉ አድርጓል ፤ "ፔንሙዕ" የሚለው ስሙ እራሱ ብዕር ማለት እንደሆነ ላቲኖች ሲናገሩ ፔን(Pen) ይሉታል መጻፍያ ብዕር ማለታቸው ነው ፡፡ “ፔንሙዕ” የሚለው ቃል ከፊደላዊው ፍቺ ባሻገር ዐውዳዊ ፍቺው ሲታይ "ስውሩ ጸሐፊ" ማለት ነው ፡፡ ምክንያቱም “ፔንሙዕ” ሆን ብሎ የሰዎች ጉድለትን በመፈልሰፍና የሰዎች በጎ ማንነትን በጽሑፍም በነገርም እየገደለ ሰዎችን ማስፈራራት የጀመረ እርሱ ስለሆነ ስሙ "ፔንሙዕ" ተብሏል፡፡ በስውር መጻፍን ከእርሱ የተማሩ ሰዎች በአንድ በኩል ስማቸውን ሰውረው በብዕር ስም መጠራት የጀመሩት ከ"ፔንሙዕ" ታሪካዊ መነሻው ጀምሮ እንደሆነ ተጽፏል ፡፡ በሌላ በኩል ሰዎች ከ“ፔንሙዕ” በተማሩት መሠረት ስውር ስመ አጋንትን መጻፍን ተለማምደው፤ ኅቡእ ስም እያሉ የተለያየ ድግምቶችንና የመስተፋቅር አስማቶችን ፈብርከዋል ፡፡
+++
#የሰውን በጎነትን የሚገድል ደብተራ ("character assassination" )
#ዛሬም ድረስ የ“ፔንሙዕ” መንፈስ የተዋረሰው ደብተራ ሆን ብሎ ባለህ በጎነት እንዳትመሰገን በእያንዳንዱ ማንነትህ አንጻር ክፉ ነገር ይሰራብሃል፤ በበጎነትህ ላይ ሆን ብሎ ጉድለት ይፈጥርብሃል ፡፡ ደግ ከሆንክ ፤ ደብተራው ክፉ ይልሃል ፤ ያለህን ነገር ለማጠልሸት የለህም ብሎ እራሱ አሉባልታ ፈጥሮ ያወራብሃል ፤ ይህ ዓይነቱ ደብተራ የራሱን ጉድለት የአንተ አድርጎ ያወራል ፤ እራሱ በፈጠረው የስም ማጥፋት ጥላሸት ስምህ የማይሰበር ከሆነ የምትሞትበት ክስና መስቀል ያዘጋጅልሃል ፡፡ ይህ ከጥንት ከ"ፔንሙዕ" ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የደብተራ ጠባይ ነው ፡፡ በአይሁድ ሃይማኖት ውስጥም ጸሐፍት የተባሉት ወገኖች የደብተራ ክንፎች ሆነው አነርሱም ሃይማኖት ሳይኖራቸው ሃይማኖታቸውን አክርረው በክርስቶስ ላይ የተገበሩት የደብተራ ተንኮላቸው ይኸው ዓይነት ነበር፡፡
#ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሲኖር ከአይሁድ ወገን ጸሐፍት ከሚባሉት ደብተሮች ስም ማጥፋት ደርሶበታል ፤ አምላክ ሲሆን አምላክ አይደለም ብለውታል ፤ የሰማይና የምድር ንጉሥ መሆኑን የተረዱ የምድር ነገሥታት ሲሰግዱለት የአይሁድ ጸሐፍት ግን ንጉሣችን አይደለም ብለው ከሰውታል ፤ በቃሉ አጋንትን ቢያወጣ እነርሱ ግን በአጋንንት አለቃ አጋንትን ያወጣል ብለው የራሳቸውን ግብር ሰጥተውታል ፤ በተአምር ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ቢቀይር ተአምር አደረገ ብሎ የተከተለውን ሕዝብ ለማዋከብ እነርሱ ግን ወይን የሚጠጣ (ሰታዬ ወይን) ብለውታል ፡፡
#ኃጢአትሽ/ህ ተወገደልሽ/ህ ተተወልሽ/ህ ብሎ ኃጢአተኞችን ኃጢአታቸውን ሲያስተሰርይላቸው ፣ ጸሐፍት የተባሉት የአይሁድ ደብተሮች ግን አዳኝ ነው ላለማለት የኃጢአተኞችና የሙሰኞች ወዳጅ (ዐርከ መጸብሐን) ብለው ስሙን አጠልሽተዋል ፡፡ ሊደግፉት ሲፈልጉ ከእኛ ወገን ነው ይሉታል ፡፡ ሊቃወሙት ሲፈልጉ "ሳምራዊ ነው" ይሉታል ፤ ከዚያም አልፈው “ሎቱ ስብሐት” የሚያሰኝ ጸያፍ ሲናገሩ “እኛስ እንዳንተ ከዝሙት አልተወለድንም” (ዮሐ.8፡41) ብለውታል ፡፡ እርሱም ሲመልስላቸው በግብር የሰይጣን፤ በሥጋ ደግሞ የቃኤል ዝርያዎች መሆናቸውን ሲነግራቸው “እናንተስ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፤ እርሱ ከጥንት ጀምሮ ነፍሰገዳይ ነው” ይላቸዋል ፡፡ (ዮሐ.8፡44)
#በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የአይሁድ ጸሐፊ ደብተራ ይህን ያህል ክፋት ካደረገ በክርስቶስ ተከታዮች ላይ ከዚህ በላይ ያደርጋል ፡፡ በሀገራችን ደብተራ አመስጋኝ ሲሆን አማሳኝ ይባላል ፤ ደብተራ ሲያመሰግንህ ከልቡ አይደለም ፤ አንዳንዴ በየትኛውም ቋንቋ አፍራሽ ቃል የሆነችውን “ግን” የምትለዋን ቃልን የፈጠረው ደብተራ ሁሉ ይመስልሃል ፤፤ ደብተራ ሊያመሰግንህ ሲፈልግ እገሌ እኮ ምሁር ነው ይልህና “ግን” አልተጠቀመበትም የሚል ሐረግ ያስከትልሃል፤ አየህ ደብተራ ሳይማር የአዋቂ ዳኛ ይሆናል ፡፡ እገሌ እኮ አገባ ይልህና “ግን” አልወለደም፣ እገሊት እኮ አገባች ይልህና "ግን" አልወለደችም የሚል ሐረግ ይጨምርብሃል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ የደብተራ ጠባይ ነው ፤
+++
#የሲዖል ዜና መዋዕል ጸሐፊ (Chronicler of Sheol)
#በመጽሐፈ ሄኖክ እንደተጻፈው የደብተራው ፔንሙዕ ችግር በቀጥታ ሰው መግደል አይደለም ፤ የሐሰት ነገር በመጻፍ ሰው እንዲገዳደል ማድረግ ነው ፡፡ ዛሬ በሃገራችን ደብተራ በጻፈው ትርክት እንደታሪክ እየተቆጠረ ሰውና ሰው ተገዳድሏል ፤ እየተገዳደለም ነው ፤ አንዱ ወራሪ ፤ ሌላው ሰፋሪ ተብሏል ፤ አንዱ ገዢ ፤ ሌላው አገልጋይ ተብሏል ፤ አንዱ ጀግና ፣ሌላው ሰነፍ ተደርጎ ተቆጥሮአል ፡፡ ይሄም ብዙ ሕዝብን በእኩልነት ስም አገዳድሏል ፤፤ መጽሐፈ ሔኖክን የተረጎሙ መተርጉማን ይህንን ሥራ ያስተማረ ሊቀ ደብተራ "ፔንሙዕ"ን ሲገልጹት "ፔንሙዕ" ማለት የመጀመርያው የሲዖል ዜና መዋዕል ጸሐፊ (Chronicler of Sheol) ብለውታል ፡፡ በሱ ጽሑፍ ሰዎች ሁሉ ተገዳድለው ሲዖል ስለሚወርዱ ይህ ስያሜ ተሰጠው ይላሉ ፡፡
#ደብተራ በሃይማኖት ስም የሚጽፈውን ጽሑፍ አንዳንዶች እንደታሪክ ይቆጥሩታል፤ ደብተራ የሚጽፈውን ሁሉ ከሃይማኖት ጋር ስለሚያያይዘው አንዳንዶች ሃይማኖትን ከታሪክ መለየት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል ፡፡ በጥበብ ስም የሚያወራው አሉባልታ እውነት እየመሰላቸው ከጽድቅ ይልቅ ኃጢአትን ተለማምደዋል ፡፡ ምሁር አዋቂ ይመስላቸዋል ፤ #ደብተራ ማለት የተማረ እንዳይመስልህ ስርግው ሐብለ ስላሴ ደብተራ ማለት "ሕዝባዊ ዕውቀት ያለው ነው።" ማለታቸው አማናዊ ትርጓሜ ነው ፡፡ ሕዝባዊ ዕውቀት ማለት መኃይም መሆን ማለት ነው ፤፤ ደብተራ እራሱ ነው እንጅ አዋቂ ነኝ የሚለው ፤ ስለአዋቂነቱ ሦስተኛ ሰው ወይም ወገን ፈትኖ አይመሰክርለትም ፡፡
#በስማ በለው ደብተራ ዐዋቂ መስሎ በተንኮሉ ፣ ጥበብ አውቃለሁ እያለ ያጃጅልሃል ፤ ከዚያም የማይተገበር ነገር ይነግርህና “ፍቱን ጥበብ ነው” ብሎ ይሰጥሃል ፤ ከዚያ ያወቅከውን እንድትጠራጠር ያደርግሃል ፤ ከዚያ የተጠራጠርከውን መልሰህ እንድትጠይቅ ያደርግና በመጨረሻም ከዚያ በጥበብ ስም ሁል ግዜ እግዚአብሔርን በጥርጣሬ ውስጥ እንድታቆየው ያደርግሃል ፡፡ ከዚያም ከእግዚአብሔር ጋር ያለህን ግንኙነት ያቋርጥብህና ግንኙነትህን ከእርሱ ጋር እንድታደርግ ያደርግሃል ፡፡ ይህ ደግሞ ኃጢአት ነው ፤
#ሄኖክ ስለደብተራው ፔንሙዕ መሠረታዊ ሥራውን ሲነግረን ይህ ደብተራው "ፔንሙዕ" በግእዝ “ዘአርአዮሙ ለውሉደ ሰብእ መሪረ ወመዓርዒረ” ተብሎለታል ፤፤ ትርጉሙም “ለሰው ልጆች ጣፋጩንና መራራውን [ቀላቅሎ] ያሳያቸዋል” ይላል ፡፡ ለሰው ልጆች የማይስማሙበትን አሉባልታና ተረት እንደ ታሪክ አድርጎ የሚጽፍ ማለት ነው ፤ ሄኖክ የ"ፔንሙዕ"ን ጽሕፈት መራራ ሲለው ተረት መጻፉን ለማሳየት ነው ፤ ጣፋጭ ሲለው ደግሞ ታሪክ አስመስሎ እንደሚጽፈው ለማስገንዘብ ነው ፤ መጽሐፈ ሄኖክ እንደነገረን ከሆነ በደብተራ መንፈስ የተጻፈውን ሥነ ጹሑፋችንን እንደገና እንድንመረምረው ጣፋጩን ከመራራው ለይተን እንድንመረምር ያደርገናል ማለት ነው ፤፤
#ዳግመኛም_መጽሐፈ ሄኖክ ስለ"ፔንሙዕ" ሲናገርም መራሩን ከጣፋጩ ደባልቆ ይጽፋል ሲል ፡፡ የአጋንንትን ስም የእግዚአብሔር ኅቡእ ስም እያለ መራራ ያደርጋል ማለቱ ነው ፤ ጸሎቱን ሁሉ በእግዚአብሔር ስም ጀምሮ ጣፋጭ ያስመስለዋል ፤ የአጋንንትን ስም ደባልቆ መራራ ያደርገዋል ማለቱ ነው ፡፡ በዚህም መጽሐፈ ሄኖክ የደብተራ አሠራርን ግልጽ አድርጎልናል ፡፡ ለምሳሌ የደብተራ ክታብ ጸሎት የሚለውን ሲጀምር “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ” ብሎ የምታምነውን ጣፋጩን ተናግሮ በቀይ ቀለምና በጥቁር ቀለም አዥጎርጉሮ መራራውን የአጋንንትን ስም በማስከተል ያስትሃል ማለቱ ነው ፤ደብተራ ዛሬም ድረስ በዚህም ክፉ አሠራሩ ምእመናን አስማትና ቀለማት ላይ ተመርኩዘው በእግዚአብሔር እንዳይታመኑ ተጠራጣሪ እያደረጋቸውና ከእግዚአብሔር እያራቃቸው ይገኛል ፡፡
#ለምሳሌ ደብተራ በክታቡ እኔ ጋር ልዩ ጸሎት አለ ግዙኝ ይላል ፤ ልዩነቱን ሲናገር በቀይና በጥቁር ተጽፏል ይልህና የእግዚአብሔርን ቃል ያከበረ መስሎ ጣፋጭ ነገር ይነግርሃል ፤ በእግዚአብሔር እንዳትታመን በቀለሙ ላይ እንድትታመን በማድረግ ጥንቆላ ያለማምድሃል ፡፡ ሄኖክ ስለ ቀይ ቀለምና ጥቁር ቀለም የደብተራ አሠራር ሲገልጽ ለመጀመርያ ግዜ በቀይ ቀለምና በጥቁር ቀለም በመጻፍ ፔንሙዕ የተባለው ደብተራ ሰዎችን ያስት እንደነበር ደጋግሞ ጽፏል፤ ለተከታዮቹ ደብተሮችም ይህንን እርሱ እንዳለማመዳቸው ተናግሯል ፡፡
#እዚህ ላይ የመፍትሔ ሐሳብ ለመጠቆም የምፈልገው የሃይማኖት እውነተኛ ምሁራን በዚህ ዙርያ ጣፋጩን ከመራራው ለይተው ማስተማር እንዳለባቸው ነው ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ነገር ከጥንት ጀምሮ እስከዘለዓለም እስከዚችም ቀን ድረስ ብዙ ሰዎች በጥቁር ቀለምና በቀይ ቀለም ጽሕፈት ይስታሉ ብሎ ሄኖክ ተንብዯልና፤ ምእመናን የትንቢቱ መፈጸምያ እንዳይሆኑ ከስሕተት መጠበቅ የሃይማኖት ምሁራን ግዴታ ነው ፡፡ ምእመናን በፍጹም ልባቸው መጸለያቸው ዋጋ እንደሚያስገኝላቸው ማስተማር እንጅ በቀይ ቀለምና በጥቁር ቀለም ሃይማኖታቸውን ሊያጸኑ እንደማይገባ ማስተማር ሁላችንም ቢሆን ይጠበቅብናል፡፡
+++
#ባለመስተፋቅሩ
#መጽሐፈ ሔኖክ ከመጀመርያው ደብተራ ከ"ፔንሙዕ" አሠራር ጋር አያይዞ ከሚነግረን አንዱ ማሳሰብያ ሰው በማያምነውና በማያውቀው ሰው በፍቅር እንዲወድቅ ማድረግ ዝሙት መሆኑን ነው ፡፡ በፍቅር ስም መስተፋቅር እየሠራ የዝሙት ኃጢአትን በምድር ላይ ያሠራጨ መስተፋቅር ደጋሚና ጸሐፊ "ፔንሙዕ" የተባለው ደብተራ መሆኑን መጽሐፈ ሄኖክ ገልጾልናል ፡፡ እዚህ ላይ የ"ፔንሙዕ" ትልቁ ሥራው ኅቡእ የሆኑ የፈጣሪ ስሞችን አውቃለሁ በማለትና በኅቡእ ስሞች አማካኝነት የመናፍስት አሠራርን ያስተማረ እርሱ ነው ፡፡ የግእዙ ንባብ "ወአርአዮሙ ኩሎ ኅቡአተ ጥበቦሙ።" ይላል ማለትም በጥበብ ስም የአጋንንትን ስውር መረብ ውስጥ ሰዎች በፍቅር ስም እንዲወድቁ ያስተማረ እርሱ ነው ፤፤
#ሰው መስተፋቅር ተብሎ ፍቅር ሲባል ጣፋጭም እውነተኛም ይመስላል፤ ነገር ግን ሐሰተኛ ፍቅርና ሰይጣን የተጎራበተው ውል መሆኑን አይረዳም ፤ ደብተራ ግን መስተፋቅርን ለእውነተኛ ፍቅር አስመስሎ በፍቅር ስም መራራ የአጋንንት አሠራር ውስጥ ይከትሃል ፡፡ ፍቅር እግዚአብሔር ነው ፤ ዝምታህን ጭንቀትን ተመልክቶ የምትወድህንና የምታፈቅርህን የትዳር አጋር ፣ ውኃ አጣጭ የሚሰጥህ እግዚአብሔር ነው ፤ አዳም ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም ያለው እግዚአብሔር መሆኑን አትርሳ !!!! ለሴትም ለወንድም የፍቅር አጋርና የትዳር መሠረት የሚሰጠው እግዚአብሔር እንጅ ደብተራ አይደለም ፡፡
#በመጽሐፈ ሄኖክ እንደነገረን ከላይ ከተዘረዘሩት የደብተራ አሠራሮች ሰዎች ወጥተው በእግዚአብሔር መታመን እንዳለባቸው ሄኖክ አስጠንቅቋል፤ ሰብኳል ፤ ስብከቱን ያልሰሙ በጥፋት ውኃ ጠፍተዋል ፤ በጥፋት ውኃ የጠፋው የደብተራ ትውልድና ተከታዮች ናቸው ፡፡
#በደብተራ ተንኮል ፤ መተትና ተረት ተጠልፈን እንዳንጠፋ የእኔም መልእክት የቅዱስ ሄኖክ መልእክት ነው ፡፡
#ሻሎም !!!
ሚያዝያ 26 ቀን 2014 ዓ/ም
ከምሽቱ 4፡03 ተጻፈ
#ኔፍሊሞች_እነማን ናቸው ??? #የኦሪዮን_ኮከብስ ምንድን ነው??? #ልቡሳነ ሥጋ አጋንንትስ እነማን ናቸው ???
“#በአባት ፣ ሥጋ የለበሰ መልአክ ፤ በእናት ሰው የሆኑ ፣ልቡሳነ ሥጋ አጋንንት አሉ” ፤ የሚለው የደብተራ ወሬ እስከ ዛሬ ድረስ ዓለምን እያሳተ ይገኛል ፡፡ ይህ ዓይነቱ መናፍስታዊ አስተምህሮ በደጋጎቹ መጻሕፍትም በታሪክ መዘግብትም በስርዋጽ እየተሰነቀረ አማኞችን እያሳተና ታሪክን እያጎደፈ አሁንም ድረስ ቀጥሏል ፤ ደብተራ ስለ "ልቡሰ ሥጋ አጋንንት" ሲተርክልህ በዘፍጥረት ታሪክ ላይ ያለውን "የኔፍሊሞችን" ታሪክ ይዞ ታሪኩን ግን በማዛባት ነው፤
#ክብረ ነገሥት የተባለው የደብተራ መጽሐፍ የ"ደቂቀ ሤትን"(በአቤል ምትክ የተወለደው የሤት ልጆችን) ና የደቂቀ ቃኤልን ጋብቻ ታሪክ አዛብቶታል ፤ የቃኤል ሴቶች ልጆችን ያገቡት "ልቡሳነ ሥጋ መላእክት" ናቸው ይላል ፡፡ የክብረ ነገሥት ገለጻ ፣ መላእክት “አዳም ሥጋ የለበሰ ፍጡር በመሆኑ ከእነሱ የተሻለ እግዚአብሔር ለአዳም ውለታ እንደዋለለት አድርገው እግዚአብሔርንም አዳምንም አሙት ፤” ይላል፤ ይኸው ክብረ ነገሥት የመላእክትን ሐሜትንና ያስከተለባቸውን ውጤት ይነግረናል ፤ በዚህ ሐሜት የተሳተፉ መላእክት እንደፍላጎታቸው በጠየቁት መሠረት እግዚአብሔር ሥጋ አለበሳቸው ይለናል ፤ ከዚያም እነርሱም "ልቡሳነ ሥጋ መላእክት" እንደሆኑ ያብራራል ፡፡ (ክብረ ነገሥት ምዕራፍ 100፡) ፤ በክብረ ነገሥት የተጠቀሰውን የመላእክት ሐሜታቸውንና ሥጋ መልበሳቸውን መጽሐፍ ቅዱስ አያውቀውም፤ ድርሳነ ሚካኤል ይህንን ዓይነት ትምህርት በጥር ድርሳኑ ላይ ገድለ ጊዮርጊስን ጠቅሶ የዚህ ትምህርት ምንጭ ሰይጣን መሆኑን በመግለጽ ይቃወማል ፡፡ ለድርሳነ ሚካኤል በክብር እጅ ነስቼአለሁ !! ክብረ ነገሥትን ግን የደብተራ ተረት ነውና ቻዎ ቻዎ ብዬዋለሁ ፡፡
#የድርሳነ ሚካኤልን ሐሳብ ተቀብለን ፣ የክብረ ነገሥት ሐሰትን አውግዘን እንቀጥል ፡፡ በጥንቱ የክብር ነገሥት ዓይነት መዛግብት ውስጥ አጋንንት ወይም መላእክት ሥጋ ለብሰዋል የሚለው የአጋንንት ትምህርት ዛሬም ድረስ በሃይማኖት ጽሑፎች ውስጥ ሥርዋጽ ንባብ ሆኖ እየተሰነቀረ ስርጭቱን ቀጥሏል ፡፡ የትምህርተ መለኮት ምሁራንና የታሪክ መዛግብት ተመራማሪዎች በቅዱሳት መጻሕፍትም ፤ በአዋልድ መጻሕፍትና በታሪክ መዛግብቶቻችን ስለ “ልቡሳነ ሥጋ አጋንንት” የተነገሩ የሚመስሉ በርካታ ንባቦች እንዳሉ እንገነዘባለን ፣ ለትርጉም ተጋላጭና አሻሚ ንባቦችን አቅንተን በመተርጎምና ታሪካዊ አመጣጣቸውን በማሳየት ትክክለኛ ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን ማሳወቅ ይጠበቅብናል ፡፡በዚህ መልኩ ቀስ በቀስ “ቃለ ደብተራን” “በቃለ እግዚአብሔር” በማረምና አማናዊ ታሪክን በማስተማር ትውልዱን ማነጽ ይቻላል ፡፡ ይህን ባለማድረጋችን ግን ተማርን የሚሉ ዘመናውያን ደብተሮችን አፍርተናል ፤ እነዚህም ዘመናዊ ደብተሮች ታሪክን ከተረት ጋር እየቀላቀሉ ሕዝቡን የታሪክ በሽተኛ፤ አማኙን የሃይሞኖት ስደተኛ እያደረጉት ይገኛሉ ፡፡
#ለዚህ ማሳያው አንድ መጽሐፍ ብቻ ልጥቀስ ፤ #የሳጥናኤል_ጎል_በኢትዮጵያ1,2,3 በሚል የተጻፈውና የተተነተነው ልቦለዳዊ መጽሐፍን ላነበበ ሰው ጸሐፊው በሚገባ እንደተደበተረበት ይረዳል ! መጽሐፉ በውስጡ የሚያወራው "ኔፍሊሞችን" እየጠቀሰ የልቡሳነ ሥጋ አጋንንትን በሥጋ መኖርና በጋብቻ ትውልዳቸውን ማስቀጠላቸው ነው ፤ ባጭሩ “የሳጥናኤል ጎል በኢትዮጵያ” የሚለው መጽሐፍ "በሥጋ የሳጥናኤል ትውልድ አለ" እያለን ነው ፤ ለዚህ ማሳሳቻ እንዲሆነው ኢትዮጵያውን ብቻ ከሰማንያ አሐዱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምንቆጥረውን መጽሐፈ ሄኖክን በመጥቀሱ፣ ሰዉ እውነት የጻፈ እየመሰለው በአድናቆት ተቀብሎታል ፡፡ እንደ እውነታው ከሆነ በዘፍጥረት መጽሐፍ የተጠቀሱትን ኔፍሊሞችን መጽሐፈ ሄኖክና ሌሎችም መለኮታዊ መጻሕፍት ትውልዳቸውን በሰፊው ሲያብራሩት የሳጥናኤል ጎል የተባለው የደብተራ መጽሐፍ በሚለው መንገድ የሳጥናኤል ትውልድ አያደርጓቸውም ፤ አሁን እየጻፍኩት ያለው “የጸረ ደብተራው ንቅናቄ” (Anti-clericalism) ተከታታይ ጽሑፍ በቀጠለ ቁጥር በኔፍሊሞች ስም የሚሰራው የዘመናዊ ደብተሮች ሴራቸውና ዓላማቸው ሳይቀር ይጋለጣል ፡፡
#ምክንያቱም የኔፍሊሞች ታሪክ ከተዘገቡበት ጥንታዊ መዛግብት ውስጥ የኒፍሊሞችን ማንነታቸውን ስናጠና የምናገኘው እውነት ከደብተሮቹ የሴራ ሽረባ ጽንሰ ሐሳብ (Conspiracy Theory) የተለየ መለኮታዊ እውነትን ነው ፡፡ መጽሐፈ ሄኖክ በግእዝ ፤ በዕብራይስጥ ፤ በስሎቫኪያ ፤ በግሪክኛ ቋንቋ ይገኛል ፡፡ የመጽሐፈ ሄኖክም ሆነ የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ያለው የልሳነ ግእዝ ምንባባት "ኔፍሊሞችን" “እለ ያርብሕ” ብሎ በግእዝ ይጠራቸዋል ፤፤ ትርጉሙም “ግዙፎች ቁመተ ረጃጅሞች” የሰው ዘሮች ማለቱ ነው ፡፡ በርግጥ ግእዙ “ኔፍሊም” የሚለውን ቃል “እለ ያርብሕ” ብሎ ሲመልሰው ፊደላዊ ፍቺው “አርበኛ የሆኑ ” ማለት ነው ፤ ቃሉ በግሪክ አፈ ተረት “ናፌሊ” (Νεφέλη) ተብሎ ከአማልክት ትውልድ ጋር ይጠቀሳል ፤ ይህ የአፈ ታሪኩ መነሻና የቃሉ ትርጉም ለደብተራ ተረት መነሻ ሆኗል ፤ ነገር ግን የጥንት መዛግብት “ኔፍሊም” የሚለውን ቃል ሲጠቀሙ ፊደላዊ ትርጉሙን አይተው እንጂ አፈ ታሪኩን ተከትለው አይደለም ፡፡ “ናፌሊ” (Νεφέλη) ማለት ከኔፎስ (νέφος) "ደመና" ለማለት እንደመጣ የግሪክ ቃላት ሥርወ ቃል (Etymology) መገኛ ጥናት ያስረዳል ፡፡ ይህም ቃል በዚህ ትርጉም መሠረት ሰማይ ጠቀስ የሆነ ግዙፍ ሰው ሲጠቀስበት ስመ ጥር ጀግና፤ የወንዶች ቁና ፣ አርበኛ ማለት ይሆናል ፡፡ መጠኑና ቁመቱም፤ ወርዱና ስፋቱም ከሰው ልክ ያለፈ ፤ ማለት ነው ፡፡
#በርግጥ “ኔፍሊም” የሚለው ቃል በዕብራይስጥም ትርጉም አላጣም፤ የዕብራይስጡ ቋንቋ “ኔፍሊም” የሚለውን ቃል ሲፈታ “ናፋል” (נָפַל) የሚል መነሻ ቃልን አግኝቶ ትርጉሙም ግዙፍ ሰውን ከመግለጽ ባሻገር “መገንደስ” ወይም “ወውደቅ” ወይም “መጋደም” ወይም "ተምዘግዝጎ በፈቃድ መውደቅ' ፤ ወይም "ከክብር ማነስ" የሚል ምሳሌአዊ አነጋገርን የያዘ ነው ፡፡ የዕብራይስጡ "ኔፍሊም" ዐውዳዊ ፍቺው የኔፍሊሞችን የምድረ ፋይድ ኑሮ ይገልጻል ፡፡ ሲደመደም “ኔፍሊም” የሚለው የግሪክና የዕብራስጡ ቃል ወደ ግእዝ ሲመጣ "ያርብሕ" "አርበኛ" ተብሎ ተተርጉሟል ፤ ይህም ተክለ ቁመናቸውን ጦረኛነታቸውን ተመልክቶ የተሰጣቸው ስም መሆኑን ያረጋግጣል ፤ መጽሐፍ ቅዱስም በገጸ ንባቡ "ኔፍሊም" የሚለውን ቃል ሲፈታው "ኔፍሊሞች" የሰው ልጆች መሆናቸውን ከገለጸ በኋላ “በጥንቱ ዘመን በጀግንነታቸው ከፍ ያለ ዝና ያተረፉ ናቸው ፡፡” ሲል መዝገበ ቃላታዊ ፍቺውን ያረጋግጥልናል ፡፡ እነ ጎልያድ ፤ እነ ደቂቀ ኤናቅ የዚህ ትውልድ ሰዎች መሆናቸውም በቅዱስ መጽሐፍ ተመዝግቧል ፡፡ ( ዘፍጥ.6፡4)፤
#ኔፍሊሞች” ከጥፋት ውኃ በኋላ እንኳን የሰው ዘር ሆነው ትውልዳቸው ቀጥሎ በአስማትና በኮከብ ቆጠራ ስራ እየተዳደሩ የሚኖሩ ደብተሮች ሆነው መቀጠላቸውን መለኮታዊ መጻሕፍት ይናገራሉ ፡ (ዘኁልቁ.13፡ 33) እነዚህም "ኔፍሊሞች" በሰውነታቸው ግዝፈት "ኔፍሊም" የሚል ስም እንዳገኙ ሁሉ በግብራቸው "ኮከብ ቆጣሪ" ፣ "መናፍስት ጠሪ" በመሆናቸው ደግሞ "ረአይት" ተብለው መጠራታቸውን የግእዝ መዛግብት ያስረዳሉ ፡፡ የግእዝ ምንባባት "ኔፍሊሞችን" ሲጠሩ “ኔፍሊም” ወይም “ረአይት” (ረዐይት) ከሁለት አንዱን መርጦ በማፈራረቅ ከሁለቱ በአንዱ ስም ይጠራቸዋል ፤ አማርኛውም የግእዙን ምንባባት ስለሚከተል አንዳንዴ “ኔፍሊም” ፤ አንዳንዴ ደግሞ “ረዐይት” (ረአይት) እያለ ይጠቅሳቸዋል ፡፡
#በግእዝ ቋንቋ መዛግብተ ቃላት ምስክርነት በዐይኑ "ዐ" ተጽፎ ‹‹ረዐይት›› የሚለው ቃል ግእዙ “ኔፍሊም” ለሚለው ቃል “ያርብሕ” ብሎ የሰጠውን ተመሳሳይ የፍቺና ትንታኔ ይደግመዋል ፡፡ በአልፋው “አ” ‹‹ረአይት›› ሲጻፍ ፍቺው ከ ዐይኑ “ዐ” ‹‹ረዐይት›› በትርጉም ይለያል፤ የአልፋው “አ” ‹‹ረአይት›› የሚለው ንባብ ፣ ኮከብ ቆጣሪነት የሆነውን ሥራቸውን ይገልጻል ፡፡ በዐይኑ "ዐ" ሲጻፍ ‹‹ረዐይት›› ማለት ግን ግዙፍነታቸውን ይገልጻል ፡፡ “ረአይት” ማለት ግብራቸውን ሲገልጽ ኮከብ ቆጣሪ መናፍስት ጠሪ ማለት ነው ፡፤ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ፣ ዎልፍ ሌዝላው (Wolf Leslau)ና ኦገስት ዲልማን (August Dillmann) ሦስቱም በየመዛግብተ ቃላቸው ‹‹ረአይት›› የሚለውን ቃል ሲተረጉሙ የአረማይክን ባህል ሳይዘነጉ በዚህ መልኩ ትንታኔ ሰጥተውበታል፡፡ እንደ መዛግብተ ቃላቱ ፍቺና ትንታኔ ‹‹ረአይት›› ማለት “ርእየ” ማለትም “አየ” ከሚለው ግስ የመጣና ‹‹ረአይት›› ማለት "የሚያዩ" ማለት እንደሆነ ተብራርቷል ፤ ከእነ ሌዝላው ትርጉምና የግእዝ ቃላት ምስክርነት “ረአይተ ኮከብ” -"ኮከብን የሚያዩ"፣ “ረአይተ ከዋክብት”- "ከዋክብትን የሚያዩ" ሲል ቃሉ ኮከብ ቆጣሪነትንና መናፍስት ጠሪነትን ያብራራል ።፡ በአረማይክ ባህል "ኔፍሊም" የሚለው ቃል “ኦሪዮን” በተባለው አውራ ኮከብ የሚመሩትን ከዋክብትና የከዋክብት ክምችት አተረጓጎምን (ፍካሬ ከዋክብት) የሚያውቁ አስማተኞችም ይጠሩበታል ፡፡ ይህም ቃልና ታሪክ የተወሰደው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ካለው የ"ኔፍሊሞች" ድርጊት ጋር ተያይዞ ነው ፡፡ በለዓም ከረአይት ወገን የሆነ "ኔፍሊም" ሲሆን ኮከብ ቆጣሪ ረአይታዊ ነው ፤
#በዚህ መሠረት በግእዛችን “ረአይት” ማለት በተለዋጭ ስም "መሰግላን" ወይም “ሰብአ ሰገል” ይባላሉ ፡፡ አብዛኛው የፈረንጅ መጽሐፍ ቅዱሶች “ሰገልን” “ጥበብ” እያሉ ተርጉመዋል ፤ ግን ሐሰት ነው ፤ “ሰገል” ማለት ጥንቆላ ኮከብ ቆጠራ እንጅ ጥበብ አይደለም ፤ የአማርኛችን መጽሐፍ ቅዱስ “ሰብአ ሰገል” ይላል እንጂ የጥበብ ሰዎች ብሎ አይተረጉማቸውም ፡፡ ለማንኛውም “ሰብአ ሰገል” ማለት “ረአይቶች” መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል ፡፡
#የነዚህ “ሰብአ ሰገል” ወይም የ”ረአይት” ሀገራቸውም አራም(ራ-ጠብቆ ይነበብ) ወይም ሜሴፖተምያ ወይም በአቅጣጫ የምስራቅ ተራራ ይባላል ፡፡ ሰብአ ሰገልም የበለዓም ወገኖች ናቸው፤ ትውልደ ሐረጋቸውና መንደራቸው ምሥራቃዊው ከሆነው ከቃኤል ሀገር ነው ፡፡ #ሰብአ ሰገል ከበለዓም ወገን የሆኑ ረአይት መሆናቸው በበርካታ የጥንታዊ የሰነድና የመዛግብት ጥናቶች ተረጋግጧል ፤ ከግብጽ ባርነት ወጥቶ በመንገድ ሲጓዝ የነበረው ሕዝበ እስራኤል በመንገድ ሲያልፍ በለዓም ረአይታዊ እንዲረግም ተጠርቶ ነበር ፤ በለዓም ረአይታዊ ለመርገም ሲሄድ ግን ተአምራዊ ክስተት አጋጠመው፤ የእግዚአብሔር መልአክ በመንገድ አገኘው፤
#በለዓዐም ኮከብ ቆጥሮ ሊናገር ያለውን ሟርት ትቶ እግዚአብሔር የባረከውን ሕዝብ መርገም እንዳይችል መልአኩ አስጠነቀቀው፤ ይልቁንም በለዓም በሚጠነቁልበት “የኦሪዮን ኮከብ” ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስን በእናቱ እቅፍ ላይ ሆኖ እንዲታየው አድርጎታል ፡፡ መልአኩም በለዓም በኮከቡ ላይ ያየውን መለኮታዊ ተአምርን ሲመለከት ሊረግመው ካሰበው ከያዕቆብ ሕዝብ መሲሕ እንደሚወለድ ተነበየ፦ “ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል ፤ የሤትንም ልጆች ሁሉ ይማርካል ፡፡” ብሎ (ዘኊ.22፡34፤24፡17) በትንቢቱ ውስጥ የሤት ልጆችን ታሪክ ከመጽሐፈ ሄኖክ ጠቅሶ በመሲሑ እንደሚማረኩ አስቀድሞ ተናገረ ፡፡
#ሰብአ ሰገልም የበለዓም ረአይታዊውን ቃል ፦ “ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል ፤ የሤትንም ልጆች ሁሉ ይማርካል ፡፡” የሚለውን ትንቢት ተመርኩዘው ክርስቶስ ወደ ተወለደበት ወደ ቤተ ልሔም መምጣታቸውን ወንጌላዊ ማቴዎስ ነግሮናል ፤ በክርስቶስ ልደት ጊዜ መለኮታዊ ተአምር መከሰቱንና መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት መኖሩን ማቴዎስ አሳውቆናል ። ከበርካታ ክስተቶች መካከልም የምሥራቅ ሕዝቦችን ከጥንቁልናና ከኮከብ ቆጣሪነት ለመታደግ መርጦ የሰብአ ሰገልን ታሪክንም ጽፎልናል፡፡
#የሰብአ ሰገል ታሪክ እውነታው ይህ ነው ፡፡ የእኛ ብሔራዊና ዘመነኛ ደብተሮች ግን ስለ ሰብአ ሰገል የሚሉት አይጠፋቸውም ፤ የምርምር መሥፈርትን በመጣስ “ የኦሮሞና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ “ ጎጃም ነው ብሎ ለመናገር ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የገባበት ድብትርና አዝናንቶኛል ፤ እንደ ፍቅሬ ቶሎሳ አገላለጽ ሰብአ ሰገል የተባሉት "የደሸት ልጆች" ከጎጃም ተነሥተው ወደ ቤተ ልሔም ሄደዋል የሚለውን ተረት ከሱ በቀር የሚያውቀው የለም ፡፡ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የጻፈው ይህ ትርክት እጅግ መስሐቲ ስርዋጽ ነው ፤ የፖለቲካ ግን ማጣፈጫ ነው ፤፤
#የፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ አሁን ባለንበት የለውጡ ዋዜማ የተጻፈ ስለነበር ለ"ኦሮማራ" ጥምረታዊ ፖለቲካ ተፈላጊ ሚና ነበረው ፤ በዚህ ደረጃ ወቅቱን የጠበቀ ርእዮት ስለነሆነ ያገናዘበው ሰው አልነበረም ፤ ይሁን እንጂ በታሪክ አጻጻፍ ዘዴ ሲመዘን ዐይን ያወጣ ሐሰትና የደብተራ ተረት ነው ፤ ለፍቅሬ ቶሎሳ ፕሮፌሰርነቱ እንደተጠበቀ ደብተራነትን ደርቤለታለሁ ፡፡ ይደልዎ !!!
#በታሪክ መዛግብት ጥናት ዘዴ ቀዳምያን ምንጮቻችንን ስንፈትሽ አማራና ኦሮሞ አንድ ናቸው ለማለት አማራነት ከመነሻው የካም ዘር ነገደ ኩሳ (ኩሽ) መሆኑን በግልጽ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ጠቅሰን ማስረዳት አለብን ፡፡ በተጨማሪም “አማራ” የተባለው ሕዝብ መለያው ቋንቋ መናገሩና ያም ቋንቋ “አማርኛ” መባሉ ፤ በተለይ በዛሬ ዘመን "የአማራ ክልል" ውስጥ ያለ ሕዝብ መኖሩ ብቻ አማራን ከካም እና ከኩሽ ቤት አውጥቶ ሴማዊ ቤት ውስጥ ከትቶታል ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን "አማራ" የምትለዋ ቃል ከተገኘችበት ቀን ጀምሮ አማራነት ፣ ነገደ ካም እንጂ ነገደ ሴም ሆኖ አይደለም ፤ ከዘመን በኋላ ግን ክብረ ነገሥት የተባለው የደብተራ መጽሐፍ "አማራነት" ላይ ሴማዊነትንና ሰሎማዊነትን ደርቦለት ከነገደ ካም አውጥቶ ነገደ ሴም ውስጥ ከትቶ በምናባዊ ዓለም አኑሮታል ፡፡
#አማራነትና አሮሞነት አንድ የሚሆነው አማራ ከክብረ ነገሥት ተረት ተረት ሲላቀቅ ብቻ ነው ፡፡ ክብረ ነገሥት ሁሉንም የሰው ዘር በየነገዱ እየከፈለ አይሁዳዊ ያደርጋል ፤ የክብረ ነገሥት ደብተራም ፣ አማራን ሴማዊ ሲያደርግ የተመለከቱት የኦሮሞው ድብተራ የሆኑት አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅ ጅራም ኦሮሞ ማለት "አረማይክ" ከሚለው ሴማዊ ሰው የመጣ ነገደ ሴም ነው ብለው እርፍ ብለዋል ፡፡
#ይህ ዓይነቱ “ነገደ ሴም” ነኝ እያሉ መፎካከሩ የተጀመረው በሀገራቸን ብቻ ሳይሆን በውጭውም ዓለም ያለ ፉክክር መሆኑን ፕሮፌሰር ዓማኑኤል ጽፈዋል ፡፡ ሴማዊነት አለን መባሉ እውነት እንኳን ቢሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ሴማዊነት ማለት በሰንበት ላይ ደብረዘይት እንደማለት በጋብቻ ትስስር ደርቦት ያገኘው ማንነት እንጅ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሠረቱ ካማዊነት ነው ፡፡ በተለይ "የዛሬው ትውልድ አማራ" ሲበራለትና ነገደ ካም መሆኑ ሲገባው ስለ አፍሪካ አንድነት በጋራ አንድ ሆኖ ይቆማል ፤ አክሱም ማለትም የካም ሀገር ማለት እንደሆነ ማረጋገጥ ሲቻል በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሕዝብ የሚታይበት ልዩነትም ቢሆን የቋንቋ (ጎሳ) ልዩነት እንጅ የደም ልዩነት አለመሆኑን መረዳት ይቻላል ፡፡ በሃይማኖትም ቢሆን አብርሃም አባት አለኝ ማለት በዋናነት እንደክርስቲያን ወይም እንደሙስሊም አልያም እንደሌሎች ሀገር በቀል እምነቶች "አብርሃም የመንፈስ አባት" እንደሆነ እንጅ የሥጋ አባት መሆኑን ለመናገርና ሴማዊነትን በሥጋ ትውልድ ለማስቀጠል አይደለም፡፡ ይኸው ነው!!!!!!!!!
#ይህ ጽሑፍ #ክፍል_አምስት በእንተ ደብተራ የተከታታይ ጽሑፌ አካል ነውና ስላነበቡት አመሰግናለሁ !!!
#ሻሎም
ግንቦት 3 ቀን 2014 ዓ/ም
ከምሽቱ 4፡10 ሰዓት ተጻፈ
ሸዋ ፤ አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
Comments
Post a Comment