የኢየሱስን እናት ብፅዕት ማርያምን አትሳደቡ! (2)

 ማርያምን አትሳደቡ! (2)

መግቢያ 

1.ስሜ ማርያምና በስሜ ማርያም ፈውስ 

2.ማርያም የክርስቶስ እናት መሆኗን መቼ አወቀች !?

3.የጥበብ ሰዎችና ስግደታቸው 

4.አብርሃም ወደ ከነዓን ለምን ወጣ !?

5.ሎጥን ያዳነው ማን ነው !?

6.መላእክትን የሚያዘው ማን ነው !?

7.ለክርስቶስ መቃብር ጥበቃ ለምን ተቀጠረለት !?

8.ሰዎች ሁሉ ማንን ይለምናሉ !?

9.የሐዋርያት ሹመት በማርያም ነውን !? 


ማጠቃለያ 

ዋቢ መጽሐፍት 


                    መግቢያ! 

ከዚህ በፊት የቀረበውን ካነበባችሁ በኃላ እንደተጠቀማችሁ ተስፋ አደርጋለሁ ።የመጀመሪያ የጹሑፌ ዓላማ የኢየሱስን እናት እኔ (እኛ) እንደማል[ን]ሳደብ እና ማን እንደ ሚሳደብ በግልጽ ማሳየት ነበር።ይዚህኛው ዓላማ ግን የስህተት ትምህርት ዲቃላ ፍሬ ስለሚያፈራ በማሳየትም የበጉ የሆኑትን መለየት ነው ።


ቃሉ እንደሚል “..፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤”— ዮሐንስ 10፥4 ፣ ስለዚህም የኢየሱስ የሆኑቱ ድምጹን ለይተው ያውቃሉ ፤ የሚከተሉትም እርሱንና እርሱን ብቻና ብቻ ነው።እረኛውን ስለሚያውቁ መጽሐፍ እንደሚል “ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፥ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና።” — ዮሐንስ 10፥5 ።ስለዚህም ወዳጆቼ አንድ ሰው ሃሰተኛ ትምህርት ፦ አስተማሪ፣ነቢይ ፣ሐዋርያ .. የሚከተል ከሆነ እረኛውን የማውቅ ፣ድምጹንም የማይለይ ፣በግም ያለሆነ  በመሆኑ ነው ማለት ነው።ባይሆንማ ቃሉ እንደሚል አይከተሉም።ይሸሹም ነበር ። 


ስለዚህም እንደ አንድ ክርስቲያን ሸክም እንደሚሰማው ሰው፣በእውነት ቃል ላይ ለዘመናት የተሸቃቀጠውን በመግልጽ እና በመቃወም ክርስቲያንነተን አሳውቃለሁ ።በእውነት ቃል አይታፈርምና፤ማንም እና ምንም አያስቆምም፤ቆሞም አያውቅም። 


በመጨረሻም በስህተት ትምህርት ላይ አምርረ የሚቃወመው መጨረሻው ጥፋት [መቃጠል] ስለሆነ ነው።ሔዋን ኀጥአት ከመስራቷ በፊት በመጀመሪያ የተደረገችው የእውነትን ቃል መጣል እና መካድ ነበር [የስህተት እውቀት መቀበል ነበር]።እግዚአብሔር ያለው “..፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።”ነው ፣ ዘፍ 2፥17 ፤ዲያብሎስ ደግሞም ያለው “..፦ ሞትን አትሞቱም፤”ነው፣ዘፍ 3፥4 ።ከዚህም በኃላ ነበር ሔዋንም የሳተችው ፤ለኀጢአት የደፈረችው ።ጅማሮው የስህተት እውቀት ነው።መጨረሻውም የሞት ሞትም ነው።


ወንድሞቼ የስህተት እውቀት ይዘው እንኳን ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅሱት ፣ እንደ መንፈስ ወርዶ የስህተት ትምህርት ስለገባ ሳይሆን አዕምሮአቸው "ልክ ነው " ብሎ ስለመዘገበው ነው።እናም ይህ የሚቀረፈው ደግሞም በእውነት ትምህርት ፤በእውነት ቃል በመተካት ነው።


ስለዚህም ብዙ ነገር የሚትገነዝቡበት ይሁንላችሁ ።"ነገሩ እንዲህ ይሁን !? " እንደ በሪያ ሰዎች ማለት ይሁንላችሁ።ደግሞም ያወቃችሁትን እውነቱን ጠብቁ ፤ ብዙ ተስፋ አለን[የማይጠፋ ሕይወት] ፤በትዕግሥት ጠብቁት።ኢየሱስ ልመጣ በደጅ ነው።


“የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥”

  — 2ኛ ቆሮ 10፥5 

.....

1. ስሜ ማርያም 

☝ ማርያም ማለት መግንሥተ ሰማይ የሚታስገባ ማለት ነው ። (የሉቃስ  አንድምታ ም.1 ፣ትንሳኤ ማተሚያ ድርጅት፤ተአምሬ ማርያም) ፣

☝በአንዳንድ ትናንሽ ስዕል ጀሪባ ያሉ ጹሑፎች ደግሞ ''መንግስተ ሰማይ መሪታ የሚታስገባ " ይላል  ፣ 

☝ እንድሁም ለእያንዳንዱ ፊደል ትርጉም በመስጠት"ማ፣ር፣..." ማለት እያሉም ይተረጉማሉ ።ለምሳሌ ፦"ማ" ማለት 'ማህደረ መለኮት ማለት ነው'  ፣" ያ" ማለት አንቺን ይለምናሉ ..ወዘተ በማለት ይተረጎማል ።ሁሉንም በዚህ ልክ መዘርዘር አልችልም ።


ግን መዝገበ ቃላት ምን ይሏል ፦ 

☝<< ቃሉ ሁለት ነው።አንደኛው ማር ፡ሚር ፣ መራራ መራር  ።ዘመኔ ልደቷ መራር ..እስራኤላውያን ምርር እርር ብሎ ያዘኑበት ያለቀሱበት የሃዘን የመከራ ወራት ነው ስሉ አባት እናቷ ..እንደዚህ ይጠሯዋታል።ዘፀ 8 _16 ፣

ሁለተኛው ትርጉም ደግሞ ፦ ማር ፡ሚር ፣ሬቶ ሐምቶ የሚባል ኮከብ ፡ያም ባህር ይሆናል ..ባህርም የዘመን ምሳሌ ነውና..።>>  (ኪዳኔ ወልደ ክፍሌ) 

☝ ማርያም የሚለው 'mer-ee' ከሚል ቃል የወጣ ሲሆን ትርጓሜውም መራራ ማለት ነው።"(strong ) 


       ከመዝገበ ቃላት የተተረጎመውን በልባችን ይዘን ስሜ ማርያም ምን ሥልጣን እንዳለው እንየው ፦

አንዳንድ ሰዎች "በማርያም ስም"በማለት ሰይጣንን ለማውጣት የሚያደርጉትን ንትርክ በአትሮኖሱ መመልከት ከተጀመረ ሰንበትበት ብሏል።መጽሐፍ ቅዱስ የሚያነብ አንዳንድ ጎበዛዝቱ "የእኛ ትምህርት አይደለም"ብሉም ፣ ምንም ለውጥ አልመጣም።ምክንያቱም እውነተኛ ትምርቷ ነው።እንዲያ ባይሆን "በኢየሱስ ስም" በሚያስተምሩት ላይ ብቻ እርምጃ ለዚያውም አፋጣኝ እርምጃ አይወሰድም ነበር።


በስሜ ማርያም መፈወስ 'የቤተክርስቲያቱ' ትምህርት መሆኑን ከአትሮኖሱ ባሻገር የአዋልድ መጽሐፍት ማስረጃም አለ።ተመልከቱ ፦ "..በድናጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ በጸናች በክብርት እመቤታችን ስም እንደቀድሞው ተመለስ አለው ያን ጊዜም ዳነ" (ተአምሬ ማርያም ም.፬ ፣ገጽ ፵ ፣  ት.ዘ.ጉባኤ 1989)።ሌላም ማስረጃ ደግሞም አለ፦ " አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች የክብርት እመቤታችን ስም ይህች ናት።በተጠራም ግዜ የሰማያት ፀናታቸው የምድር ግዘፍ እስከ ሲኦል መሠረት ድረስ ይናወጣል።ቅጠል ነፋስ ባናወጠው ጊዜ እንዲረግፍ የመላእክት ክንፋቸው በመደገጥ ልረግፍ ልረግፍ ይላል ።ይህ ስም በተጠራ ግዜ የፉጡራን መደንገጥ ይቅርና የሁሉ ሥልጣን በእጁ የተያዘ ልጇ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጥዑን በፊቱ አቁሞ የበቀሉን ፍርድ በገለጠ ጊዜ በኃጥዐን ፊት ላይ በቃል ኪዳን ቀለም የተጻፈ የድንግልን ስም ሲጠራ ሰምቶ የአደባባዩን ፍርድ ትቶ በቸርነቱ በኀጥአን መፍረድን ይተዋል "(ድ.ኪ.ምህረት ገጽ 26፣2010ዓ.ም ት.ማተሚያ ቤት) 


ስለዚህ በማስረጃው መሠረት ስሜ ማርያም 'መፈወስ ብቻ ሳይሆን ፍርድን የሚያቀለብስ ፣ምህረትን የሚያሰጥ ፣ የመላእክትን ክንፍ ልረግፍ ልረግፍ የሚያስብል፣ከሰማይ እስከ ምድር ሲኦል የሚያናውጥ 'ስም'  ነው.. '  መባሉን አይታችኋል ።'


መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ምን ይለናል ፦

ሐዋርያት 4 ፥ ⁷ እነርሱንም በመካከል አቁመው፦ በምን ኃይል ወይስ በማን ስም እናንተ ይህን አደረጋችሁ? ብለው ጠየቁአቸው። …   ¹² መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና። 


☝ መጽሐፍ ቅዱስ "መዳን በሌላ በማንም የለም" ብሎ ፣ "የተሰጠን ሌላ ስምም የለም" የሚለን ከሆነ ፣ በስሜ ማርያም "እንፈውሳለን" ወይም "ይፈወሳል" የሚሉ ሁሉ ሃራጥቃን ናቸው ።

☝ ሌላው ሁሉ የአሮግቶች ተረት ነው።ምንም እኮ ጥቅስ አያስፈልግም "ማርያም የሚለው ስም ብፈውስ አንድ ብሎ የሚፈውሰው 7 አጋንንት ያደረባትን ነው" ግን ምን ያደርጋል መጽሐፍ እንደሚል “ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ፦ ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ?..።” — ሮሜ 10፥16 ፣እንዳለው ነውና።


ስለዚህም እኛ “የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥”— 2ኛ ቆሮ 10፥5 

..........

2.ማርያም የክርስቶስ እናት መሆኗን መቼ ታወቀ !?


'ከሦስት አመቷ ጀምራ በቤተመቅደስ ውስጥ ፣ ሰው የሚበላውን እህል ሳትበላ ፣ መጠጥም ሳትጠጣ ያደገችው 'ማርያም' ፣ ገና በሦስት አመቷም የኢየሱስ ክርስቶስ እናት መሆኗ እንደሚታወቅ የቤቷ ማስረጃዎች ያበስራሉ ' (ተ.ማ ገጽ 19 ት.ዘጉባኤ.ማ 1989፣ዜና ማርያም ገጽ 24፣2010 ዓ.ም ፣ወ.ቅ አንድምታ ፣ው.ማርያም....ወዘተ) 


ማርያም ገና በ3 ዓመቷ ቤተሰቦቿ ወደ ቤተመቅደስ ስያመጧት ፦ "ካህናት በቤተመቅደስ ያሉ ሁሉ በሰሙ ግዜ ለመቀበል ወጥተው መንፈሳዊ ሰላምታ ሰጧቸው ..።እመቤታችንንም ለእግዚአብሔር ለእናትነት የተመረጥሽ ንዕድ ክብርት ሆይ ፍቅር ይገባሻል አሏት ።( ተአምረ ማርያም ተስፋ.ገ.ሥ ማተሚያ ቤት ም.2፣ ት.ዘጉባኤ.ማ ገጽ 19 )


በዚህ ታርክ መሠረት የመቅደሱ አገልጋዮች እና ወላጆቿ ማርያም የኢየሱስ እናት እንደሆነች አውቀዋል ማለት ነው።ልብ በሉ።በሌላ ክፍል ደግሞ ከእግዚአብሔር በቀር ማንም እንዳላወቀ ይተርካል ።"ከአባቴና ከመንፈስ ቅዱስ በቀር የእኔን ሰው መሆን ያወቀ የለም"( ተአምሬ ማርያም ት.ዘጉባኤ.ማ ገጽ 38 ) 


ይህ ትርክት ይቀጥላል በወንጌል ቅዱስ አንድምታ መጽሐፋቸው ላይም ፤ ማርያም እንዳረገዘች አውቀው ፣ከቤተመቅደስ በማውጣት ለዮሴፍ አስጠንቅቀው እንደሰጧት ይተረካል። 


ተአምሬ ማርያም ስሁት ነው።አንደኛው ነገር እርስ በርስ ይጋጫል ፣ሁለተኛው ነገር ታርኩ ራሱ ተአማኒነት የለውም "የእግዚአብሔር እናት መሆኗን አውቀው አመሰግኗት" ብሎም፣እንደገና መልሶ "ቤተመቅደስ ታስረክሳለች" ብለዋት ፣ "ከቤተመቅደስ አወጧት"ብሎ የሚነገረው ትርክት የደብተራ ተንኮል ነው።


መጽሐፍ ቅዱስ ግን እንዲህ ይለናል“ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ።”— ሉቃስ 1፥27 ።ስለዚህም የታርኩ ውሸት የተገለጠ ነው ። የእግዚአብሔር እናት መሆኗን ቀድሞ ካወቁ ደግሞም "ዝሙት ፈፀመች" ተብሎ መጠራጠርን ምን አመጣው !? (ዜና ማርያም ገጽ 40፣2010ዓ.ም መዝገቡ ስብሃት ) 


ስለዚህም ምክንያት “የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥”— 2ኛ ቆሮ 10፥5 

........

3.የጥበብ ሰዎችና ስግደታቸው 

"እነዚህ ሰበአ ሰገል እና እረኞች ወደ ዋሻ ገብተው አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ በጸናች ክብርት እመቤታችን ፊት ሰገዱ"(ት.ዘጉባኤ.ማ፣ተ.ማ 1989፣ገጽ 40) 


ተአምሬ ማርያም " እመቤታችን ፊት ሰገዱ"የሚለው ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም ።አውዱ ስግደቱን የተቀበለችው ማርያም እና ማርያም ብቻ መሆኗን ያሳያል ።እንዲህ ያደረገው ቃሉን ለመሸምጠጥ ነው።


መጽሐፍ ስናገር ፦“ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት።”— ማቴዎስ 2፥11፣ 

☝ ማርያምን ብቻ ሳይሆን ሕፃኑን ጭምር አዩ ፣

☝በማርያም ፊት ማለትም ለማርያምም ሳይሆን የሰገዱት ለሕፃኑ ብቻና ብቻ ነው ፣

☝መጽሐፍ ቅዱስ እናቱን ከልጇ ጋር ማየታቸውን መዝገቦ ፣ መስገዳቸውን ግን ለሕፃኑ ብቻ አደረገ ፦ "ሰገዱለት" በማለት ነጥለው ስግደቱን ለሕፃኑ ብቻ አደረገ፣

☝ደግሞም "አቀረቡለት" በማለትም ለሕፃኑ ብቻና ብቻ እንደቀረበ አስገነዘበን ።(ወ.አንድምታ ማቴ 2፥11-12 "ሰገዱለት" " አቀረቡለት" ይለናል ራሱ )


ሌላው ነገር ደግሞ ሰበአ ሰገል ጋር እረኞች አንድላይ መጥተው መስገዳቸውን መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም   “ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ።”— ሉቃስ 2፥16


ስለዚህም ምክንያት “የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥” — 2ኛ ቆሮ 10፥5  

......

4.አብርሃም ወደ ከነዓን ለምን ወጣ !? 

"..ስለ እመቤታችን ስለ ቃል ኪዳኗ አብርሃም ከካራን ወጥቶ ወደ ርስቱ ወደ ከነዓን ገባ ከመከራውም ሁሉ ዳነ" (ድ.ኪ.ምህረት 2010 ዓ.ም ጢ.አባይ.ማ ባ.ዳር) 


መጽሐፍ የሚለው ግን ዘፍጥረት 12 ¹ እግዚአብሔርም አብራምን አለው፦ ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ።² ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፤³ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ።⁴ አብራምም እግዚአብሔር እንደ ነገረው ሄደ፤ ሎጥም ከእርሱ ጋር ሄደ፤ አብራምም ከካራን በወጣ ጊዜ የሰባ አምስት ዓመት ሰው ነበረ።⁵ አብራምም ሚስቱን ሦራንና የወንድሙን ልጅ ሎጥን፥ ያገኙትን ከብት ሁሉና በካራን ያገኙአቸውን ሰዎች ይዞ ወደ ከነዓን ምድር ለመሄድ ወጣ፤ ወደ ከነዓንም ምድር ገቡ።


ስለዚህ ድርሳን ኪዳነ ምህረት የሚለው ትርክት ውሸት ነው።ምክንያቱም ፦

☝አንደኛ የመጽሐፉ እውነት የሚለው አብርሃም ቃል ኪዳን የገባው ከእግዚአብሔር ጋር እንጂ ከማርያም ጋር አይደለም ፣

☝ሁለተኛ ማርያም በዚያ ዘመን ልትኖር እና ቃል ኪዳን ማስገባት አትችልም፣ 


ስለዚህም ምክንያት “የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥”— 2ኛ ቆሮ 10፥5 ።

.....

5.ሎጥን ያዳነው ማን ነው !? 

"እግዚአብሔር ታላላቅ የሰዶም አገሮችን በገለባበጣቸው ጊዜ ሎጥ ከዲንና ከእሳት ዝናብ ባንቺ ዳነ" (እንዚራ ስብሐት ፣ዘሰኑይ፣መዝገቡ ስብሐት 2007፣ገጽ 81) 


መጽሐፍ ቅዱስ ግን “እግዚአብሔርም እነዚያን የአገር ከተሞች ባጠፋ ጊዜ አብርሃምን አሰበው፤ ሎጥ ተቀምጦበት የነበረውንም ከተማ ባጠፋ ጊዜ ከዚያ ጥፋት መካከል ሎጥን አወጣው።”ዘፍ 19፥29 

እግዚአብሔር አብርሃምንም ዝም ብሎ አላሰበውም ፤አብርሃም ስለ ሎጥ አብዝቶ ለምኖ ነበርና ዘፍ 18፥22-33። 


እንደውም እኮ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ፣ፈቃድ አብርሃምን በማሰቡ ፦"ሎጥን ረድቷል" ብባል ነው እውነቱ እንጂ ማርያምን በማሰቡ አይደለም።እንደው  ሁለቱ መላእክት በእግዚአብሔር ትዕዛዝረድቷል ብባል እሙንነት አለው።ምክንያቱም ሎጥ ቶሎ መውጣት ባለመቻሉ ራሳቸው መላእክት አቻኩሎት ወስደው ነበር።ዘፍጥረት 19 ¹⁵ ጎህም በቀደደ ጊዜ መላእክት ሎጥን፦ ተነሣ፥ ሚስትህንና ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ውሰድ በከተማይቱ ኃጢአት እንዳትጠፋ እያሉ ያስቸኵሉት ነበር።¹⁶ እርሱም በዘገየ ጊዜ እግዚአብሔር ስላዘነለት እነዚያ ሰዎች የእርሱን እጅ የሚስቱንም እጅ የሁለቱን የሴቶች ልጆቹንም እጅ ይዘው አወጡትና በከተማይቱ ውጭ አስቀመጡት።¹⁷ ወደ ሜዳም ካወጡአቸው በኋላ እንዲህ አለው፦ ራስህን አድን፤ ወደ ኋላህ አትይ፥ በዚህም ዙሪያ ሁሉ አትቁም እንዳትጠፋም ወደ ተራራው ሸሽተህ አምልጥ።


"በማርያም ዳኑ" የተባለው የኢየሱስን እናት እስከሆነ ድረስ በእርሷ ላይ ማሾፍ ነው፤መሳደብ፣ መዘበት፣መሳለቅ ነው።አትሳደቡ!።እሷ በዚያ ጊዜ አልነበረችም ።እንደው ''እንወዳለን" በማለት ያላደረገችውን 'አድርጋለች' ብሎ መዋሸት መሳለቅ እና ንቀት ነው።ፍትህ ለኢየሱስ እናት ለብፅዕት ድንግል ማርያም ።ይህ እኮ የሚያሳፍር ነው፤የደብተራ ተንኮል ነው ።ንቃ እንጂ!።


ስለዚህም ምክንያት “የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥”— 2ኛ ቆሮ 10፥5 ።

....

6.መላእክትን የሚያዘው ማን ነው !? 

"በጸሎቱ ኃይል ዘወትር ይጠብቀን ዘንድ እመቤታችን ሆይ ቸር መልአክሽን ፋኑኤልን ላኪልን (ዝክረ ቃል ፣መ.አ.ሄኖክ ፣አርቲስቲክ ማ.ድ ገጽ 86፤እንደሁም የተለያየ "መልከአ መጽሐፍ" ይህንን ይተባበራሉ ) 


ግን መጽሐፍ ስናገር “በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤”— መዝ 91፥11።መጽሐፍ መላእክት የእግዚአብሔር ተላላኪዎች መሆናቸውን እንጂ በሰው ትዕዛዝ እንደሚቀሳቀሱ አይነግረንም ።አሁን ይህ መላእክትን ማክበር ነው ወይንስ ንቀት!? ።


አሁን በራሳቸው በግል ቤተክርስቲያንያቸው መላእክትን "አዛለው፣የኛ ታዛዥ ናቸው" የሚሉም አሉ።ግን በእውነትም ሰው መላእክትን የማዘዝ ስልጣን የለውም።መላእክት ብገለጡ በፍራት የሚንወድቅ ድኩማን ፉጡሮች ነን እንጂ የመላእክት አዛዦች አይደለንም ።አትሳቱ።


በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማንም መላእክትን ያዘዘ የለም፤ደግሞም "መላአኬ መላአኬ" ብል የግል የራስ መላአክ ስለመኖሩ መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም፤ እንዲያ የሚለው ሚራክል ተካ ነው (Heaven Tv) ሃሰተኛ ነቢይ እንደሆነ እናውቃለን ።እናንተ ግን አትሳቱ።


ስለዚህም ምክንያት “የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥”— 2ኛ ቆሮ 10፥5 ።

......

7.ለክርስቶስ መቃብር ጥበቃ ለምን ተቀጠረለት !?

"ከዚህ በኃላ በዚያ ትጸልይ ዘንድ ሁለተኛ እንዳትደርስ መክረው በልጇ መቃብር ላይ ጠባቆች ሾሙ" (ት.ዘጉባኤ.ማ ፣ተ.ማ ገጽ 44)


መጽሐፍ ስናገር ግን “እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም፦ ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ፥ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት።”ማቴ 27፥64 ።ከዚህ የሚንረዳው ፦

☝ ደቀመዛሙርቱ ይሰርቃሉ የሚል ስጋት ስለነበራቸው መቃብር ላይ ጠባቅዎችን እንደቀጠሩ እንረዳለን፣

☝ ዋና ፍራታቸው መሰረቁ ሳይሆን መነሳቱ ነው።ኢየሱስ "ተነሳ" ከተባለ ያልቅላቸዋል፤ይጋለጣል ውሸታቸው፤ብዙ ሰውም ያምናል ፣

☝ስለዚህ ኢየሱስ በሦስተኛው ቀን እነሳለሁ ማለቱን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ስለ መነሳቱ ሰግተዋል “ጌታ ሆይ፥ ያ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ፦ ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን።”ማቴ 27፥63፤ አሉ ፣

☝ ጠባቂዎች የተቀጠሩት "ኢየሱስ ይነሳል" የሚል ሥጋት ስለነበራቸው ነው።እንዲያ ባይሆን መቃቡሩ ባዶ ከሆነ በኃላ ፦ "እንደ ፈሩት ደቀመዛሙርቱ ሰርቀዋል ብለው ደቀመዛሙርቱን ያሳድዱ ነበር" ግን ኢየሱስ እንዳለው ስለተነሳ "ሰርቀዋል" የሚል ውሸት ፈጠሩ ።


በእርግጥ እናቱ ወደ መቃብር ሄዳለች የሄደችው ግን ብቻዋን አይደለችም ።ምናልባት ሄዳ ብሆን ብባል የሚትሄደው አርብ ከተሰቀለ ማታ ደግሞ ሰንበት ስለሆነ በሰንበት (በቅዳሜ) አልሄደችም፤እሁድስ ሄዳ ብትሆን ብባል እንኳን በጧቱ ነው ከሌሎች ሰቶች ጋር የሄደችው “በሰንበትም መጨረሻ መጀመሪያው ቀን ሲነጋ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ።”— ማቴዎስ 28፥1።


እናም አይደለም መጸለይ ብቻዋም አልሄደችም ፣ ስትሄድም ከሌሎች ሴቶች ጋር ነው የሄደችው ፤ከሄደችም በኃላ መቃብሩ ባዶ ነው።ስለዚህም ትርክቱ  የደብተራ ተንኮል ነው።ውሸት ነው።


ስለዚህም ምክንያት “የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥”— 2ኛ ቆሮ 10፥5 ።

....

8.ሰዎች ሁሉ ማንን ይለምናሉ !? 

"ሰዎች ሁሉ ወደ ወደ አንቺ ይማልዳሉ ፣ይለምናሉ ፣ያንጋጥጣሉ" (ነ.ማርያም  ፣ገጽ 29፣ተስፋ.ማ.ቤት 1991ዓ.ም )


መጽሐፍ ስናገር ግን ፦ መዝሙር 123 ¹ በሰማይ የምትኖር ሆይ፥ ዓይኖቼን ወደ አንተ አነሣሁ።² እነሆ፥ የባሪያዎች ዓይኖች ወደ ጌታቸው እጅ እንደ ሆኑ፥ የባሪያይቱም ዓይን ወደ እመቤትዋ እጅ እንደ ሆነ፥ እንዲሁ እስኪምረን ድረስ ዓይናችን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ነው። ደግሞም በሌላ ክፍል ፦“..፤ ነገር ግን ዓይኖቻችን ወደ አንተ ናቸው።”— 2 ዜና 20፥12 


ወደ እግዚአብሔር የጮኹት ስመሰክሩ “አቤቱ አምላኬ፥ እየኝ ስማኝም፤ ጠላቴ፦ አሸነፍሁት እንዳይል፥”— መዝሙር 13፥3፣ምክንያቱም የሚሰማ የሚመልስ አምላክ ነው።ኢየሱስ ስያስተምር ወደ አባቱ እንዲንጸልይ እንጂ ወደ እመቤት እንዲንጸልይ እንዲንጋጥጥ አላስተማረም ።ምክንያቱም “ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።”— ዮሐንስ 14፥14 ብሏልና።ይህ ማለት በኢየሱስ ስም ስልጣን እንዲንለምን ነው እንጂ በስሜ ማርያም እንዲንለምን አይደለም።ደግሞም በሌላ ክፍል ሁሉንም በኢየሱስ ስም ስልጣን አድርጉ እንጂ ያለን ማርያም ወይንም ሌላ አካል ጨምሩበት አላለም ።ስሙ በቂ ነው፤ረክቻለሁ።መርካት ይሁንላችሁ ።


ከተናገርን አይቀር እውነቱን ለምን ቆይ "ሁሉም ማርያምን ይለምናሉ" ስባል የብሉይ አባቶች ወይንም የአድስ ኪዳን ሐዋርያት አልለመኗትም፤ይህ እኮ ክህደት ነው፦የማያምን ፣ከንቱ ፣ዲቃላ ፣ሃራጥቃ የሆነ ልብ የፈጠረው የደብተራ ተንኮል እኮ ነው።ንቃ እንጂ ወገን።አትሙቱ።


ስለዚህም ምክንያት “የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥”— 2ኛ ቆሮ 10፥5 ።

...

9.የሐዋርያት ሹመት በማርያም ነውን !? 

"ሐዋርያት ያስሩ ፣ይፈቱ፣ይዘጉ፣ይከፍቱም ዘንድ በአንቺ ሰማያዊ ሥልጣንን ተሰጡ"(እ.ስብሐት ፣መ.ተስፋዬ ሚካኤል ታከለ 2007 ዓ.ም ፣ገጽ 129-)


ይህ ሃራጥቃዊ ስብከት ዓይንን በጨው ያጠበ ፣ ያለምርመራ በግልጽ የሚታወቅ፣የሚታይ፣ሃሳዊ ትምህርት ነው።ቃሉ እንደሚል "ብዙ ሃሰተኛ አስተማሪዎች ይነሳሉ" የተባለው እንደተፈፀመ ልብ ይሏል።ደግሞም ብዙዎችንም አስተዋልና አይገርምም ።ግን ምናልባት ለዘንዶ ያልሰገድ አንድ ከተገኘ ብለን ወትበናል ።ተገናዘቡልኝ።


መጽሐፉ የሚለው ከጅምሩ ብንፈትሸው ፦“ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ፤..”— ማቴዎስ 5፥1።ማቴዎስ እንደመዘገበው ኢየሱስ ማስተማሩን በም.5 ይጀምራል ፤ከዛም አስተምህሮ ጨረሰው በም.7፤በም.8 ከተራራው ወረደ “ከተራራም በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።”— ማቴዎስ 8፥1።


ከተራራ በወረደ ግዜ ወደ መንደሮች ስገባ አንዳንዶቹ ተቀበሉ አንዳንዶቹ ከሃገር እንድወጣ ግድም አሉት “እነሆም፥ ከተማው ሁሉ ኢየሱስን ሊገናኝ ወጣ፥ ባዩትም ጊዜ ከአገራቸው እንዲሄድላቸው ለመኑት።”— ማቴዎስ 8፥34 


በምዕራፍ ዘጠኝ “ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፥የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፥ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ፥ በከተማዎችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር።”ማቴ 9፥35

☝ በሙኩራብ አስተማረ ፣

☝የመንግስት ወንጌል ሰበከ፣

☝የታመሙትን ፈወሰ ፣

☝በተለያየ ከተማ እና በከተማ ውስጥ ባሉት መንደሮች ሳይቀር እየዞረ አስተማረ። ይህንን ስያደርግ ጌታ ቡዙ ነገር ተገናዘበ ፦


“ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፥ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።”— ማቴዎስ 9፥36 ።ኢየሱስ እየዞረ፣እያመሰ፣ስለሚያስተምር ብዙዎችን በመድረሱ፣ያሉበት ሁኔታ አሳዛኝ መሆኑን ተረዳ።ከዚህ በኃላ እንዲህ አለ ፦ 

“በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፦ መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤”ማቴ 9፥37፤አለ፣

☝ልቀበሉ የሚችሉ ብዙዎች አሉ ግን ወንጌሉን የሚነግራቸው ጥቅቶች ናቸው ብሎ ።እልካችሁ ዘንድ ለምኑኝ አለ።“እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት አላቸው።ማቴ 9፥38 


ከዚህ በኃላ ነበር ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሐዋርያትን በራሱ ስልጣን የሾመው ።ተመልከቱ።“አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲያወጡአቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው።”— ማቴዎስ 10፥1

☝እዚህ ጋ በማርያም ተሾሙ የሚል የት አለ!? 

☝አስተውሉ አትሳቱ ለቃሉ ግድ ይበላችሁ ።ኢየሱስ ሰዎች ከፈጠሩት ተቋም ይልቃል ።


ስለዚህም ምክንያት “የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥”— 2ኛ ቆሮ 10፥5 ።

...

ማጠቃለያ 

    እስኪ ራሳችንን እንጠይቅ ? በብሉይ እኮ የእምነት ተቋም አልነበረም ፣ በሐዋርያት ዘመን እንኳ የእምነት ተቋም አልነበረም ።እስኪ አስተውሉ መጀመሪያ ሐዋርያት ስሰብኩ የሌለው ተቋም በፖለቲካ ተጽዕኖ ለሁለት ተከፈ ምዕራብ (ካቶሊክ ) ና ምስራቅ (ኦርቶዶክስ ) ተብለው ።የእምነት ተቋም እንድቋቋም ያደረገው እግዚአብሔር ሳይሆን ሰዎች በራሳቸው ለራሳቸው ፖለቲካ ለማራመድ ስሉ ነው።


የእምነት ተቋም ማቋቋም ብያስፈልግ የመጀመሪያ ክርስቲያኖች ይመስሪቱ ነው።ግን ዓላማቸው ወንጌልን መስበክ ብቻ ስለነበር በመንግሥት እውቅና እየተወሰድ የሚቋቋም ተቋም አልመሰረቱም፤በዚያ ግዜም አልነበረም ።


መጽሐፍ ስናገር አንድት ሃይማኖት ስል እንኳን እኮ አንድት ተቋም የሚለን ይመስለናል።ለዚያውም በፖለቲካ የተቋቋመው ።እናም ወንድሞቼ አሁንም እላለሁ የተኛውም የእምነት ተቋም አባል ስለሆንክ አትድንም።ሰው የሚድነው በኢየሱስ ስራ በማመን ነው።


በኢየሱስ ሥራ ያመነ ሰው ደግሞ ብቻል የተቋሞችን ልዩነት ያጣብባል እንጂ አያሰፋም።ደግሞም ከየትኛውም ነገር በላይ ለእርሱ ለሞተለት ጌታ ለቃሉ ታማኝ እና ታማኝ ሆኖ ፤እንደ ወታደር ለቃሉ ብቻ ይሟገታል እንጂ ለተቋም ብሎ አይኑን በጨው አያጥበውም።


ስለዚህም ራስህን መውደድ አለብክ።ማናቸውም እኮ ከኢየሱስ በላይ ወይም እኩል ልወዱ አይችሉም።እንወዳሃለን ብሉ እንኳን ለጥቅማቸው ነው፤ለጥቅማቸው።አንተ ግን ንቃ።ያንተ ነፍስ በእጅህ ናት።ወደ ጌታ በመምጣት ታደጋት።ወዮታ አለብ። 

ተባረኩ!



ዋቢ መጽሐፍት 

☝ ነገረ ማርያም በመናፍቃን አንደበት መሪጌታ ሙሴ መንበሩ 2012ዓ.ም ፣

☝መጽሐፍተ ኑፋቄ ጥላሁን መኮንን ፣

☝ ውዳሴ ማርያም ፣ መልከአ ማርያም app ፣

☝ተአምሬ ማርያም PDF 















Comments

Popular posts from this blog

"ደብተራ ማን ነው?" ጸረ ደብተራ ንቅናቄ በሊቀ ጠበብት በዶክተር ዘሪሁን ሙላቱ

ካህናት ነን