ነገረ ታቦት

ነገረ ታቦት 

መግቢያ 

1.የቃሉን ትርጉም 

2.እንድሰራ ማን አዘዘ?ለምን ተሰራ?መቼ አዘዘ ?

3.አሰራሩን እና ስለ አሰራሩ የእግዚአብሔር አቋም!

4.ታቦቱ አሁን የት ነው ? 

5. በአድሱ ኪዳን የብሉይ ታቦት አገልግሏልን ?

6.በአድስ ኪዳን አሰራሩ እና አጠቃቀሙ የተነገረለት፣ በአድስ መልክ የሚሰራ ታቦት አለን !?

7. የጌታ እራት የምንካፈልበት እቃ "ታቦት" ነውን !?

8. በአድስ ኪዳን አሰራሩ ለየት ያለ ታቦት አለ የሚሉት ለምን የብሉይን ታቦት ይጠቅሳሉ !?

9.በሰማይ ታቦት አለን !? የተኛው ነው (የብሉይ ነው ወይንስ የአድስ ኪዳን ታቦት ) ምን ማለት ነው በራሱ !? 

10.የመጽሐፍ ቅዱስ ዝምታ ይከበር !

11. ለቃሉ እና ለቃሉ ጌታ ታማኝ እንሁን !

............................................

                መግቢያ 

በዚህ ርዕስ ዙሪያ ለመጻፍ ያነሳሳኝ የከበረውን የእግዚአብሔርን ታቦት ነገር እንደ ቃሉ እንዲንረዳ እና እንድናውቅ ብሎም ለቃሉ ተማኝነትን ለማሳየትና ለቃሉ መሸነፍን ለማበረታታት ነው።

ብዙ ግዜ ብዙ ትምህርቶች ላይ አቋም ይዤ፣ "ተሳስቻለሁ" ብዬ ፣ ከሰው ተምሬ አውቃለሁ ።ቃሉን ሳጠን ፣ ቃሉ ዘምበል ወደ ሚልበት ዘበል ማለትን ተምሬያለሁ ።ለምሳሌ የልሳን ጸጋ የለም የምል አቋም ነበረኝ ፤ትቸዋለሁ ፤ስህተትም ነበር።ይህንን በማድረጌ ተጠቀምኩ እንጂ አልተጎዳሁም ።እንደ ሽንፈት አልቆጥርም፤ቃሉ አሸነፈኝ፤ያስተማሩኝ ይባረኩ።

      ትልቁ ችግር ከስህተት አለመማር እና ልብን እልከኛ ማድረግ ነው፤ሞኝነት ነው።ለማወቅ የሚጥር ሰው፣በልቤ ሰፊነት "ቃሉ ግን ምን ይላል?" ፤ "አንተ የእግዚአብሔር ቃል ተናገር!"፤"እኔ እስተካከላለሁ" ካለ ፣ ሁለም የእውነት መንፈስ ወደ እውነት ሁሉ ይመራዋል እንጂ ከቶ ወድቆ አይቀርም ።

ወዳጆቼ  እኔም ራሴ ባለተራ አድርገ፤ ቆጥሬ፤ኃላፊነት እንደሚሰማው ሰው የበኩሌን ለመወጣት ጥረት አደረኩ፤ "የሚትጠቀሙበት ፣ የሚታተርፉበት ይሁን" ፤አሜን።ስለ ፍደል ስህተት ከወዲሁ ይቅርታ እየጠየኩ መልካም ምንባብ እንድሆንላችሁ ተመኘሁ ።

...........................................

 1. " ታቦት የቃሉ ትርጉም "

እጅግ በጣም የሚንወዳቸው እና የሚናከብራቸው ለትውልድ መልካሙን ሥራ አስቀምጠው የሄዱቱ ደስታ ተክሌ ወልድ ባዘጋጁት በዐድስ አማረኛ መዝገበ ቃላት እንዲህ ብለዋል ፦ 

" ዐሥርቱ ቃሊት የተጻፈባቸው ሁለት ጽላቶች በውስጧ ያሉባት ሣጥን በወርቅ የተለበጠች፤ ጽላት ከእብነ በረድ ታቦቲቱ ከማይነቅዜ እንጨት ነው የተቀረጹት፤ ሁለም የሙሴ ሥራዎች ናቸው፡፡ ጽላት እንደ መጽሐፍ ታቦት እንደ ማኅደር (ኢያሱ 3÷14፡17)"፡፡ 

☝ ጽላት እንደ መጽሐፍ ዥርግ ሰለዳ ሲሆን ፣

☝ ታቦት ደግሞ እንደ ሳጥን ያለ ማህደር ነው። 

ታቦት የሚለውን ቃል በእንግሊዝኛው ark ,coffin,box ማለት ነው።“ዮሴፍም በመቶ አሥር ዓመት ዕድሜው ሞተ፤ በሽቱም አሹት፥ በግብፅ ምድር #በሣጥን ውስጥ አኖሩት።”— ዘፍጥረት 50፥26

 ☝ በዚህ ክፍል ላይ ሣጥን ተብሎ የተቀመጠው የሬሳ ሣጥን ነው ።

የእግዚአብሔር ታቦት ምንም እንኳን በአሰራሩ (ሣጥን በመምሰሉ) እና ተመሳሳይ ቃላት ታቦት የሚባሉ ብኖሩም (መርከብ ፣ ሣጥን ፣ የሬሳ ሣጥን ፣...) ፥ግን  "ታቦት" ለዚያውም "የእግዚአብሔር ታቦት" ስንል ለየት ይላል ።ከላይ ለእነዚያ እቃዎችም መጠሪያነት ሆኗል ለማለት እንጂ የእግዚአብሔርን ታቦት ለመናቅ እና "ናቸው" ለማለት አይደለም ። የእግዚአብሔር ታቦት እና "ታቦት/ark" የሚል መጠሪያ ካላቸው ጋ ተመሳሳይነታቸው በሰው እጅ መሠራቱ ነው፤ልዩነቱ ግን በእግዚአብሔር ታቦት ውስጥ ላይ ጽላት መኖሩ (የእግዚአብሔር ጽፈት ያለበት ጽላት መኖሩ) ፣በእግዚአብሔር ስም መጠራቱ ፣ እግዚአብሔር በዚያም ሆኖ ማነጋገሩ እና ለአሰራሩ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ነው ። 

......................................

2.<<ታቦትን እንድሰራ ማን አዘዘ? ለምን ተሰራ ? መቼ እና የት አዘዘ ? >>

"እንድሰራ ማን አዘዘ ?"

አምላካችን እግዚአብሔር ያዘዘው መቅደስ እንድሰሩ ነው።“በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ።”— ዘጸአት 25፥8 ። እግዚአብሔር መቅደስ እንድሰሩ አዘዘ፤ አንድ መቅደስ "መቅደስ" ለመባል በውስጡ መያዝ ያለባቸውን እቃዎችን እንድሰራ ወረድ ብሎ ትዕዛዝ ሰጠ።“ከግራር እንጨትም ታቦትን ይሥሩ፤ ።”— ዘጸአት 25፥10 ። ከመቅደሱ ውስጥ ልኖር የሚገባውን "ታቦት" እንድሰሩ እግዚአብሔር ራሱ ቃል በቃል አዘዘ ።ስለዚህም ማንም በገዛ ፍላጎት መስራት አይችልም ።

" ለምን ተሰራ ?" 

ይህ ታቦት የተሰራው ፦

☝1ኛው. “በታቦቱም ውስጥ እኔ የምሰጥህን ምስክር ታስቀምጣለህ።”— ዘጸአት 25፥16 ።ጽላቱ እንድቀመጥ ነው፤የሚቀመጠው በታቦቱ ውስጥ ነው።

☝2ኛው.“በዚያም ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛውም ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ።”— ዘጸአት 25፥22 ። እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር ለመገናኘት እና ለሕዝብ መልእክት ለማስተላለፍ ነው ታቦት የተሰራው። 

"መቼ እና የት አዘዘ ?"

ሙሴን እግዚአብሔር ታቦት እንድሰራ ያዘዘው፣በሲና ተራራ ላይ አውጥቶ በ40 ቀን ጾሙና ጸሎት ግዜ ነበር፤ ብቻውን እያናገረው ነበር ያሳየው ።ይህንን ሊቃውንት ስያመሳጥሩ "ሙሴ ሕግ ይዞ መጣ ፣ ኢየሱስን ግን ጸጋና እውነት ይዞልን መጣ" እንዳሉ፤ሙሴም በዚህ ግዜ ነበር ታቦት እንዲሰራ የታዘዘው ።

መጽሐፍ ስገልጽ “በተራራ ላይ እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንድትሠራ ተጠንቀቅ።”— ዘጸአት 25፥40 ።በተራራ ላይ በጾም ፣ በጸሎት በነበረበት ግዜ እንደታዘዘ እንረዳለን ። 

....................................... 

3.<< የታቦት አሰራሩ እና ስለ አሰራሩ የእግዚአብሔር አቋም! >>

" አሰራሩ "

እግዚአብሔር "ታቦት ይሥሩ" ብሎ ፣ ብቻ አልተወም ፤ ""እንደ ሬሳ ሳጥን ፣እንደ ልብስ ሳጥን ወይንም እንደ መቃብር የማይንቀሳቀስ ወይንም እንደ መርከብ ... ይሁን የሚሰራው !?"" አይደለም ፤ እግዚአብሔር እንዴት መሰራት እንዳለበት ጭምርም ነው ለሙሴ የነገረው ።ተመልከቱ ፦

“ከግራር እንጨትም ታቦትን ይሥሩ፤ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን።” — ዘጸአት 25፥10

☝ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተክል ነው።እንግዲህ ክንድ የድሮ ሰዎች የርቀት መለክያ ነው።በዚህ መለክያ መሠረት አሁን ወደ ሳይንሱ ብናመጣ "የእጅ ረዥምም አጭርም" ስላለ ፣አማካዩ 2.5 ክንድ =1.75 m ነው።ይህ ርዝመቱ ነው።

☝ ከምድር ከፍታው (ቁመቱ) አንድ ክንድ ተኩል  = .75 m ነው።

☝ ወርዱም ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል= .75 m ነው።

(በራሳችሁ ክንድ መለካት ትችላላችሁ)

☝በነገራችን ላይ ታቦቱ የሚሰራው ከግራር እንጨት ብቻ ነው፤ሌላ ውድም እርካሽም ነገር (እንጨት) መጠቀም አይቻልም፤ከግራር እንጨት ይሠራል። 

....

“በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው፤ በእርሱም ላይ በዙሪያው የወርቅ አክሊል አድርግለት።”— ዘጸአት 25፥11

☝ እንግዲህ እንደ ሣጥን የተሰራው "ታቦት" ውስጠኛ ክፍል አለው፤ውጨኛው ክፍልም አለው።ማለትም እንደ ሰሌዳ ያለ ( ለጥ ያለ ) ሳይሆን ሣጥን ይመስላል ማለት ነው።

☝ ግራር እንጨቱም በንፁህ ወርቅ ይለበጣል።

☝ እንድ ንጉስ ቆብ ወርቁን በታቦቱ ዙሪያው ጉቡ ጉቡ ይደረጋል፤እንደ አኪሊል ።

....

“አራት የወርቅ ቀለበቶችም አድርግለት፥ እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኑር፤ በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላው ወገን ሁለት ቀለበቶች ይሁኑ።”— ዘጸአት 25፥12

☝ ታቦቱ አራት አንግል ያለው ነው።በአንዱ ወገን በኩል ሁለቱ ቀለበቶች ይሰራሉ ፣

☝ የሚሰራው በእግሩ በእታቸኛው ክፍል ነው።

☝ የሚሰራውም በንፁህ ወርቅ ነው ።

.....

“መሎጊያዎችንም ከግራር እንጨት ሥራ፥ በወርቅም ለብጣቸው።”— ዘጸአት 25፥13

☝ ረዘም ያለ ፣ ልክ ከታቦቱ ርዝመት የሚበልጥ ተደርጎ ፣ የግራር እንጨት ይዘጋጃል ፣

☝እንጨቱም በወርቅ ይለበጣል፣

....

“ለታቦቱ መሸከሚያ በታቦቱ ጐን ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አግባ።”— ዘጸአት 25፥14

☝የእግር ቀለበት የተሰራው ፦ከግራር እንጨት የተሰራው Pole (ቀጥ ያለው እንጭት) እንዲገባ ነው።

☝ ቀጥ ያለው እንጨት የተሰራው ታቦቱን ለመሸከም ነው።

☝ ስለዚህ ሁለት ረዥም እንጨት ይሰራል ፤ይህንን እንጨት ተጠቅሞ ልክ እንደ ገጠሩ የሀገረ ሰው ፣ የታመመውን ወደ ጤና ኬላ እንደሚወስዱ ይሸከማሉ ማለት ነው። 

☝ታቦቱን የሚሸከሙት በትከሻቸው ነው፤እንጂ በራስ ላይ አይደለም።“ሙሴም እንዳዘዘው እንደ እግዚአብሔር ቃል የሌዋውያን ልጆች የእግዚአብሔርን ታቦት #በትከሻቸው ላይ በመሎጊያዎቹ ተሸከሙ።” — 1 ዜና 15፥15፤ እንዳለው ነው።

.....

“መሎጊያዎቹም በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ይኑሩ፥ ከቶም አይውጡ።”— ዘጸአት 25፥15

☝ ታቦቱን ለመሸከም የገባው መሎጊያ ከቶም የማይወጣ ነው።ማውጣት አለመታዘዝ ነው፤ትዕዛዝ ስለሆነ።

....

“በታቦቱም ውስጥ እኔ የምሰጥህን ምስክር ታስቀምጣለህ።”— ዘጸአት 25፥16

☝ እግዚአብሔር ራሱ አዘጋጅቶ ፣ጠርቦ የሚሰጠውን ምስክር (ጽላት) በታቦቱ (በሣጥኑ) ውስጥ ይቀመጣል ።ስለዚህም በውስጡ ሁለት የድንጋይ ጽላት ይቀመጣል፤ካልተቀመጠ እግዚአብሔርን መናቅ ነው።

...................................... 

የታቦቱ አሰራር (የቀጠለ)

“ከጥሩ ወርቅም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሥራ።” ዘጸአት 25፥17

☝ ለተሰራው ታቦት(ሣጥን) መክደኛ ይሰራል፣

☝ መክደኛው ከጥሩ ወርቅ ብቻ ይሰራል፣

☝ርዝመቱ 1.75 m ሲሆን 

☝ስፋቱ 0.75 m ነው።

☝ይህም በወርቅ ብቻ ይሰራል፤ ቃሉ ስለሚል ይሆናል። ብፁዕ ወቅዱስ አብነ በርናባስ አሰራሩ ከባድ እና የማይቻል መሆኑን ስገልጽ "አይደለም ኢትዮጵያ ደ.አፍሪቃ እንኳ ይህንን ያክል ወርቅ የላትም "ብሏል፤አሁንም የላትም ፣ ታቦቱንም ራሱ እያለ እንደሆነ ያስተውሏል።

“ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ፥ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ።”— ዘጸአት 25፥18 ፤19 ።

☝  "ኪሩቤል ሥራ " መላእክት የሚመስል እና ክንፍ ያለው ነው፣

☝ የሚሰራው ከወርቅ ብቻ ነው ፣

☝ በታቦቱ መክደኛው ላይ ይሰራል ፣

☝ የሚሰራው ሁለት ኪሩቤል ነው ፣

☝ በአንደኛው ማዕዘን እና በሌላኛው።

“ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ይዘረጋሉ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፥ ፊታቸውም እርስ በርሱ ይተያያል፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ስርየት መክደኛው ይመለከታሉ።”— ዘጸአት 25፥20

☝ኪሩቤል ክንፎቻቸውን ከወገባቸው ወደላይ ይዘረጋሉ ፣

☝ የስሪዬት መክደኛውን ክንፋቸው ይሸፍናል (የመክደኛው መጠን ያውቁዋል፤ክንፋቸው ይሰፋል ማለት ነው)

☝ሁለት ኪሩቤል ፊት ለፊት ይተያያሉ ፣

☝ዓይናቸውን ግን የታቦቱን መክደኛውን ብቻ ይመለከታል ።

“የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ ታደርገዋለህ፤ እኔም የምሰጥህን ምስክር በታቦቱ ውስጥ ታኖረዋለህ።”— ዘጸአት 25፥21

☝ ጽላቱን ታቦቱ ውስጥ በማስገባት ፣በመክደኛው (ኪሩቤል ተሰሪቶ እየለ ) ይደከናል ፣

“በዚያም ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛውም ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ።” ዘጸአት 25፥22

☝ ጌታ ተስሪቶ ስያልቅ በተሰራው ታቦት እንደሚነጋገር ገለጸ ፣ ለሕዝቡም መልእክት እንደሚሰጥ አስታወቀ።

 ☝በወርቅ ለእግዚአብሔር የተሰራው ታቦቱ ብቻ ሳይሆን ገበታ፣መቅረዝ.. ጭምር ነው።

“በተራራ ላይ እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንድትሠራ ተጠንቀቅ።”ዘጸአት 25፥40

☝ እግዚአብሔር እርሱ እውነት እና በምክንያት የምሰራ አምላክ ነው።እያንዳንዷን ነገር በኀጢአት የወደቀውን የሰውን ልጅ ፊት ለፊት ያወራው ዓላማ ስላለው ነው።ደግሞም  "ተጠንቀቅ " በማለት እያንዳንዷን ነገር በተጠንቀቅ እንድሰራ ያስጠነቅቃል ።

☝ ይህንን በመናቅ ወይንም ባለማወቅም(ምናልባት ) ወይንም በቸልተኝነት እንደ ፈለጉ ቀርጸው " ታቦት " ነው ብሉ እግዚአብሔርን መካዳቸው እና መስደባቸው ነው።

☝ እግዚአብሔር አይዘበትበትም!

☝ አዎ "ታቦት ነው" ስትል ያውም "የእግዚአብሔር ቃል ክዳኑ ታቦት ነው" ስትል "ዋ" ፣

☝ ተጠንቀቅ ! ሌሎች ካልተጠነቀቁ ግን አንተ ተጠንቀቅ! ለራስህ! ፤ አዎ የእግዚአብሔር ቁጣ አሁን ያስታገሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው፤ስመጣ ወዮውልሽ።

*"ተጠንቀቅ እንዳሳየው ሥራ" ከማለቱ ወጩ ታቦቱን እንዲያባዛ አልነገረውም። "ሙሴ ሰብሮ እንደገና አልሰራም ወይ" ይላሉ ፣ ግን ሙሴ ታቦቱን አልሰበረውም፤ጽላቱን ነው የሰበረው።

☝ጽላቱ “ጽላቶቹም የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፤ ጽሕፈቱም በጽላቶች ላይ የተቀረጸባቸው የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበረ።” — ዘጸአት 32፥16 ።የጸሐፈው እና የቀረጸው እርሱ እግዚአብሔር ብቻ ነበር።

☝ግን ሙሴ ጽላቱን ሰባበረው  “እንዲህም ሆነ፤ ወደ ሰፈሩ ሲቀርብ ጥጃውንም ዘፈኑንም አየ፤ የሙሴም ቍጣ ተቃጠለ፥ ጽላቶቹንም ከእጁ ጥሎ ከተራራው በታች #ሰበራቸው።”— ዘጸአት 32፥19።አዎ ሙሴ ጽላቶቹን ነው የሰበረው እንጂ ታቦቱን አይደለም ።

☝ሙሴ ጽላቶቹን ሰበረ፤እግዚአብሔር ድንጋዩን ጥረብ አለው ፤ግን ጹሑፉን ጻሐፍ አላለውም።ስለዚህም ሁለተኛ ለሚሰራው ጽላት ቀራጩ ሙሴ ሲሆን ጻሐፍው እግዚአብሔር ነው።“እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች እንደ ፊተኞች አድርገህ #ጥረብ፤ በሰበርኻቸው በፊተኞቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃሎች #እጽፍባቸዋለሁ።”— ዘጸአት 34፥1፤ ዘዳ 10 ።

      ስለዚህም ወዳጆቼ ሙሴ ጽላቱን ብሰብርም እስከ ዛሬ ድረስ "ጽላት ሰራለሁ" ብሎ ፣ የተነሳ እስራኤላዊ የለም ፤ሙሴም በድጋሚ አልሰራም፤ማንም "ሰራለሁ" ብል ፣ ጽሑፍን ማን ይጽፍበታል !? እግዚአብሔርን ካልናቀ በስተቀር።እያስተዋላችሁ እግዚአብሔር ራሱ ብቻ ነው መጽሐፍ የሚችለው፤አላስጻፈውም፤ "እንድጽፍም ፈቃድም ሰቶኛል" የሚል እንደ እግዚአብሔር ቃል ማስረጃ ያምጣ፤እንደሌለም እወቁም።

*በታቦቱ አሰራር ላይ ብዙ ነገር የተገናዘባችሁ ይመስለኛል ።በታቦቱ ላይ የማንም ስም አልተጻፈበት፤ሌላ ምስልም እንዳልተቀመጠበትም ልብ ይሏል! ። እግዚአብሔር ስም መጻፍ እና መሣል ብያስፈልግ አይረሳውም ነበር።ስለዚህም ከወዲሁ ልብ እያላችሁ።"ተጠንቅቀ ሥራ" የሚለው ቃል የታመነ ነው።

...............................................

4. "ታቦቱ አሁን የት ነው ? "

የአንዳንድ ሰዎች ምልከታ ፦

*"ታቦቱ ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል" ስሉ ፤ "እንዴት መጣ ?" ለሚለው ጥያቄ የተለያየ ሀሳብ ያስቀምጡታል።እንደሚከተለው ቀርቧል፦ 

☝ በምኒልክ በኩል መጣ  ፤ ምንጭ  [ስርግው ገሊው፣ ክብረ ነገሥት - ግእዜና ዓማርኛ (2005 - ሁለተኛ ዕትም) ገጽ 157-158።]

* የሊቀ ካህናቱ ልጅ በአዚርያስ በኩል ተሰርቆ ወጣ ከቤተመቅደስ ፤ ምንጭ  [ሰልሞን ዮሐንስ (ዲያቆን)፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወርቃማ ዘመናት (መጋቢት 27/2001) ገጽ 55-57።]

* ይህ ሀሳብ በየትኛውም መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የማይሆን ነው ፣አይደለም ታቦቱን መስረቅ ፣ በባዶ እጅ መግባት ፣ ለዚያውም ልቀ ካህናት ያልሆነው፤ደም ያልያዘው ፤መያዝም የማይችለው ቀርቶ ፥  ልቀ ካህናቱ  ደም የያዘው እንኳን በዓመት አንደ ነው የሚገባው፤በማስተሰሪያ ቀን ብቻ።“ይህም አንድ ጊዜ በዓመት ለእስራኤል ልጆች ስለ ኃጢአታቸው ሁሉ ያስተስርይ ዘንድ የዘላለም ሥርዓት ይሁንላችሁ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ አደረገ።” ዘሌዋውያን 16፥34

☝ "አትናዎቴዎስ ለአባ ፍሬምናጦስ ሰጥቶት ነው " ምንጭ አሳታሚው ያልተገለጸ፣ ገድለ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን (1998) ገጽ 11 ።

*በዚህ መሠረት ካየን ታቦቱ መጀመሪያ በአባ አትናዎቴስ እጅ ነው ማለት ነው፤እሱ "መቼ እና ከማን ተቀበለ !?" መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው።

☝"ፍሬምናጦስ አመጣ ?" ፣ "ምንልክ አመጣ?" እሺ ማን አመጣ !? ተረት ነው ፤ እወቁም። 

☝ ሌላው ደግሞ "ከሁለቱ ጽላቶቹ በዕጣ ሰለሞንና ምኒልክ ተከፋፍለው ፣አንዱን ለኢትዮጽያ አንዱን ለእስራኤል ወሰዱ" የሚል ነው።ምንጭ አያላው ታምሩ (አለቃ)፣ የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት (2003 - ሁለተኛ ዕትም) ገጽ 58።

* በዚህ ገለጻ መሠረት ከላይ ያለው ሀሳብ ውድቅ የሚደርግ ነው።ምክንያቱም አንዷን ጽሌ ብቻ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣች ይነግረናል ፤ታቦቱ እና አንደኛው ጽሌ እስራኤል እንደቀረች ። አሁን እያስተዋላችሁ ማን ወሬ እየፈጠረ እንደሚያስተምር።

ይህ እውነታ የሌለው የአሮግቶች ተረት ያመጣው አስተምህሮውን ወንድም ተዎድሮስ ደመላሽ በዕንተ ታቦት ፤ገጽ 60 ፤ላይ ስገልጽ እንዲህ ብሏል ፦"" .የቃል ኪዲኑ ታቦት ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል የሚለው ክብረ ነገሥት ወደ ቤተ ክርስቲያን ያስገባው ይህ እንግዳ ትምህርት፣አኹን ላይ በስም ብቻ 'ታቦት' የሚለውን ይዘው በአገሌግልትም ኾነ በይዘት ታቦት ያልኾኑትን ሰሌዳዎች  ወደ ቤተ ክርስቲያን

ለማስገባት ምክንያት ኾኗል። ይህን ሀሳብ የሚያቀነቅኑት ክፍሎች “ከክርስትና በፊት የብለይ ኪዲን ሀገር የነበረችው

ኢትዮጵያ በክርስትናም ጊዛ ታቦትን በክርስትና መንፈስ

ትጠቀምበታለች "" ማስባሉን ገለፀ።

ደግሞም እንደ እግዚአብሔር ቃል እንያ፦ሙሴ የጠረበው ጽላት ፣ የእግዚአብሔር የእጁ ጽሕፈት ያለበት ጽላት ፣ ከግራር እንጨት የተሰራውና በወርቅ የተለበጠው ታቦት አሁን የት ነው !? 

☝ ምንም እንኳ ከተረቱ አንዱ ""በሰለሞን ዘመን ተሰርቆ ወይንም በስምምነት(ተከፋፍሎ) ይሁን ፣ እንደ መጣ ባይታወቅም፥እንዲያ ብነግረንም ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከሰለሞን ሞት በኃላም ታቦት በእስራኤል መኖሩን ይነግረናል ።“እስራኤልንም ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩት፥ ለእግዚአብሔርም ለተቀደሱት ሌዋውያን እንዲህ አለ፦ ቅዱሱን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤት ውስጥ አኑሩት፤ ከዚህም በኋላ በትከሻችሁ ላይ ሸክም አይሆንባችሁም፤ አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ፤”— 2 ዜና 35፥3 

☝ እስራኤላውያን እንደ ቃሉ ባለመገኘታቸው እግዚአብሔር ለባቢሎን ምርኮ አሳልፎ ሰጣቸው ።በዚህ ወረራ ላይ ቤተመቅደስ ተዘረፈች።

☝ ቤተመቅደስ ተቃጠለች ሁሉንም ዘረፉ ፤

2ኛ ነገሥት 25

¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯

⁸ በባቢሎንም ንጉሥ በናቡከደነፆር በአሥራ ዘጠኝኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ባሪያ የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።

⁹ የእግዚአብሔርንም ቤትና የንጉሡን ቤት አቃጠለ፤ የኢየሩሳሌምንም ቤቶች ሁሉ፥ ታላላቆቹን ቤቶች ሁሉ፥ በእሳት አቃጠለ።

 …  

¹³ ከለዳውያንም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የነበሩትን የናስ ዓምዶች፥ በእግዚአብሔርም ቤት የነበሩትን መቀመጫዎችና የናስ ኵሬ ሰባበሩ፥ ናሱንም ወደ ባቢሎን ወሰዱ።

¹⁴ ምንቸቶቹንና መጫሪያዎቹንም መኰስተሪያዎቹንና ጭልፋዎቹንም የሚያገለግሉበትንም የናስ ዕቃ ሁሉ ወሰዱ።

¹⁵ የዘበኞቹም አለቃ ማንደጃዎቹንና መቀመጨዎቹን፥ #የወርቁን_ዕቃ_ሁሉ_በወርቅ፥ የብሩንም በብር አድርጎ ወሰደ።

¹⁶ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ቤት የሠራቸውን ሁለቱን ዓምዶች አንዱንም ኵሬ መቀመጫዎቹንም ወሰደ፤ ለእነዚህ ዕቃዎች ሁሉ ናስ ሚዛን አልነበረውም።

¹⁷ የአንዱም ዓምድ ቁመት አሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፥ የናስም ጕልላት ነበረበት፤ የጕልላቱም ርዝመት ሦስት ክንድ ነበረ፥ በጕልላቱም ላይ በዙሪያው የናስ መርበብና ሮማኖች ነበሩ፤ እንዲሁም ደግሞ በሁለተኛው ዓምድ ላይ መርበብ ነበረበት።

☝ከዚህ ምርኮ በኃላ እግዚአብሔር " እመልሳቸዋለሁ ፣ትበዛላችሁ ፣ አንድ አደርጋለሁ "የሚል መልእክት ስያስተላልፍ በዚያውም ከተመለሱ በኃላ በቁጥር ከበዙም በኃላ ፣ የእግዚአብሔርን ታቦቱን እንደሚረሱ ይገልጻል ። “በበዛችሁም ጊዜ በምድርም ላይ በረባችሁ ጊዜ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚያ ዘመን፦ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ብለው ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሩም ልብ አያደርጉትም፥ አያስቡትምም፥ አይሹትምም፥ ከእንግዲህ ወዲህም አይደረግም።” — ኤርምያስ 3፥16 

☝ አዎን ቃሉም እንደምል ረሱ፤ አሁንም አይፈልጉም።ግን አሁንም ታቦቱ የት ነው !? 

☝ ከምርኮ ስመለሱ እስራኤላውያን የተዘረፉትን እቃዎችን መልሰዋል  ፣ግን ከነዛ መኃል ታቦት አልተጠቀሰም ።

ዕዝራ 1

¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯

⁷ ንጉሡ ቂሮስም ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በአማልክቱ ቤት ያኖራቸውን የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች አወጣ።

⁸ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስም በመዝገቡ ላይ በነበረው በሚትሪዳጡ እጅ አወጣቸው፥ ለይሁዳም መስፍን ለሰሳብሳር ቈጠራቸው።

⁹ ቍጥራቸውም ይህ ነው፤ ሠላሳ የወርቅ አንድ ሺህም የብር ሰሐኖች፥ ሀያ ዘጠኝም ቢላዎች፥

¹⁰ ሠላሳ የወርቅ ደካዎች፥ አራት መቶ አሥርም ሌላ ዓይነት የብር ደካዎች፥ አንድ ሺህም ሌላ ዕቃ ነበረ።

¹¹ የወርቁና የብሩ ዕቃዎች ሁሉ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ፤ እነዚህንም ሁሉ ሰሳብሳር ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱ ምርኮኞቹ ጋር ወሰደ።

☝በባቢሎን ምርኮ ቃል በቃል ታቦቱን ወሰዱ ባይልም በ2ነገ በቁ.15 ወርቁን ሁሉን እንደወሰዱ ያስገነዝባል ።ታቦቱም ወርቅ ስለሆነ ተዘርፏል ማለት ያስችላል ።

☝ከምርኮ ስመለሱ ደግሞ ታቦት ስለመመለሱ አይነግረንም ፤ እስራኤላውያን ቃሉ እንደሚል ፍጹም ረስተውታልና፤ትንብቱም ተፈጽሟል ።

☝አሁን ታቦቱ እዛው በባቢሎን ይሁን አይሁን የምናውቀው ነገር የለም።ምናልባት ታርክ ከተደፈነም፤ከቀለጠም፤ከተማረከም በሌላ ሀገር፤ወይንም ከተሰረቀም፤አውጥቶ አሳይቶ ያሳምን ይሆናል፤ያወጣው ይሆናል፤አስካሁን ግን እንዲህ ነው የሚል ፍንጭ እንደሌለ ልብ ይሏል።መጽሐፉ በዚህ ይዘጋል ስለ ታቦት።እንዲህ በዋጋ የሠሩትን ታቦት ፣ የተሰጣቸው እስራኤላውያን ረስተዋል፤አዎ ረስተዋል። 

............................................

5. "በአድሱ ኪዳን የብሉይ ታቦት አገልግሏልን ?" 

ትንሽ የሞኝ ጥያቄ ነው፤በሌለ ታቦት።ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት የጀመረው በ30 ዓመቱ ነው፤ስያገለግልም ቅድስተ ቅዱሳንን አልደረሰም፤ የምድር ሊቀ ካህናት አይደለምና።ቃሉ እንደሚል “እርሱም በምኵራባቸው ያስተምር፥ ሁሉም ያመሰግኑት ነበር።”ሉቃስ 4፥15 ።

የኛ ጌታ ! ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ፦ ብሰደብም፣ብገረፍም፣ደሙ በምድር ብፈስም፣ብተፋም፣ብመታም፣ብቸነከርም፤ደሙ በተሰቀለበት እንጨት፣በተገረፈበት ጅራፍ፣በለበሰው ልብስ፣በምስማር፣በመዶሻው ብፈስም፤ከደሙ ፍሰት የተነሳ የአሰቃዮች አይሁዳውያን ልብስ እንኳን ብነካም ፥ ስለእኛ ራሱን ያቀረበው ግን #በሰማይ ነው።

ጌታ ስለእኛ አርጌውን ክዳን አስረጅቶ ፤ አስወግዶ አድስ ክዳን የገባልን በሰማይ ነው፤በሰማይ ነው።በእጅ ባልተሰራች በእውነተኛ መቅደስ ነው።ቃሉ እንደሚል “ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።”— ዕብራውያን 9፥24

የሰማይ መቅድስ ካለ ፤የሊቀ ካህናቱ አገልግትም በዚያ ነው ያለው ።ጌታ በሰማይ መቅደስ ለዚያውም በእጅ ባልተሰራች መቅደስ የሚያገለግል ነው።ስለዚህም ስሪዬቱ ፣ ማስተሰሪያው የሚደረገው በዚህ በሰማይ መቅደስ፦ በኢየሱስ ደም ነው።“ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ #የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤”— ዕብራውያን 8፥1 ።ይገርማል ሊቀ ካህናት አለን ግን የተቀመጠ ሊቀ ካህናት፤ሃሌ ሉያ።

ጌታ እንደ ብሉይ መቅደስ በዓመት አንድ ግዜ እንኳን መግባት አላስፈለገውም፤አንድ ግዜ ገብቶ፤ቆሞ ደሙን አቅርቦ፤ ዳግም መቆም እና ደሙን ማፍሰስ ሳያስፈልግ ይሰራል፤ይታይልናል።“ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤”— ዕብራውያን 9፥25።

ስለዚህም ጌታ በእግዚአብሔር የተመሰከረለትና የረካውን ሥራ በመስራት ፣ በክብር ተቀምጧል።ዳግም መሞት አላስፈለገውም፤  "ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኔ ነው የሞተው ፣ ደሙን ( ራሱን ) ያቀረበው " ብለው የሚያምን ሁሉ ከኀጢአት ነፃ ይሆናል፤ሃሌ ሉያ።

*የኢየሱስ ምሳሌ እንደሆነ ኢየሱስ ራሱ ጠቅሶ ያስረዳው የናሱ እባብ ታርክ እንመልከት ።“ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ፤ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ።”— ዘኍልቁ 21፥9 ፤ እንዲህ ልሞቱ የደረሱ በእባቡ የተነደፉ ፣ እባቡን ሳይሆን የናሱን እባቡ ፣አርትፊሻለሁን በመመልከት ብቻ ከተፈወሱ ፤ ኢየሱስን መመልከት እንዴት አይፈውስም !?ይፈውሳል።በአርተፊሻል እባቡ ከዳኑ፥ በእውነት ሙሉዕ ሰው በሆነው ፣ የእውነትም ባፈሰሰልን ደም እንዴት አይነፁም!? ይነፃሉ ። 

ለማስተሰሪያ የሚሆን የደም መስዋዕት ለማቅረብ ፦ በብሉይም አንድ መቅደስ ብቻ ነው ያለው ፤በአድስም አንድ መቅደስ ብቻና ብቻ ነው ያለው ።ጌታም ለማስተስሪያ የሚሆን የደም መስዋዕት ይዞ የገባልን ፣ ብቸኛው ሊቀ ካህናት ነው። በአንድ መቅደስ አንድ ሊቀ ካህናት ብቻ ነው ያለው ፣ ጌታችን ሰለማይሞት እሱ ብቻ ሊቀ ካህናት ነው፤ይገባናል።

ስለዚህም በእጅ ያልተሰራች አንድት መቅደስ እና አንድ ሊቀ ካህናት አለን።ጌታ የምድር የብሉይ መቅደስ አገልጋይ አይደለም፤የብሉይ መቅደስ አገልግሎቱ አክትሟል።ምክንያቱም "የእኛ ሰው በሰማይ ነው" ሰባኪ ጳውሎስ ፈቃዱ እንዳለው። 

*ስለዚህም አድስ ክዳን የተጀመረው በሰማይ እና በሰማይ ብቻና ብቻ ነው፤በቡሉይ ምድራዊ መቅደስ አላገለገለም ።ሃሌ ሉያ።

..........................................

6.<< በአድስ ኪዳን አሰራሩ እና አጠቃቀሙ የተነገረለት፣ በአድስ መልክ የሚሰራ ታቦት አለን !? >>

እግዚአብሔር አምላክ በብሉይ ኪዳን በሕዝብ መካከል ለማደር ወድዶ መቅደስ ሥርሉኝ አለ።“በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ።”— ዘጸአት 25፥8 

በአድሱ ኪዳን በእኛ መካከል ማደሩን በመቅደሱ ሳይሆን ሰው በመሆኑ አረጋገጠ ፤አማኑኤል፤ "ከእኛ ጋር ሆነ" ቃሉ እንደሚል “እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም፦ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።”— ማቴዎስ 1፥23 ።ይህ የእግዚአብሔር መገኘት ከመቅደሱ መገኘት ይልቃል ።በብሉይ እግዚአብሔር በመካከላቸው የሚያድረው፣መቅዱሱ ባለበት ብቻ ሲሆን በአድስ ክዳን ግን ያለ ቦታ ገደብ ፣ ከእኛ ጋር ባለንበት ሁሉ እንደሚሆን ገለጠ።ስለዚህም ከድንግል የተወለደው አማኑኤል ፦እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የመሆኑ ማረጋገጫ ነው።እንዲያ ባይሆን ለእግዚአብሔር ለመስገድ ወደ እስራኤል ወደ መቅደሱ እንወጣ ነበር።ግን ባለንበት ቦታ ሁሉ ከመካከላችን ስለሆነ ባለንበት ቦታ ሆነን መገናኘት እንችላለን ።አሜን አማኑኤል ስለሆነልን።

ሌላው ደግሞ ይህ መቅደስ በውስጥ "ታቦት"አለው፤ታቦቱ እግዚአብሔር በእርሱ ሆኖ የሚያነጋግርበት ነው። በአድስ ኪዳን ታቦትን ሥሩልኝ አላለም ።ምክንያቱም “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥..።”— ዮሐንስ 1፥14 ።አምላካችን በብሉይ መቅደስ በአድስ ኪዳን አያድርም ፤ በእኛ በሰዎቹ! አደረ እንጂ ።ስለዚህም እኛን ለማነጋገር "ታቦት ይሥርሉኝ" ማለት አላስፈለገውም ፤ እኛን ሆኖ በእኛ አድሯልና።

እስራኤላውያን ሕግም ሥራዓትም የተሰጣቸው ታቦቱን ቃሉ እንደሚል ልብም አይሉትም፤ጌታም እንደገና "ልብ እንድሉ አደርጋለሁ" አላለም፤ወይንም "ሌላ እሰራለሁ ወይንም ሥሩም" አላለም።ከመጀመሪያው በሚልቀው እና በተሻለው ከእኛ ጋር ለመሆን እና ለማነጋገር ወደደ።ስለዚህም እኛን ሆነ፤በእኛ አደረ። ሰማዩ እና ምድር የማይወስኑለት ጌታ በእኛ ፥ በሰው ላይ ለማደር ወደደ።"እንዴትስ ያለ መቅረብ ነው!?" አዎ ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ “ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ።” — ፊልጵስዩስ 4፥6 ያለው ።

በአድሱ ኪዳን "መቅደስንም (በመቅደስ ውስጥ ያሉትን ታቦትን ጭምር ሥርሉኝ)" ያላለው ጌታ ፣ እኛን መቅረብን እንዴትስ ብወድ ነው !? ድንቅ ነው። መቅደስ ፍለጋ ከምትንከራተት ከሀገር ወደ ሀገር ፣ እኔን << መቅረብ፣ ማናገር ፣ ብትወዱ "በስሜ ተሰብሰቡ" >> እንደሚል ፣ እንዲህ አለ ፦ “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።”— ማቴዎስ 18፥20፤አለ።

አሁን እዚህጋ ነው ቁም ነገሩ። "በስሙ ተሰብሰቡ" ብቻ ነው ቃሉ የሚለው ።በስሙ ከተሰበሰቡ የመሰብሰቢያ ማዕከሉ መቅደሱ አይደለም ማለት ነው፤ለዚህም ነው በአድሱ ክዳን "መቅደስ ሥርሉኝ" ያላለው ። በእኛ ላይ የሆነው ጌታ በመካከላችን ሆኖ ያስተምረናል፤ያናግረናል ።

ስለዚህም ሳጠቃልለው "ለአድስ ኪዳን ታቦትን ሥሩልኝ" አላለም ፣ አሰራሩንም አልነገረንም ማለት ነው፤አራት ነጥብ፤የሚሻል ፣ የሚልቅ ፣ መጥቷልና ።

................................................... 

7. << የጌታ እራት የምንካፈልበት እቃ "ታቦት" ነውን !?>>

ምንም እንኳን ከኢየሱስ መፀነስ ጀምሮ አድስ ኪዳን ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ ብመዘገብም ኪዳኑ የጀመረው ግን ጌታ ስወለድ ፣ስጾም ወይንም በምድር እየተመላለሰ ስያስተምር ሳይሆን ራሱን ስለእኛ ስያቀርብ ነው።ይህንን ሐዋርያው ጳውሎስ ስገልጽ “ስለዚህም ፊተኛው ኪዳን እንኳ ያለ ደም አልተመረቀም።”— ዕብራውያን 9፥18፤ ይለናል ። 

"በደም ተመረቀ" ስባል ደሙ እንዲሁ ከሰውነት የፈሰሰውን መንገሩ ሳይሆን መሞቱን የሚናገር ነው። አንድ ሥራ "ተመርቋል" ከተባለ ፣ ለተመረቀበት ዓላማ ክፍት ሆኗል፣አገልግሎት ጀምሯል ማለት ነው።"በክርስቶስ ደም አድስ ክዳን ተመረቀ" ስባልም በኢየሱስ ሞት ደሙ ለተከፈለበት ዓላማ አገልግሎት ጀምሯል ማለት ነው።ታዲያ እንዲህ የአድስ ኪዳን አጀማመሩን ካየነው ፣ ደሙን ወይንም ራሱን ለእኛ ያቀረበው " የት እና በምን እቃ ላይ ነው " የሚለው ማጠን መልካም ነው ፦

ጌታ የዚህ የምድራዊ የብሉይ ሊቀ ካህናት ባለመሆኑ መጠን ፥ በሰማይ ስለእኛ መስዋዕት ይዞ የገባ ነው ።የአድስ ክዳን አገልግሎት የጀመረው በሰማይ ነው።"..በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።”— ዕብራውያን 9፥24 ፤እንደሚል።

ጌታ ወደ ሰማይ ከገባ ፣ ስለእኛ ያፈሰሰውን ራሱን (ደም እና ሥጋውን) በምን ላይ ነው ያቀረበው !? በእጅ ባልተሰራች መቅደስ።ይህች በእጅ ያልተሰራች መቅደስ ሥጋውን እና ደሙን ስለእኛ ያቀረበበት ናት።ታዲያ በእጅ ያልተሰራችውን መቅደስ የሠራው ማን ነው!? “..፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት።”— ዕብራውያን 8፥2 ።

የሠራው ሙሴ አይደለም ! የሠራው ጌታ ራሱ ነው።ታዲያ ሰዎቻችን 'የእኛ ታቦት በሰማይም ላይ አለ' ስሉ ፣ የሙሴ ታቦት ነው  የሚሉት ? ወይንስ ማንም የማያውቃትን በጌታ የተተከለችዋን ነው የሚሉት !? በሰማይ ያለው የራሳቸው መሳይ ዠርግ ሰሌዳው አለ ነው  የሚሉት !? በእርግጥም አዎ! ጌታ ራሱ የሠራትን መቅደስን እናውቃለን እያሉ እንደሆነ ያስተውሏል ።እውነታው ግን ማንም አያውቅም የአድስ ኪዳን የመቅደሷን አሰራሯን፤ሰማያዊቷን።

ጌታ የሰማይ ሊቀ ካህናት ነው(የምድር ሊቀ ካህናት አይደለም) የሚለውን በልባችን ይዘን የሚከተሉትን እናጠን ፦ 

☝“በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ልናሰናዳልህ ትወዳለህ አሉት።”— ማቴዎስ 26፥17 ።እንደ ማነኛውም አይሁዳዊ የፋስካ በዓል ለማክበር ተማሪዎቹ "የት እናከብር" የሚል ጥያቄ ለኢየሱስ አነሱ ፣

☝“እርሱም፦ ወደ ከተማ ከእገሌ ዘንድ ሄዳችሁ፦ መምህር፦ ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ከአንተ ዘንድ ፋሲካን አደርጋለሁ ይላል በሉት አለ።”— ማቴዎስ 26፥18።ጌታ በስም ወዳልተጠቀሰ ግለሰብ ቤት በዓሉን ለማክበር ወደደ፣ጌታ "ግዜ ቀርቧል" የሚል መልእክት መስጠቱ ሰውየው ጌታን የሚያውቅ ሰው ይመስላል ፣

☝ “ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ ፋሲካንም አሰናዱ።”— ማቴዎስ 26፥19 ።በስም ያልተጠቀሰው ግለሰብም ጥሪውን ተቀብሏል ፣

☝ “በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ።”— ማቴዎስ 26፥20 ፤ቅድሞ መልእክት ነግሮ በአመሻሹ ላይ እንደቀጠረውም ጌታ መጣ፣

☝ “ሲበሉም፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል አለ።” — ማቴዎስ 26፥21 ፤ "ስበሉም" እንደ ማነኛውም አይሁዳውያን በዓሉን በሚበሉበት እቃ እና አቀማመጥ እየበሉ እያሉ ጌታ "ተላልፎ እንደሚሰጥ" ተናገረ ፣

☝“እጅግም አዝነው እያንዳንዱ፦ ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር።”— ማቴዎስ 26፥22 ።ተማሪዎቹ ደነገጡ (ራሳቸውን ጠረጠሩ) ፣ 

☝“ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና፦ እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ።”— ማቴዎስ 26፥26 ፤ ጌታ ስለመሸጡ እና በመሸጡ ሰውየውን የሚከተለውን ከነገረ በኃላም ፣ አሁንም እየበሉ እንዳሉ ቃሉ ይነግረናል፤ስበሉም።እንጀራውን ከፍ አደረገ ፣ ባረከም፤ራሱ የባረከውን ቆርሶ ሰጣቸው፤ እንካችሁ ብሉ ፤ሥጋዬ ነውም አለ።

☝ “ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፦ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤”— ማቴዎስ 26፥27 ፤ጽዋ ወይንም ኩባያ በእጁ ይዞ አመሰገነ ፤አመስግኖም ሰጣቸው ፤ጠጡም አለ።

☝“ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።”— ማቴዎስ 26፥28 ፤አለ።

      አስተውሉ!  ጌታ ስለ የሚያፈስልን ደም እና ስለሚያቀርብልን ሥጋ እንጂ " እህሉን " ስለያዘው እቃ አንዳንች ነገር አልተናገረም ፤ጉዳዩ ከእቃው ጋር በፍጹም አይደለምና።ሰዎቻችን "እኛ ታቦት የሚንለው የኢየሱስ ሥጋና ደም ስለምቀርብ ነው" ይላሉ ፣ አሁን አሁን ነው የተጀመረው እንዲያ ማለት(ከእስራኤል እንደመጣም ያስተምሩ ነበር ጌታም እንዲያባዙ እንደነገረ አድርገው )፤ግን ኢየሱስ ማንም አይሁዳዊ ለራሱ ቤት ባዘጋጀው እቃ ነው የተገለገለው ፣ በሌላ ክፍልም “..፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ።” — ሉቃስ 22፥19 ፤ይህንንም ስል ' እቃውን እንድናባዛ እና እንድንሸከመው ወይንም አድራለሁ ወይንም ታቦት ነው ፤ የሚሸከም ሰው ያስፈልጋል' አላለም፤በፍጹም ።

እስኪ አስተውሉ! ጌታ በዓል ያከበረው እቃው/መብያው/ ለየት ይላልን !? ሌላ አገልግሎት የዋለም አይደለምን !?ከዚህ በፊትም የሚበሉት ነው፤ግን ማንም ምንም ብል የመጀመሪያዎቹ የእርሱ ተማሪዎች "የጠጡበትን እቃ" ተሸከሙ !? ፥  "የእግዚአብሔር ታቦት ነው" አሉ ? ፥ ከእኛ ከአሁኖቹ እና ከሐዋርያት በላይ ቃሉን ልረዳ እና ልያደርግ የምችለው ማን ነው !? ፥ ጌታ "የእግዚአብሔር ቃል ክዳኑ ታቦት" ብለው እቃውን እንድጠሩ ካዘዘው እምብተኛ ሆኖ ሐዋርያት ተውን !? ፥ ወይንስ እኛ ከእነሱ በላይ መረዳት እና 'ሊቃውንት ' መሆናችን ነው !? ፥ ግን ሐዋርያት በአንደም ቦታ "የእግዚአብሔር ታቦት" ብለው አልተጠቀሙም መብያውን፤እወቅም።

የጌታ እራት የሚካፈሉበት እቃ ለሌላ ነገር አለማዋል መልካም ነው።ግን "የእግዚአብሔር ቃል ክዳን ታቦት ነው" ብሎ መጥራት መዘበት ነው። ተጠንቀቅ፤ አዎ አንተ ። የእግዚአብሔር ቃል ክዳን ታቦት እኮ ተራ ነገር አይደለም ማንም ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ሠርቶ ፣ በእግዚአብሔር ስም መጥራት አይችልም።ዋናው ነገረ መብያ ትሪውን በራሱ 'ሥጋና ደሙን ' አልያዘም ፤ እህሉን ብቻ ነው ትሪው የያዘው ። ስለዚህም እህሉን የያዘውን 'ታቦትን' ካልን መጠቻውን ኩባያ ምን ልንል ነው!? ታቦት ተብሎ የተሸከሙት የእህሉን ትሪ ከሆነ ፣ ኩባያውን ለምን አይሸከሙትም !? እንደ ሞኝ ሰው እላለሁ ፤ላሳፍር ፈልገ።

*ሳጠቃልለው

☝አንደኛ እግዚአብሔር ሥሩልኝ አላለም፣

☝ስቀጥል ጽላት የለበትም መብያው ውስጥ፣

☝ደግሞም እግዚአብሔር በእርሱ አድራለሁ አላለም፣

☝ደሙም ሥጋው አንዴ በሰማይ መቅደስ ራሱ ሊቀ ካህናቱ ጌታ አቀረበ እንጂ እዚህ በምድር ላይ እርሱ (መስዋዕቱ) አይቀርብም ፣

☝ለዚያውም አንድ ግዜ ብቻ የቀረበ እንጂ እንደገና እንደገናም አይቀርብም፣

☝በመብያው ሆኘ አነጋግራለሁም አላለም፣ 

☝እነዚህ ከሌሉ ታቦት ልባል አይችልም ፣

☝የእህሉን መቢያ ትሪ 'ታቦት' ካልን መጠጫ ኩባያውን ምን ልንል ነው !? 

☝ መጠጫውንም 'ታቦት' ካላችሁ ፣ ከመጀመሪያው ጀምሮ እንደልብ መሆኑን ተመልካች በቀላሉ ይፈርዷል።

*በመጨረሻም! 

☝ታቦቱ ከእስራኤል ነው የመጣው የተባለው ተረት እንደሆነ አይታችኋል ፣ ድሮ ድሮ " የሙሴ ታቦት ነዉ" ስሉም ስምታቻኃል ፣ አሁን አሁን ደግሞ "የጌታ እራት የምንካፈልበት ስለሆነ ነው" ስሉ .... ፣ አያልቅበት እንደሆነ ይረዷል፤እናም ንቃ አንተ! አትሙት።ግን በዚህ ሁሉ ነገር የእግዚአብሔር ምህረት ይደንቀኛል፤ሃሌ ሉያ።

............................................... 

8. << በአድስ ኪዳን አሰራሩ ለየት ያለ ታቦት አለ የሚሉት ለምን የብሉይን ታቦት ይጠቅሳሉ !? >>

የሞኝ ጥያቄ ነው።ግን መነጋገሩ አይከፋም።መልሱም ታቦት በአድስ ኪዳን የሰራ፣ያሰራ ስለሌለ ነው ።እስክ የሚጠቀሱትን በወፍ በረር እንያ ፦

“ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፥ እርሱና የእስራኤልም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግምባራቸው ተደፉ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ።” — ኢያሱ 7፥6

 ☝ ይህ ታቦት በእግዚአብሔር ትዕዛዝ የተሰራ ነው፤ እግዚአብሔር የሚያውቀው ፣

☝ታቦቱ ብቻውን ስግደት የሚቀበል ቁስ ሳይሆን እግዚአብሔር በእርሱ ሆኖ የሚያነጋግር ነው፣

☝የተደፉት 'እገሌ/ት' በሚባል 'ታቦት' ፊት ሳይሆን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ነው፣ 

☝የእግዚአብሔር ታቦት ስጠራ እግዚአብሔር ራሱ "አምላካቸው ነኝ" ብሎ ባላፈረባቸው ሰዎች ስም እንኳን አይጠራም (ታቦተ አብርሃም ፣ታቦተ ይስሀቅ ፣ታቦተ ያዕቆብ ) እየተባለ፤መጽሐፍ የእግዚአብሔርን ታቦት ስጣራ ፦

1) የምስክሩ ታቦት (ዘጸአት 25÷22፤ 30÷26፤ 31÷7)፣

2) የእግዚአብሔር የኪዲኑ ታቦት (ዘኁሌቈ 10÷33)፣

3) የእግዚአብሔር ታቦት (1ኛ ሳሙኤሌ 3÷3፡፡ 1ኛ ነገሥት 

2÷26)፣

4) ቅደሱ ታቦት (2ኛ ዛና መዋዕል 35÷3)፣

5) የመቅደስህ ታቦት (መዝሙረ ዲዊት 131÷8)፡፡ 

እንዲሁ ተብሎ ነው የተጠራው እንጂ በሠራው በሙሴ ስም እንኳን "ታቦተ ሙሴ "ተብሎ አልተጠራም (ወንድም ተዎድሮስ ደመላሽ እንዳለው፤በእንተ ታቦት፤ገጽ 44 ፤ አልተጠራም ።)

☝ አንድም ቦታ የእግዚአብሔር ታቦት ብቻውን ስግደት አልተቀበለም፤ብቻውን ስግደት የሚቀበል ከሆነ ''ጣኦት" ነው ማለት ነው።ግን በዚህ ክፍል ላይ የሰገዱት ፦ ያልገባቸው ነገር እግዚአብሔር ለመጠየቅ ነው፤እንጂ ለታቦቱ እየሰገዱ አይደለም፤ከእግዚአብሔር ጋር ነው።

☝ምንም እንኳን አሰራሩን ለመግለጽ "የሙሴ ታቦት" እያለን ብንጠራም ፣ "የሙሴ ታቦት" የሚባል የእግዚአብሔር ታቦት የለም።

☝ ከተጠራ አይቀር ''እኛ የጌታ እራት የሚንካፈልበትን ፣ ለዚህ አገልግሎት ብቻ የሚውል "እቃ" ነው" የበሉ እንጂ "የእግዚአብሔር የክዳኑ ታቦት ነው" ብለው መጥራት መዘመበት ነው ፤እንድሰሩ አላዘዘምና ! 

በአድስ ኪዳን አሰራሩ ከብሉይ ታቦት ለየት ያለ 'ታቦት' እንድሰሩ እግዚአብሔር ካዘዘ ለምን ሐዋርያት የመጀመሪያ ተማሪዎቹ አልሰሩም ፣ሐዋርያት የቤተክርስቲያን ፖፖስ አድርገው የሾሙት ለምን አልሰሩም ? ወይንም የሐዋርያት ተማሪዎች ለምን አልሰሩም !? ያልሰሩት እግዚአብሔር ስላላዘዛቸ ነው።እናም ምን ለማለት ነው የብሉይን የእግዚአብሔርን ታቦት ራሳችሁ ለፈጠራችሁት አትጥቀሱ ለማለት እወዳለሁ ።

አይደለም በአድስ ኪዳን ሌላ ፈጥረው 'የቃል ክዳኑ ታቦት ነው ' ማለት ይቅርና የብሉይን እንኳን ልብ አያደርጉትም እንደተባለው እስራኤላውያን ልብ አላደረጉትም እስከዛሬ ፤የእውነት ቃል ስፈፀም እንዲህ ነው።

በእርግጥ ደፈር ብለው ከአድስ ኪዳንም ጥቅሶቹን በመጥቀስ ያስጨንቃሉ ። እስክ እንያ ፦ 

“ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥”— ፊልጵስዩስ 2፥10 

☝ይህንን በመጥቀስ "እኛ ለታቦቱ የሚንሰግደው አልፋና ኦሜጋ የሚል የኢየሱስ ክርስቶስ የባህሪ ስም ስለተጻፈ፣ስላለም ነው" ይላሉ 

☝ በመጀመሪያ ደረጃ እግዚአብሔር በብሉይ ታቦቱ ላይም ስም አልጻፈም ፤ አላጻፈም።ታዲያ ማን ጻሐፉ ብሏአቸው ነው !?" ስለተጻፈ ነው" የሚሉት !? የፈጠሩት ነገር አይደለምን!? 

☝ ደግሞም ፍደል/ስም/ እየጻፈ የሚሰገድ ከሆነ ለምን ሐዋርያት አልጻፉም !? 

☝ ክፍሉ  "ለኢየሱስ ስም " መስገድ እንዳለብን ይነግረናል ፤ያ ማለት "የፍደላትን ስብስብ" እየጻፍን እንድንሰግድ ነውን !? ለፍደሉ!? ታዲያ ለምን በሌላ እቃም ላይ እየተጻፈ አይሰገድም !? ሐዋርያት ለምን ፍደላት እየደረደሩ አልሰገዱም !? ነገሩ ወዲህ ነው ፣

☝ የእግዚአብሔር ስም ወይንም እኛ "ኢየሱስ ክርስቶስ" የሚንለው ስም ከሌላ ፉጡር ለመለየት የተሰጠ መጠሪያ ስም አይደለም ፣

☝ አዎ ብዙ ሰዎች በእንግሊዝኛ "Jesus " ይባላሉ ፤ ግን አንዳቸውም አይፈውሱም ፤ እንደውም ከእነሱ መካከል የአውሬው ተከታይ ልኖር ይችላል ።በእኛ ሀገር ለስሙ ክብር መስጠታችን ደስ የሚል ነገር ነው ለዛ ይሆናል 'ኢየሱስ' ተብሎ የሚጠራ ሰው እስካሁን የሌለው ፣

☝ "የኢየሱስ ስም" እና በጸሎታችን "ስምህን ቀድስህ" የሚንለው የፍደላትን ስብስብ ሳይሆን "ማንነቱን" ነው ፣

☝ "ለኢየሱስ ስም ይንበረከኩ" ስልም ለኢየሱስ ለአምላክነቱ ፣ ለባህሪው ፣ ለማንነቱ ይንበርከኩ ማለቱ ነው እንጂ ፊደላትን በእቃ ላይ ጽፍችሁ "ስሙ የተጻፈበት ነው" እያለን እንድንሰግድ አይደለም ፤እንዲያ ብሆን ሐዋርያት ራሱ በእቃ ላይ እየጻፉ በሰገዱ ነበር ፣

☝ እናም የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይፈውሳል የሚፈውሰው ኢ የ ሱ ስ የሚለው ፈደል ሳይሆን ፈዋሽ ማንነቱ ነው ፣ 

☝ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ስም ብቻ ነው የባህሪ ስም ፣የማንነቱ ስም ፤ መለያ ያልሆነ ስም ፣

☝ በየትኛው ሀገር ቋንቋ የተሰቀለውን ፣ የሞተውን ፣ ኢየሱስን በራስህ ቋንቋ ብትጠራ ትድናለህ፤የደሙ ሃይል ማንነቱ ፈዋሽነት ስለሆነ ።

...............................................

9.<< በሰማይም ታቦት አለን !? የተኛው ነው (የብሉይ ነው ወይንስ የአድስ ኪዳን ታቦት ) ምን ማለት ነው በራሱ!? >>

በየመድረኩ ይስተጋባል ስለ 'ታቦት' ስነሳ "ታቦት አይደለም በምድር ላይ በሰማይም አለ ፤እዚህ ጠልተ ወደተስ ትሄዳለህ በሰማይ ቤት ስትሄድ? እዛም የኛ ታቦት አለ" የሚል መፈክር ያነ አስምቻለው(ነበረ)፣ስምቻለሁም፤አሁንም የሚያሰሙ አሉ።

ለዚህ መፈክር መልሴ አጭር ጥያቄ ናት ፦"የተኛው ታቦት ነው !? ሙሴ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ የሠራው ታቦት ነው ? ወይንስ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ በራሳችሁ ፈቃድ የሰራችሁት 'ታቦት' ነው  በሰማይ ያለው !? "

በእርግጥም "የእኛ ታቦት ነው" ይሏል፤ግን ምን ማለት እንደሆነ "ቆም" እንድሉ ነው የጠየኩት፤የራሳቸውን ዓይነት ከሆነ በምድር እንኳን ያዘዘ የለም እንድሰራ ፣ ወይንም "የአድስ ኪዳኑ ታቦት አካሉ የኛው ነው" እያሉ ይሁን !? አዎ እንዳዛ ማለታቸው ነው ማለት ይቻላል።

እስኪ ክፍሉን እናጥና “በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፥ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ።”ራእይ 11፥19 

ወደዚህ ማብራሪያ ከመግባታችን በፊት በዚህ ክፍል ላይ በቤተክርስቲያኗ መምህራን ዘንድ (ቤተክርስቲያንቷ) ወጥ ያለ አስተምህሮ የላትም።ይህንን ወንድም ተዎድሮስ ደመላሽ የገመገመውን ከበእንተ ታቦት ከምለው መጽሐፍ በቀጥታ ከገጽ 55_56 ያለውን ቀንጨብ አድርገ ለማቅረብ እወዳለሁ ፣ 

☝ ‹‹አቡቀለምሲስ ዮሐንስ በራእዩ <የቃል 

ኪዲኑ ታቦት በሰማይ ታየ> ብል የመሰከረለት ታቦተ

ጽዮን ሳትሆን አማናዊት ጽዮን ድንግል ማርያም ናት፡፡

አማናዊት ጽዮን ድንግል ማርያም ሰው እንደ መሆኗ

ሞታ ተቀብራለች፤ ይሁን እንጂ ተቀብራ አልቀረችም 

እንደ ልጇ እንደ ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን ተነሥታ ወደ ሰማይ አርጋለች፡፡ በልጇ በወዳጇ በክርስቶስ ቀኝ ተቀምጣ ዮሐንስ ያያት ድንግል ማርያም ናት ታቦት ቢሆን በሰው አምሳሌ ተቀምጦ አይታይም ነበርና››፡፡

 ምንጭ ኪዲነ ማርያም ጌታሁን (መምህር)፣ ገድል ለመናፍቃን ገደል (1996) ገጽ 119-120፡፡

*በዚህ ትምህርቷ መሠረት ዮሐንስ ያየዉ ታቦት ድንግል ማርያምን ነው ፣

☝ ‹‹ከዚህ በኋላ በሰማይ ያለ የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ አለ መንግሥተ ሰማይ ተሰጠች፤ በአስተርእየት ታቦተ ሕጉ ለእግዚአብሔር እንተ ውስተ መቅደሱ ፤ ሕጉን ጠብቃ የምትኖር ምእመን መንግሥተ ሰማይን ወርሳ ከብራ ታየች››፡፡ ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ፣ መጻሕፍተ ሐድሳት ሠለስቱ (2007 -

ሦስተኛ ዕትም) የራእየ ዮሐንስ ም. 11 ቈ. 19 ማብራሪያ ይመልከቱ፡፡

*በዚህ ትርጉም መሠረት ዮሐንስ ያየው ታቦት ምዕመናንን (ትን) ነው ፣

እንግድህ ተመልከቱ በአንድት ቤተ እምነት ሁሉም የየራሱን አስተምህሮ ስያሰራጭ ፤ ሁሉም ደግሞ ትክክል ስባሉ ። 

የክፍሉን አውድ እንደሚከተለው ቀርቧል ፦ 

“በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፥ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ።”— ራእይ 11፥19

☝በሰማይ ፤ ሙሉዕ ቅድስና ወይንም ፍጹምነት ያለው ህይወት ስለመኖሩ የሚያሳይ ሳይሆን ከሰይጣን ጋር ጦርነትም ያለው ነው (በአውዱ) ፣

☝የእግዚአብሔር መቅደስ ፤ ቃሉ “.. እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል፦ በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።” 2ኛ ቆሮ 6፥16፤እንደሚል ፥ እግዚአብሔር ከሕዝብ ጋር እንደሚኖር የሚያሳይ ነው ፣

☝ የኪዳኑ ታቦት ፤ የሙሴ ታቦት ብጠፋም እግዚአብሔር ክዳን የገባውን ሕዝብ አይረሳም ፣

☝መብረቅና ድምፅ ነጎድጓድም ፤ ታላቅ የእግዚአብሔር መገለጥ የሚሆነውን የሚያሳይ ነው፣

☝ስለዚህም እግዚአብሔር ከሕዝብ ጋር በመካከላቸው ሆኖ ፣ ክዳኑን እንዳልረሳ በታላቅ ኃይል በሲና ተራራ እንደሚገለጥ ፣ እንደሚመጣ የሚያሳይ ክፍል ነው፤እንጂ በሰማይ በሙሴ እንድሰራ የተደረገው የክዳኑ ታቦት ይሁን ፤ ዛሬ ሐዋርያት ፣ የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎችና ተማሪዎች የማያውቁት 'ታቦት' በኢኦተቤክ የተፈበረከው በጭራሽ በሰማይ የለም፤ለዚያውም ዥርግ ሰሌዳ ።በፍጹም የለም ፣

☝ ልታውቁ ብትወዱ "መቅደሱ በእጅ አልተሰራም" የሚለው ቃል የታመነ እና ሁሉም እንድቀበሉት የተገባ ነው፤ቁስን ከአዕምሮ የሚፍቅም ነበር።እግዚአብሔር ምድርቷን ይፈውሳት።

............................................

10.<< የመጽሐፍ ቅዱስ ዝምታ ይከበር ! >>

በዚህ ክፍል ላይ እግዚአብሔር የተናገረውን ፣ ሕይወት እንድሆነልን ያስቀመጠውን በመቀበል ፣ የቃሉን ዝምታ የመንፈስ ቅዱስ  ዝምታ መሆኑን አክብረን መቀበልን በማበረታታት ፥ ከተደፈሩ ጥቅሶች ጥቂቶቹን እናያለን። 

“ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም።”— ማቴዎስ 24፥36

☝ኢየሱስ ይህንን ስናገር ራሱ በሙሉዕ ሰውነቱ ብቻ እንኳን አላውቅም በማለትም ነው፤ሰው ውስን እና ደካማ ነውና፤ጌታችንም በሙሉዕ ሰውነት አላውቅም አለ፣

☝ኢየሱስ በሰውነቱ አላውቅም ያለውን ፣ ፉጡራን ሰዎች ደግሞ ያውቃሉ ማለት ዘበት ነው ፣

☝ ቅዱሳን መላእክትም አያውቁም ፣

☝ምክንያቱም ይህች ቀን የጌታ መምጫ ቀን ናትና ፣

☝ ግን የኢኦተቤክ 'ሊቃውንት' ብቻ ያውቁታልi ከሰውም ከመላእክትም እና ከኢየሱስ ስግውነት አልፈው ፤ ይህ ነው ድፍረት ፣

☝ ይህንን ቀን እናውቃለን የኢኦተቤክ 'ሊቃውንት' ያሉት በማቴዎስ ወንጌል አንደምታ ክፍሉን ማየት ይቻላል ።የሚያውቁት ከእኔ ወሩ ነው ።እንዲህ ብለውታል ፦"በዘመን ዮሐንስ ፣በወርኃ መጋቢት ፣እሁድ እለት በመንፈቀ ለሊት እንደሚመጣ ተርጉመውታል ፤ዓ.ም አልጠቀሱም እነኚ ሁሉ አዋቅ ነን ባዮች ።

☝ በእርግጥ የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ያበረከተችሁት ቤተክርስቲያንቱ ብትሆንም ይህኛውን ግን በየትኛው ሕሳብ ስለት እንደደረሱ አይታወቅም፤ በሌላ ክፍል ጌታ “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።”— ማቴዎስ 24፥42 ፤ በማለት እንደሌባም  እንደሚመጣ በቁ.43ም እንደገለጸ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል ፣

☝ስለዚህም የመንፈስን ዝምታ አለማክበር ሃሰተኛነት ነውና፤ተጠንቀቁ፤እወቁም።

ሌላው ደግሞ ፦

ማቴዎስ 2

¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯

¹³ እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ፦ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ #ግብፅ_ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ #በዚያ_ተቀመጥ አለው።

¹⁴-¹⁵ እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ፦ ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም #ወደ_ግብፅ_ሄደ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ #በዚያ_ኖረ።

 …  

¹⁹ ሄሮድስም ከሞተ በኋላ፥ እነሆ፥ የጌታ መልአክ #በግብፅ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ፦

²⁰ የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ አለ።

²¹ እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ያዘና ወደ እስራኤል አገር ገባ።

ይህንን ክፍል በመነሻነት በመያዝ በተለመደው እናውቃለን ባይነታቸው በመኮፈስ "ማርያም እና ኢየሱስ ደግሞም አረጋዊ ዮሴፍ ጨምሮ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው (አክሱምን..) እና የኢትዮጵያ አራት አጥቃጫዎችን በመባረክ ፣ ለእናቱ የተሰጠች የቃል ክዳን ምድር ተደርጎ ይተረካል" (ተአምረ ማርያም ) 

☝"..ወደ ግብፅ ሽሽ.." እዚህ ጋ የጌታ መላአክ ያዘዘው ወደ ግብፅ ሀገር እንድሸሽ ነው ፣

☝ ደግሞም "በዚያውም ወደ ኢትዮጵያ ምድር ሂድ" አላለሁም ፤ እንድሁም ተመለስ እስከሚልህ ድረስ "በዚያ በግብፅ ተቀመጥ" ነው ያለው ፣

☝ ዮሴፍ የመላአኩን ቃል ተቀብሎ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ ፤ ማለትም የመልአኩን ቃል አላቃለለሁም ፣ እንዳለውም አደረገ ፣

☝ ቃሉ "በዚያ በግብፅ ምድር ኖረ" ካለን በግድ ግብፅን ኢትዮጵያ ልናደርጋት ወይንም በግድ ጎትተንም ኢትዮጵያ ለማስገባት መጣር የለብንም ፣ 

☝ ሄሮድስ ከሞተ በኃላ መልአኩ ለዮሴፍ ወደ እስራኤል እንድመለስ በግብፅ እያለ መንገሩ የተአምረ ማርያምን ተረካ ተረት ያደርገዋል ፤ምክንያቱም "ተመለሱ" መልአኩ ስልም በግብፅ ነበሩ እንጂ በኢትዮጵያ ምድር አልነበሩም ፣

☝ ስለዚህም አውቃለሁ በማለት መጽሐፍ የሚለውን በመተው እና የራስን ሀሳብ በማስገባት መንፈስ ከገለጠው በላይ እናውቃለን ብሎ መተርተር በቃሉ መዘበት ነው።ብዙ መጥቀስ ይቻላል ለማሳየት ግን በቂ አድርገ ቆጥርያለሁ።" አሁንም ጌታ ምህረት ያድርግ ።"

11. << ለቃሉ እና ለቃሉ ጌታ ታማኝ እንሁን ! >> 

ለቃሉ እና ለቃሉ ጌታ ታማኝ መሆን የመንፈስ ቅዱስ ዝምታን ማክበርም ብሆንም በዚህ ርዕስ ስሪ ላይ የማተኩረው የተሸቃቀጡ ጥቅሶቹን እና ለራስ ለግል ፍላጎት ስባል በትክክል ያልተተረጎሙትን  በወፍ በረር አንድ ሁለት የምናይ ይሆናል።

“ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ፥ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ ማንምም ሊዘጋው አይችልም፤ ኃይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፥ ስሜንም አልካድህምና።”— ራእይ 3፥8

☝እዚህ ጋ "..የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ."የሚለው ስንኝ ይዘው ፣ የተከፈተው በር "ኤኮኖሚ ፣ ዝና፣..ወዘተ ነው በማለት " ይከፈታሉ ።እግዚአብሔር የመባረክ ችግር የለበትም፤እጆቹ ያጠግባሉ፤አያልቅም፤አይጐድልም ።ግን የክፍሉ አውድ የሚለው የተከፈተው በር የሥራ በር ነው ይህም "የወንጌል ሥራ" ነው። ቃሉን ማስጨነቅ አግባብ አይደለም ። 

...

“እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው።”— ዮሐንስ 1፥52

☝ይህንን ጌታ " መላእክት ይወጣሉ ይወርዳሉ ያንንም ታዩታላችሁ " ብሎ የተናገረውን በራሱ ላይ እንደሆነ እየታወቀ የእውነትን ቃል ፣ በመሸምጠጥ "ማርያም ናት"በማለት የሚሸቃቀጡ ሚሊዮኖች ናቸው ፣

☝ ግለጽ ነው በአንድም ክፍል ላይ መላእክት በማርያም ላይ መውጣታቸውን እና መውረዳቸውን ደግሞም መሰላል መሆኗን የሚያሳይ ክፍል የለም፣ 

☝ግን የክህደት ጥግ ኢየሱስ "በእኔ ወደ አብ ትደርሳላችሁ ፤ እኔ መንገድ ነኝ" ያለውን በመሸምጠጥ እስካሁን ለወንጌል ጠላት ሆነው ይመላለሉ፤እግዚአብሔር ምድርቷን ይፈውሳት።

የእግዚአብሔርን ቃል የነጠረውን እውነት ፣ ለራስ ለግል ዕሳቤ እና አስተምህሮ ማዋል የወንጌል ጠላትነት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምን ይሆናል!? ልክ እንደዚህ ነው በምድራችን 'የታቦት' ነገረ የተፈጠረው ከላይ እንዳየነው ።

ጸሎት

ቅዱስ አባት ሆይ አንተን እና አንተን ብቻ አጥርተን ማየት እንድሆንል እርዳን፤በእውነት አባ በድለናል ፤ በአንተ ላይ ሌላ አምላክ አምልከናል፤ አመዝረናል፤አባ ምድርቷን በምህረት እንድትጎበኝ እለምንሃለሁ ፤ከነጣቅዎች (ለራሳቸው ወደ መንግሥትህ አይገብም ወይንም ሌሎችን አያስገቡም) ከእነዚህ እንድትነጥቃቸው አባ እለምንሃለሁ ፤አባ ቸርነትህ አይለየን ፤ እጆችህ ምድሯን በወንጌል ያምሱ፤ያርሱ፤የዘላለም አባት ሆይ በርናባስ እንድሆንልን ስለሚያስቱ 'መምህራኖች' እለምናለሁ ፤ እንድትወርሳቸው ።ሰለሰማህ ተባረክ ምስጋና፣ ወዳሴ ና ክብር ላንተ ይሁን።ሃሌ ሉያ።አሜን።

እድሉ ዮሐንስ ጋምሳ 

(ደቀመዛሙርቱ )


Comments

Popular posts from this blog

"ደብተራ ማን ነው?" ጸረ ደብተራ ንቅናቄ በሊቀ ጠበብት በዶክተር ዘሪሁን ሙላቱ

ካህናት ነን

የኢየሱስን እናት ብፅዕት ማርያምን አትሳደቡ! (2)