የልሳን ጸጋ (የቋንቋ ስጦታ )
የቋንቋ ስጦታ (የልሳን ጸጋ)
☝ የልሳን ጸጋ ቀርቷልን !?
☝ የተገለጠው ቋንቋ የማይተረጎም ከሆነ ፥ በቤተክርስቲያን [ሳይተረጎም] መነገሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ?
☝ እንዴት እንጠቀም ?
☝ የልሳን ጸጋ በአግባቡ ከተጠቀምን ጥቁሙን ፣
☝ በቤተክርስቲያን የልሳን ጸጋ በአግባቡ ካልተጠቀምን ጉዳቱ ፣
☝ የልሳኑ መልእክት ስተረጎም ትክክለኛነቱን እንዴት እናውቃለን !?
☝ "" አንድ አማኝ በልሳን ጸጋ ባይናገር በመንፈስ ቅዱስ አልተጠመቀም ማለት እንችላለን !? ""
_____________________________________
ይህ የቋንቋ ስጦታ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ፦"አደስ ቋንቋ ፣ልሳን " ተብሎአል ።ከዚህ በፊት የቋንቋ ስጦታ ወይንም ልሳን የተባለው "ቀርቷል ወይንም አሁንም አለ !?" ብዬ ጠይቄ ነበር።ስለሰጣችሁኝ ሀሳብ አመሰግናለሁ ግን በቂ የሙግት ነጥብ አላገኘሁትም (ቀርቷል በሚሉት ወገኖች )።
እኔ የልሳን ጸጋ አለ ብዬ በአራት ነጥብ ዘግቼ አምናለሁ( ሀሳብ ለመቀበል ነፃ መሆነ ይታወቅ) ።
ቀርቷል የሚሉት ሰዎች የሚያቀርቡትን ነጥቦችን (ከዚህ በፊት ካነበብኩት በራሪ ጹሑፉ "አንቀፀ ብርሃን" የሚል ነው) ላቅርብ ፦
1ኛ. "ልሳኖች ብሆኑም ይቀራሉ 1ቆሮ 13፥8 " ይህንን በመጥቀስ ይህ አንቀፀ ብርሃን የሚለው በራሪ ጹሑፍ "የልሳን ጸጋ ቀርቷል" ብሎ ይሞግታል ።
ይህ ክፍል የልሳን ጸጋ አሁን መቅረቱን አያሳይም የሚለውን ላቅርብ፦
፦ ሙሉ ቁጥሩን እንመልከት ።“ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል።”— 1ኛ ቆሮንቶስ 13፥8
በእርግጥም በዚህ ክፍል ላይ "ትንቢት ይሻራል" ይላል ምክንያቱም ስፈጸም ያንን ትንብት ገና ይፈጸማል ብሎ ተስፋ አድርጎ የሚጠብቀው የለም፤ተፈጽሟልና፤ግን የትንቢት አገልግሎት አሁን ቀርቷል ማለት አይደለም።
ወደ ጉዳያችን ስንገባ መጽሐፍ ቅዱሳችን ፦"ልሳኖችም ቢሆኑ ይቀራሉ" ይለናል፤ይቀራሉ ይለናል።"መቼ ነው የሚቀረው?" የሚለውን እዛ ክፍል ላይ ብቻ ከዶቆስን ልናውቅ አንችልም ወይንም ማስረጃ አለባ ግምት እንድንሰነዝር ያደርገናል ፤ ""ተቃዋሚ የተባለው ፣ "ተሃዲሶአዊ እንቅስቃሴ" እስኪመጣ ድረስ የለም""፤ የሚሉ ዓይነት ግምት ውስጥ እንገባለን ።
በእውነትም ልሳን ይቀራል? አዎ ይቀራል።የሚቀረው መቼ ነው ? የሚለውን ለማወቅ ወረድ ብለን ከቁ.8 አልፈን ማንበብ ይጠበቅብናል ። እንዲህ ይለናል ፦
1ኛ ቆሮንቶስ 13
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና፥ ከትንቢትም ከፍለን እንናገራለንና፤
¹⁰ ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ተከፍሎ የነበረው ይሻራል።
"እውቀት ፣ትንቢት.." እነዚህ ጸጋ ስጦታዎች ናቸው፤ግን ሙሉ በሙሉ አናውቃቸውም ይለናል ።ልሳንም ጸጋ ስጦታ ነው፤በከፍል የሚታወቅ ፤እንደሌሎቹ ።
ስለዚህ በከፍል በከፍል የሚታወቀው ይቀራል፤ይሻራል። መቼ ?ፍጹም የሆነ ሲመጣ፤ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ስመጣ ፤ልሳንም ፣ትንቢትም ፣እውቀትም ይቀራል ማለት ነው።
በዚህ ክፍል ላይ በ1ቆሮ 13፥8 ልሳን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጸጋዎችም እንደሚቀሩ ይነግረናል ፤ታድያ ለምን ልሳንን ብቻ ነጥለን ተሽሯል፤ቀርቷል እንላለን!? የሚለው የእኔ ጥያቄ ነው።
ከላይ "ልሳን አሁን ቀርቷል" ፤"ኢየሱስ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት ቀርቷል(ፍጹም የሆነው ከመሚጣቱ አስቀድሞ ቀርቷል)የሚለው ሀሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደሚቃረን፤ወይንም 'ፍጹም የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቷል' እንደማለትም ስለሆነ፣ የተገናዘባችሁት ይመስለኛል።
...........
"አንቀፀ ብርሃን" የሚለው በራሪ ጹሑፍ ሌላ ነጥብም ያነሳል "የቋንቋ ስጦታ ቀርቷል" የሚለውን ለማሳየት ፦
2ኛ.በአጭሩ ፦"መጽሐፍ ቅዱስ ከ2000 በላይ በሆኑት ቋንቋዎች ስለተተረጎመ እና በየቦታው ተርጓም ወይንም ሁለት ቋንቋ የሚችል ሰው ስለታይጣ የቋንቋ ስጦታ ቀርቷል " የሚል ነው።
የቋንቋ ጸጋ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚሰጠው ሰምዎቹ የተናጋሪውን ቋንቋ ስለማይሰሙ ወይንም ተናጋርው የሰምዎቹን ቋንቋ ስለማያውቅ ብቻ ነውን !?
ይህን የሙግት ነጥብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደሚቃረን፣ለማሳየት ጥረት አደርጋለሁ ።
፩ኛ."ሰምዎቹ የተናጋሪውን ቋንቋ ብሰሙም(ተናጋሪው የሰምዎቹን ቋንቋ ባይችልም)የልሳን ጸጋ ይሰጣል ።ለዚህ ሁነኛው ማስረጃ የሐዋ 2 ነው።“ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ፦ እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን?”— ሐዋርያት 2፥7 ። ከተለያየ ከዓለም ክፍል የመጡት አይሁዳዊያን "የሚሰብኩቱ፤ሰዎቹ" የገሊላ ሰዎች እንደሆኑ አውቀዋል ።ያ ማለት ከሌላ ሀገራት የመጡት ፥ የአይሁዳዊያንን ቋንቋ ይችላሉ ማለት ነው።እንድሁም ሰዎቹን ጭምር ከገሊላ አውርጃ እንደሆኑ እና ከንግግራቸው ሌዛ የተነሳ የራሳቸውን ወገን አይሁዳውያን መሆናቸውንም (ከገሊላም እንደሆኑ ጭምር)አውቀዋለሁ ።ስለዚህ ከተለያየ ዓለም የመጡት አይሁዳውያን ፥ የአይሁድ ቋንቋ እንደሚችሉ ማወቅ ይቻላል።
ስለዚህ እነ ጴጥሮስ ፣ በራሳቸው በገዛ ቋንቋቸው (በአረማይክ) ብሰብኩ እንኳ፥ በአረማይክ መስማት የሚችሉ ሕዝብ ናቸው፤የመጡቱ።ግን በሰዎቹ ሀገር ቋንቋ ሰበኩ።ስለዚህ ይህ ነጥብ ከላይ የተነሳውን "ተርጓሚ ስላለ ጸጋው ቀርቷል" የሚለውን ሀሳብ ውድቅ ያደርጋል ማለት ነው።
፪ኛ.ተናጋሪው የሰምዎቹን ቋንቋ ብችልም ይሰጣል። የ1ቆሮ 14 ላይ የተገለጸው የልሳን ስጦታ ለአንድ አጥቢያ ምዕመናንን የተገለጠ ነው።ማለትም በገዛ ቋንቋቸው መናገር እየቻሉ ፥ግን የቋንቋ ነፃ ስጦታ ተሰቷቸዋል ።ይህም "ከ2000 በላይ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ተተረጎመ የልሳን ጸጋ ቀርቷል" የሚለውን ነጥብ ውድቅ ያደርጋል ማለት ነው።
የቋንቋ ስጦታ እግዚአብሔር ስለወደደ ስያድል፣ሁለም ሰምዎቹ የማይሰሙት ወይንም "ስጦታውን የተቀበለው ተናጋሪው" የሰምዎችን ቋንቋ ስለማያውቅ ብቻ አይደለም፤እግዚአብሔር ይህንን ስሰጥ ልሰራ ወድዷልና ፤ ዓላማዊን መግባባት ብቻ አድርገን አንውሰድ።ምክንያቱም ከእግዚአብሔር የተሰጠ ነፃ ስጦታ ነው ፤ለቤተክርስቲያን ሕንፀት ።
የቋንቋ ስጦታ እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን የሰጠው፦ መግባባት ስላቃታቸው ብቻ አይደለም፤እውነት እውነት ።ምክንያቱም መግባባት ስላቃታቸው ብቻ ብሆን፥ ከዓለም ሀገራት እየመጡ፥በዓለ አምሳ የተባለውን በዓላቸውን፥አይሁዳውያን እንዴት አከበሩ ከመንፈስ ቅዱስ መውረድ በፊት? ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት አላከበሩም ?ኢየሱስ ተወልዶ እስከሚሞት ድረስ አላከበሩም ? አክብረዋል ። ከኢየሱስ እርገት በኃላ ለማክበር ስመጡ በምን ቋንቋ ይግባቡ ነበር ?
የቋንቋ ስጦታ ፣የቋንቋ ስጦታ ነው።ቋንቋ ዓላማው መግባቢያ ብሆንም ጸጋ ስሆን ግን ዓላማው ለቤተክርስቲያን ሕንፀት ብቻ መሆኑ መረሳት የለበትም።እርስበርስ መግባቢያ አራማይክ ቋንቋ እያላቸው ፤ለተናጋርዎች የሌሎች ሀገር ቋንቋ መሰጠቱ ያላመኑትን እንዲያምኑ አድርጓል።
በመጨረሻም ሳጠቃልለው የቋንቋ ጸጋ ፦"ጸጋ መሆኑ ከታመነ" ፥አገልግሎቱም ለቤተክርስቲያን ሕንፀት መሆኑን እንጂ ማግባቢያ ብቻ አድርገን ማሰብም መወሰድም የለብንም።
...............
""" የተገለጠው ቋንቋ የማይተረጎም ከሆነ ፥ በቤተክርስቲያን [ሳይተረጎም] መነገሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ? ወይንስ አይደለም ? """
ይህንን ጥያቄ ሳነሳ ሁለም የማልረሳው ነገር ብኖር በአካል ስለ ልሳን ጸጋ አስቸ ስናገር ፥ ከወንጌላውያን አማኞች የሆኑቱ ተጨንቀው ስመለከቱ ፦""አቁም እንደማለት ፊት እያሳዩ፤የመንፈስ ቅዱስ ስራ ይመረመራል እኮ! ምን ያደርጋል አሁን?" ስሉ ፣ "የኢኦተቤክ አባል የሆኑቱ ደግሞ አሁን አሁን አሜን ለማለት ደርሰው መስማታቸውን አልረሳውም፤"ልጁ ያለው ሕይወት አለው" ስል የሚጨማደደው ፊት"" ።ብቻ የቃሉ እውነት ስነገር በቃሉ እውነት መደሰት፣ መባረክና መታነጽ እየተቻለ ፥ ሰው ስለራሱ ውዥንብር ልምምድ እንዴት "ተነካብኝ" ብሎ ይጨነቃል።መጽሐፍ ቅዱስ ልምዳችንንና ሀሳባችንን እንድቀርጸው ሁለም የተዘጋጀን እና ፈቃደኞች መሆን ያስፈልጋል ።
ማነኛውም ሰው "ከወንጌላውያን አማኞች እስኪ ስህተት ትምህርት አሳይ" ብትል ፣ይህንን ውዥንብር ልምድ ጠቅሶ መናገሩ አይቀሬ ነው፤ዋናውም ማነቆም ነውና፤እውነትም ነው።
እኛ ግን የሚንታደሰው ሰዎች ስለሚናገሩት እና ስለወቀሱ ሳይሆን ታድሰን ያላለቅን ስለሆንን ነው።ሁለም የሚንታደስ አማኞች ስለሆንንም ነው፤ሆኖም ግን "ስለ ልሳን ልምድ ጉዳያችን" ለምን ከምንኮራበት መጽሐፍ ቅዱስ መጥቀስ አቃተን ? እንደ ቃሉም ፥ ከልምምዳችን መውረድስ ለምን አቃተን ? የሚለው የእኔ ድምጽ አልባ ጩኸትም፣ጥያቄም ነው።
እጂግ ከምሳቀቅባቸው እና መንፈሴ ከምታወክባቸው ነገሮች አንዱና ዋነኛው "ሁሉም በአንደ በልሳን ጸጋ የሚናገር መሆኑ ነው"።ግን ለምን አልሳቀቅም ? ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድርግት በቤተክርስቲያን ስመለከት ፤ለምን አልታወክም !? የሚሉት ካልገባልኝ ፤ካልተተረጎመልኝ።
ይህንን ጹሑፍ ለመጽሐፍ ያነሳሳኝ ፦ ይህንን ድርግት እንደ ምክንያት ቆጥረው፤አድርገው ፥ "ወንድሞቼ" ማርሽ እና ዘር በመቀየራቸው ነው (""እንደ ምክንያት' ያልኩት አንድ ስህተት ልምድ እንዴት ከባዕድ አምልኮ በለጠባቸው ወይንም ለንፅፅር ቀረበ!?" የሚለው ጥያቄ በውስጤ ስላለ እና ዘር መቀየርም አግባቢም ስላልሆነ ነው)፤የጻፍኩት እኛ ፍጹም በመታደስ አንዳች ጥቅስ የምጠቅሱትን እንኳ እናሳጣ ለማለትም ነው፤ወደ ኃላ ስለ መመለሳቸው ። ብቻ መሆን ያለበት የቃሉ እውነት ለምን አይሆንም !? ደግሞም ለምን !?
ምንም እንኳን ፈጣን የሆነ ጥልቅ ተሃድሶ ባልጠብቅም ፣በሽታ መሆኑ ከታመነ እና ህመሜን እንድትጋሩኝ እና እንዲሰማችሁ እፈልጋለሁ ።
ደግሞም ምናልባት Sense Organ የሚባለውን ካጣችሁ ማለትም በሰውነታችሁ ቁስለኛ ሆናችሁ እያላችሁ፣ቁስላችሁ የማይሰማችሁ ወይንም የተጎዳበት የሰውነት ክፍል በአዕምሮአችሁ እንዳይታውቅ ከተደረጋችሁ sense organ አጥታቿል ማለት ነው።ይህ ማለት የራሱን እጅ ራሱ ቆሮጦ ፤ ሕመም የማያሰማ በሽታ ዓይነት ነው፤ sense organ ማጣት ።
ስለዚህም መንፈሳዊ sense organ ማጣት ለቃሉ እና ለቃሉ ጌታ ታማኝ አለመሆን ነው። ቅዱስን መንፈስን ማሳዘን ነው፤ካልተሰማን ፤ካላመሜን።ወንጌላውያን አማኞችን ፦ሕመሜ እንዲሰማችሁ በክርስቶስ ፍቅር እለምናችኋለሁ ።
ወደ ርዕሱ ሀሳብ ስገባ ፦ የልሳን ጸጋ ለሰምዎቹ ባይተረጎም ፣ ምንም ችግር እንደሌለበት(መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንደሆነ)ለማሳየት ፣ለመጥቀስም የደፈረ የለም። ይህ ጸጋ ጥቃትም ፣ ብዝበዛም የተፈጠረበት ጸጋ ነው። ጥቃት ያልኩት እንደ ቃሉ ባለመተገበሩ ነው፤ብዝበዛ ያልኩት ጸጋውን ያልተቀበሉት ጭምር "ለአምስት ደቂቃ.. ወዘተ ልሳን እንናገራለን" በማለት ስለተበዘበዘ ነው፤በግድ።
የተገለጠው የቋንቋ ነፃ ስጦታ ለሰምዎች ግልጽ እና የማይረዱት ከሆነ ፥ ሳይተረጎም መንገር ቸልተኛነት ነው፤ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም ።ቃሉ እንደሚል ፦ “የሚተረጉም ባይኖር ግን በማኅበር መካከል ዝም ይበልና ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር።”— 1ኛ ቆሮንቶስ 14፥28
ይህንን ለሰምዎች ግልጽ ያልሆነውን ቋንቋ ፣ ግልጽ እንዲሆንና ሰዎች አምላካችንን እንዲያመሰግኑ ለማስቻል እንዴት እንጠቀም (በቀጣይ) ፦
..............
"የቋንቋ ነፃ ስጦታ" አንድ ክርስቲያን ቋንቋውን ሳይማር፣ ሳይለማመድ ፣ እግዚአብሔር እንዲሁ በነፃ የሚሰጠው ስጦታ ነው።
ታዲያ ይህ ስጦታ በሐዋ 2 ፣ እንደተቀመጠው በግልጋሎት ላይ ስውል፦ ግቡን መትቷል፤ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር መንግስት ጨምሯል፤ግልጽ ስለሆነ መመሪያ የለውም።ነገርግን የቋንቋ ስጦታው ለተናጋሪዎችም ለሰምዎችም ግልጽ ያልሆነ ከሆነ ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዴት አድርገን መጠቀም እና ግቡን መምታት እንዳለብን ይገልፃል በ1ቆሮ 14 ላይ እንደተቀመጠው ፤ እንደሚከተለው ቀርቧል ፦
1ኛ.ቋንቋው የግድ መተርጎም አለበት፤ስለዚህም ራሱ ለልሳኑ [አጥብቆ] መጸለይም አለበት ።“ስለዚህ በልሳን የሚናገር እንዲተረጉም ይጸልይ።”— 1ኛ ቆሮንቶስ 14፥13።
2ኛ.ራሱ መተርጎም ካልቻለ ወይንም የመተርጎም ጸጋ ከሌለው፦የመተርጎም ጸጋ ባለው ሰው ያስተርጉም ፤መተርጎምም ራሱን የቻለ ጸጋ ነውና ። “..፥ በልሳን መናገር አለው፥ መተርጐም አለው፤ ሁሉ ለማነጽ ይሁን።”— 1ኛ ቆሮንቶስ 14፥26።እንደሚል።
3ኛ.ከተተረጎመ ተራ በተራ ይናገሩ።ሁሉም በአንደ አይናገር።“በልሳን የሚናገር ቢኖር ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት ሆነው በተራቸው ይናገሩ አንዱም ይተርጉም፤”— 1ኛ ቆሮንቶስ 14፥27
4ኛ.የተተረጎመውን ደግሞ ፦ “ ...፥ በመግለጥ ወይም በእውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኋችሁ ምን እጠቅማችኋለሁ?”— 1ኛ ቆሮንቶስ 14፥6 ፤ እንደሚል ፥ በአጭሩ የልሳን ጸጋ ከሌሎች ጸጋዎች ጋ ተቆራኝተው መነገር እንደሚገባ እንረዳለን፤ማለትም ብያንስ በአንዱ ጸጋ መላወስ(መከሸን) አለበት ማለት ነው ፦
፩.የተተረጎመውን ልሳን "በእውቀት መናገር" ፦
ይህ ጸጋ በልሳን የተናገረውን ምስጥር ነገር ( ሰዎች ያላዩትን ወይንም ማየትም ያቃታቸውን ነገር፤ችግር በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ፦ ጥበብ በተሞላ መንፈስ ፣ የተገለጠውን ልሳን እንዲናገር የሚያሳስብ ነው።ልሳኑን በዚህ ጥበብ ከሽኖ መናገር እንዳለበት ሐዋሪያው ይገልጻል ።
፪.የተተረጎመውን ልሳን "በትንቢት መናገር"፦
ይህ ጸጋ በልሳን የተነገረውን ፥ ግለሰብን ይሁን ብድን ወይንም ቦታ እና ስም በመጥቀስ ፥ በግልጽ ፥ በማያሻማ መልኩ የልሳኑን መልእክት መንገር እንደሚያስፈልግ ሐዋርያው ይነግረናል ።
፫.የተተረጎመውን ቋንቋ "በትምህርት መንገር" ፦
ይህ ጸጋ በልሳን የተነገረውን በማህሩ መካከል ያሉትን ዕድሜ ክልል፣እውቀት ልክ፣..ወዘተ ፥ ልክ እንደ አስተማሪ ፦ ልጎርሱ ፣ ልያላምጡ በምችሉ መንገድ፣ ሁሉንም ነገር ፣ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ፣ መንገር አለበት ።ምናልባትም መልእክቱ በግል የምነገርም ልሆን ይችላልና።
*ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በፍቅር መሆን እንዳለበት ማንም ይወቅ፤ካላወቀ አይታወቅ ።
ከላይ እስከታች ባለው ዝርዝር መሠረት ተናጋሪው ሆነ ሰምዎቹ የማያውቁትን ቋንቋ (ልሳን) በዚህ ልክ እንደ ቃሉ ብንጠቀም ፦ እግዚአብሔር ይከብርበታል፤ቤተክርስቲያንም ይታነፃል፤ለዓላማውም ይውላል።
በነዚህ ደንቦች እንደ ቃሉ እስከሄድን ድረስ ፤ ማንም እንደ ቃሉ ፦ “" ..፥ በልሳኖች ከመናገርም አትከልክሉ፤” 1ኛ ቆሮ 14፥39 ፤በማለት፥ በሐዋርያው ትዕዛዝ ጸጋውን አበረታታለሁ ።
የልሳንን ጸጋ በዚህ መሠረት ከተጠቀምን፦ ጥቁምን (በቀጣይ) ፦
..........
የልሳን ጸጋ በአግባቡ ከተጠቀምን ጥቁሙን
"በቤተክርስቲያን የቋንቋ ነፃ ስጦታ በአግባቡ ከተጠቀምን" እስከ ማለት ድረስ ያስቻለው በአግባቡ ስላልተጠቀምን ነው።ወደ ጥቅሙ ከመግባቴ በፊት ቤተክርስቲያን ትኩረት ያልሰጠችው ጸጋ ብኖር፣ ራሱን የቻለውን ፦ ልሳንን የመተርጎም ጸጋ ነው።
የመተርጎም ጸጋ ቸል መባሉ እና ትኩረት ማጣቱ ሁሉንም ፦ ተናጋሪዎች ስያደርግ (አድማጭ በማሳጣት ) ፥ ሌሎችን ደግሞ ተደናጋጋሪዎች እንድሆኑ አድርጓል ። የመተርጎም ጸጋ መኖሩ ልፋቅ የማይቻል ትልቁ እውነት ነው፤እውነት እውነት ።ልሳንን የመናገር ጥቅሙን የሚያወሱ ሰዎቹ በዚያ ልክ የመተርጎም ጥቅሙን "በዎፎ-በረሪም" የማይገልጽት ነገር ያስታዝባል፤እንደው ።
በቤተክርስቲያን ልሳንን የመናገር ጸጋ እስካለ ድረስ የመተርጎም ጸጋም አለ፤መኖርም አለበት፤ ቸል መባል የለበትም፤የቃሉ እውነት ነውና። በቤተክርስቲያን የመናገር ጸጋ ኖሮ ፣ የመተርጎም ጸጋ ከሌለ ፣ የልሳን ጸጋ መኖሩ ጥቅም የለውም፤አራት ነጥብ፤እውነት እውነት።ስለዚህ እኔ መናገሩንም ፣መተርጎሙንም በይበልጥ አበረታታለሁ፤ለቤተክርስቲያን ጥቅም ስል።
*የመተርጎም ጸጋ ስኖር መንፈስን የመራመር ጸጋ ይኖራልና ቸል መባል የለበትም ።
ወደ ርዕስ ጉዳዩ ስገባ ፣ በቤተክርስቲያን ልሳንን የመናገር ጥቅሙ እንደሚከተለው ቀርቧል ፦
፨ አምላካችንን ያላመኑ ሰዎቹ በሥራው እንድደነቁ ያደርጋል ሐዋ2 1ቆሮ 14፣
፨ ያላመኑቱ የአምላካችንን ስም ያከብራሉ 1ቆሮ 14፣
፨ የደከመ፣የተከዘ፣ግራ የተጋባው.. አማኝ ይታደሳል ፣
፨ ዓላማው የቤተክርስቲያን መታነጽ ስለሆነ ግቡን ይመታል፤መታነጽ አለ።
*በእርግጥ አንድ ሰው በግሉ ፣ ብቻውን እቤት ከሆነ ፣ለጸጋው ሕግ የለበትም ፤ከመናገርም አይከለከል።በማህበር መካከል ከሆነ ግን መተርጎም ወይንም ማስተርጎም አለበት ፤አልያ ድምፅ ሳያወጣ በውስጥ ይጸልይ ፤ እግዚአብሔር ይሰማልና።እንዲህ ከሆነ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም።
በአግባቡ ካልተጠቀምን ጉዳቱን (በቀጣይ)
...........
በቤተክርስቲያን የልሳን ጸጋ በአግባቡ ካልተጠቀምን ጉዳቱ ፦
የእግዚአብሔርን ቃል እያወቀ ሆን ብሎ በግደለሽነት ሳይተረጉም እና ተርጉመውም ተራ በተራ ካልተናገረ ያ ሰው የእግዚአብሔር ተቃዋሚ እና ስሙን አሰዳብ ፥ ሰንፍ ሰው ነው።ይህም ብቻ ሳይሆን ጸጋው ሳይኖር 'አለኝም' የሚል ሀሰተኛ ነው ፤እንዲህ እንደሆነም እናውቃለን ።
ለማህበሩ ወይም ለቤተክርስቲያን ልሳኑ ሳይተረጎም እና ያለ ስርዓትም የሚነገር ከሆነ ጉዳቱ እነሆ ፦
፨ አንድም ሰው አይጠቀምም ፣አያስተውልም ፣
፨ ቤተክርስቲያንን አትታነጽም ፣ በተቃራኒው ትቆሽሻለች ፤ ውበቷን ታጣለች ማለትም ክርስቶስን ማሳየት አትችልም ፣
፨ ዓላማውን አያሳካም ፣ "ዓላማ ብስም ነው" በራሱ ፣
፨ አንድም እ-አማኝ እግዚአብሔርን አያመሰግንም ፤አሜንም አይልም፤ይልቁንም የእግዚአብሔር ስም ይሰደባል ፣
፨ ለማህበሩ አለመተርጎም በአዕምሮ ሕፃን መሆን ነው፤ አለመብሰልንም ያሳያል ፣
፨ ለማያምኑት ሰዎች ምልክትም መሆን አይችልም ፤ በፍጹም ፣
፨ የማያምን ሰው ፦"ከእነርሱ ጋር እግዚአብሔር እየሰራ ነው! ፤ በመካከላቸውም አለም " አይልም ፣
እያንዳንዷ ነጥብ ከ1ቆሮ ም.14 የወጡት ናቸው።ጸጋው ለቤተክርስቲያን ሳይተረጎም እና ተራ በተራ ካልተነገረ በአጭሩ ከላይ እንደተቀመጠው ነው፤ጉዳቱ እና ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊነቱ ፥ ስለዚህም "የእግዚአብሔር ቃል ራሳችንን እንደ መስታወት እንድንመለከት ይርዳን" ፤ የሚለው ልመናዬ ነው።
“እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ በቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲህ ነው።”— 1ኛ ቆሮንቶስ 14፥33
የልሳኑ መልእክት ስተረጎም ትክክለኛነቱን እንዴት እናውቃለን !? (በቀጣይ)
.........
የልሳኑ መልእክት ስተረጎም ትክክለኛነቱን እንዴት እናውቃለን !?
የመተርጎም ጸጋ ያስፈለገው ተናጋሪው ፥ ለጉባኤው የሚናገረው ቋንቋ ግልጽ ባለመሆኑ እና ተናጋሪው ራሱ የሚናገረውን ስለማያውቅ ነው።እንዲያ ባይሆን ማ ተናጋሪው ራሱ ልሳኑ እንድተረጎምለት መጸለይ ባለስፈለገ ነበር፤ትርጉሙን ካወቀ ለምን ይጸልያል !?። ተናጋሪው ለልሳኑ ስጸልይ ብተረጎም፥ራሱ መልእኩቱን ለጉባኤው ይነግራል ማለት ነው፤ማለትም ሌላ ሰው መተርጎም አያስፈልገውም ። ማለትም ተናጋሪው የመተርጎም ጸጋም አለው ማለት ነው።
"..የመተርጎም ስጦታ ቃል በቃል መልእክቱን የማስተላለፍ የቱርጅማንነት አገልግሎት አይደለም።
...የመተርጎም ስጦታ ያለው ሰው ያንን ቋንቋ አያውቀውም።ጉዳዩ ከመልእክቱ እንጂ ከቋንቋው አይደለም ።ትርጉሙን ያወቀው ቋንቋውን ስላወቀ አይደለም ።.." (መጋቢ ዘላለም መንግሥቱ መንፈስ ቅዱስ እና ካሪዝማዊ ቀውሶች ፤ገጽ 90-91 )
ይህንን በልባችን ይዘን እግዚአብሔር ለልጆቹ የሚናገረውን ፣ ፈቃዱን ፣ ዓሳቡን እና ዓላማውን መጽሐፍ እንደሚል፦ “ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።”— ዮሐንስ 6፥40 ፤በኢየሱስ እንድናምን ነው።
ወደ ርዕስ ጉዳዩ ስገባ አንደኛው እና ዋናው ነገር የመልእክቱን ይዘት ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ፤በመጽሐፍ ቅዱስ መዛኝነት ማስተያየት ነው።ለሥራ በሄድኩባት በአንድት ገጠር ወረዳ ላይ በዓይነ ያየሁትን አክዬ እንድትገነዝቡልኝ ለማድረግ እወዳለሁ ።እንዲህ ነው ፦
መጋቢው ቃለ እግዚአብሔርን ስሰብክ ልቤን ውልቅ እስከሚልልኝ ተማርከ ስምቻለሁ ።በመሃል እያስተማረ በአድስ ልሳን በዜማ አለው።ካለውም በኃላ እንዲህ ስል ተናገረ ፥"ልሳን ለጉባኤው ካልተተረጎመ አይጠቅምምና እኔም ትርጉምን አልውቅም ፣ የመተርጎም ጸጋ ያለው ነቢይ እገሌ ይተረጉማል ፣ ከዛ እናንተም ስምታችሁ አሜን ትላላችሁ" አለ። የተጋበዘውም 'የመተርጎም' ጸጋ ያለው ነብይም ወደ መድረክ መጥቶ ፣ ማይክ ተቀበለ ። እንዲህ ነው አለም ፦"ይህ ከተማ ፣ የወረዳ መቀመጫ እንዳይሆን ፎቶውን ወደ ተለያየ አቅጣጫ አስልከው እያስደገሙ ነው"አለ ፤ ከዛ አሁንም ይቀጥልና ፥ " እግዚአብሔር ግን አይሰራም፤ በተንኩ አለ" አለን።ነብዩ መልእክቱን ነግሮ ወደቦታው ስመለስ ፣ ሕዝቡ ዘለው አሜን አሉ፤በቅጽበት። እኔም ወይጉድ ብዬ መውጫዬን አማትረ መመልከተን ተያያዝኩ ግን አልወጣውም ነበር ወዲያውኑ ።
በዚህ ጹሑፍ ላይ የልሳኑን ተአማንነቱን ሳይሆን ተተረጉመው የተነገረውን ፦ የመልእክቱን ተአማንነት ብቻ እንደሚገመግመው ልብ ይሏል ። ስሁት መሆኑን እንደሚከተለው አቅርቤያለሁ ፦
1ኛ. መልእክቱ በጭራሽ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር አይገናኝም። መልእክቱ ላይ አንድ ቀበሌ የወረዳ መቀመጫ በመሆኗ ፣ ሌላኛዋ ቀበሌ ደግሞ "የወረዳ መቀመጫ ለእኔ ይገባኛል" በማለቷ ፤በተፈጠረው ውዥንብር ፣ እርስበርስ ቀበሌዎችን የሚያጣላ ነበር ።ምክንያቱም የእግዚአብሔር ዓላማ እና ፈቃድ አንድ ቀበሌ ወረዳ ወይም ዞን ወይንም ክልል ወይንም "የዓለም እትን" መቀመጫ ማድረግ አይደለም ።
ሕዝብ በሰዓቱ በዚህ "ይገባኛል" ስሜት ግለው ስላሉ፣ የሕዝቡን ልብ ለማግኘት የተነገረ መልእክት እንደሆነ ግልጽ ነው።እስኪ እንነጋገር እግዚአብሔር የተኛውን ከተማ ነው ለእኛ እየሰራ ያለው !? በምድር ወይም በሰማይ ነው !?
እስክ እንነጋገር አንድ ቀበሌ ወረዳ መቀመጫ መሆኑ እና አለመሆኑ ለጌታችን ምኑ ነው !? መቀመጫ ብሆንስ ለወንጌል ምን ይጠቅማል !? አይደለም የወረዳ መቀመጫ የዓለም የንግድ ከተማ የተባሉቱ እንኳን ለእግዚአብሔር አይደለም ።
ይህ አተረጓጎም ሆን ተብሎ የሁለቱ ቀበሌያትን ሕዝብ በወከባ ለማጣላት ነው።ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ቤተክርስቲያናትን ጭምር ለማጣላት ነው ። ወይንም ለማሸማቀቅ እና እንዳይጠይቁ ለማድረግ ነው፤"የእኛ መለኮታዊ ፈቃድ ነው" በማለት።
በእርግጥ እንደ ኢትዮጵያ ደሃ ለሆንን የመንግሥት ብሮዎቹ መገንባታቸው፣እንዲናድግ መንገድ ልሆን ይችላል ።አዎ።ግን የተኛው እድገት ? የመንፈሳዊ ወይንስ የኢኮኖሚያዊ ? የኢኮኖሚያዊ እድገት ነው።ታድያ ይህ ሕዝቡን አማኝ ያደርጋልን !? በፍጹም ። እስኪ ልጠይቅ ፦ የአፍርካ ሕብረት መቀመጫ አድስ አበባ ነው።ለአድስ አበባ ሕዝብ ምን መንፈሳዊ ፋይዳ አለው !?
2ኛ. አንድ ቀበሌ ወረዳ ወይንም ዞን ወይንም ..ፈደራል መቀመጫ ማድረግ ፖለቲካዊ እንጂ መንፈሳዊ ፋይዳ የለውም።መንግሥት ለራሱ ፖለትካ አገዛዝ የሚመቸውን ያደርጋል ፤ እግዚአብሔርን ግን አይዘበትበትም ።
3ኛ. ይገባኛል ብሎ እንደ መመሪያው ማንም መጠየቅ ይችላል ፤የዜግነት ነው ። ከወንጌል እውነት ጋር አይገናኝም ።
4ኛ. ደግሞ የሀገር "የከተማ ፎቶ ተነስቶ ጠንቋይ ቤት ሄደ" ያለው ነገር ገርሞኛል ።ፍርዱን ለእናንተ ትቻለሁ ።
እንዲህ በልቤ ሰፊነት ፣ የሰዎችን የልብ ትሪታ እየሰሙ ያንን የሚናገሩትን ስሁት ነገር ፦መገለጥ ሳይሆን መገልበጥ እንደሆነ ያስተውሏል።
የልሳን ጸጋ የሌለው በመንፈስ ቅዱስ አልተጠመቀምን !? (በቀጣይ)
............
"" አንድ አማኝ በልሳን ጸጋ ባይናገር በመንፈስ ቅዱስ አልተጠመቀም ማለት እንችላለን !? ""
ወደ ርዕሱ ከመግባቴ በፊት በመንፈስ ቅዱስ ያልተጠመቁቱ በመንፈስ ቅዱስ እንድጠመቁ ፣ስለመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ምንነት አክዬ ማለፍ እወዳለሁ ።
የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት (መነከር) የሚፈፀመው አንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ስያምን፤በቅጽበት ነው።ምንም እንኳን መንፈስ ቅዱስ አምላክ ብሆንም የማጥመቁ ግብር ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ነው።ቃሉ እንደሚል ፦ “...፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ።”— ዮሐንስ 1፥33 ።
አንድ ሰው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አሜነ ማለት ትክክለኛ መረዳት ይዟልም ማለትም ነው።አልያ በአስመሳይ 'መንፈስ' ነው የተጠመቀው። ማለትም ፦
☝ ኢየሱስ ክርስቶስ አብም መንፈስ ቅዱስም አይደለም ፣
☝ የኢየሱስ ክርስቶስ ስጋ የሰው ስጋ ነው፤ያውም የዳዊት ልጅ የእናቱ የማርያም ስጋ ነው ፣
☝ ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉዕ ሰው ፣ ሙሉዕ መለኮት ነው ፣
☝ ኢየሱስ ክርስቶስ ፋጡር አይደለም ፈጣሪ ነው ፣
እንዲህ የማይያምን ሰው በራሱ እንጂ በቃሉ አላመነም፤እምነቱም የሰይጣን እምነት (ሀሰተኛ) ነው።ጥምቀቱም እውነተኛ አይደለም ፤ 'ተጠምቅያለሁ' ብልም ።
ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛ መከራ ተቀብሎ ሞቶ ተነስቶ ማረጉን ፣ ለእኛ ደግሞ ብርቱ ልመና ማቅረቡን የሚክዱ ፦"የእውነት ልመና አይደለም (ምሳሌ ነው) " የሚሉቱም ባለማመናቸው ጠንቅ፣ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ አያጠምቃቸውም፤ 'ተጠምቀናል' ብሉም።
ያመኑቱ እንዲህ ይላሉ ፦"ኀጢአተን ሙሉውን እርሱ ተሸክሞ እኔን ነፃ አደረገኝ፤እኔ የሚሞተውን ሞት ሞቶ፣ ከሞት ነፃ አደረገኝ " ብሎ ያምናሉ፤ማንም እንዲህ ካመነ ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ኃጢአቱን ሸፍኗል ፣ ነፃ አድርጎታል ፤አድናታል ፤ስለዚህም ስለዳነ በመንፈስ ቅዱስ በቅጽበት ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ያጠምቀዋል። መንፈስ ቅዱስም ባመነው ሰው ሕይወት [በመቆጣጠር] መሥራት ይጀምራል ፤ወደ እውነት ሁሉ ይመራልም ።
ጌታም ራሱ ያለማንም እገዛ ፣ብቻውን ፣ መንፈሳዊቷን ፣ አንድቷን ቤተክርስቲያን ብልት በማድረግ ይሰራል ፤ “..፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።”— ማቴዎስ 16፥18 ።እንዳለው፤የቤተክርስቲያን አካል ያደርጋል ።
በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስያምን ፦ ዳግም ተወልዷል ፣ በመንፈስ ተጠምቋል፤በመንፈስ ቁጥጥር ስሪም ይሆናል። ቅዱሱ መንፈስ ባደረበት ሰው ላይ ስጦታን ያድላል 1ቆሮ 12 ። በመንፈስ ቅዱስ ሳይጠመቅ ማንም የክርስቶስ ቤተክርስቲያን አካል አይሆንም፤ምድራዊ 'ቤተክርስቲያን' አባል ብሆን ነው እንጂ።
መንፈስ ቅዱስ ባደረበት ሰው ላይ ስጦታውን ያድላል ፤እንደወደደ።ይህ ስጦታ ከተፈጥሮ ማወቁ ጋር አይገናኝም ።ምክንያቱም የተፈጥሮ ዕውቀት ሰው ስለሆነ ብቻ የሚያውቀው እውቀት ነው፤የአምላክ ባህሪውን ስለተካፈለ።የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ግን መንፈስ ቅዱስ ያለአንዳች መስፈርት ፣ እንዲሁ የሚሰጠው ነው።ይህም ስጦታ ለቤተክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ብቻና ብቻ ነው።
ወደ ርዕሱ ስገባ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን አካል ስኮን በመንፈስ ቅዱስ ይጠመቃል ፤ይሞላልም።ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ መጠመቁ የሚረጋገጠው በቋንቋ ጸጋ ከተናገረ ነው ? በፍጹም አይደለም ።
የልሳን ጸጋ ጸጋ ነው፤ማለትም እንደማንኛውም ጸጋ እግዚአብሔር የሚሰጠው ነው። እንደየ አከባቢው ፣ እግዚአብሔር ለሰዎች መዳን አስፈላጊ እንደሆነ ተመልክቶ ፣ ከመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በኃላ ወዲያውኑ የልሳንን ጸጋ ልሰጥም ፥ ላይሰጥም ይችላል፤ንጉሥ እንደወደደ ነው።
ስለዚህም ከዚህ በመቀጠል "የቋንቋ ስጦታ ማግኘት የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ማረጋገጫው ነው።" ለማለት የሚጠቅሱትን ለማጠን እሞክራለሁ ፤ "በጌታ ያመነ ሁሉ በልሳን መናገር አለበት!!" ለሚለው ፈልጥ ፣ የሚውለውን ክፍል በማጠን እንጀምር ፦
ማርቆስ 16
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁷ ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ፥
¹⁸ የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም፤ እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይድናሉ።
በእርግጥ በዚህ ምንባብ ላይ ያመኑትን "የቋንቋ ስጦታም" እንደሚከተላቸው በሚሳይ መልኩ ቀርቧል፤እውነት ነው።ግን በስጦታዎች ዝርዝር ውስጥ የቀረበው የቋንቋ ስጦታ ብቻ ነው? ወይንስ ተአምራት ማድረግም ተጠቅሶበታል!? ለምን ተአምራት ማድረግንም አይጠቅሱም!? እንደውም ሌላውንም የተዘረዘሩትን ጭምር ለምን አይጠቀስም ?ለምን የቋንቋ ስጦታ ብቻ ? ምክንያቱም ክፍሉ የቋንቋ ስጦታ ብቻ ልከተላቸው እንደሚችል አይናገርምና፤ሁሉንም ጸጋዎችን ያማከለ ነው።
ክፍሉ የሚለውን በእግረ መንገዴ አንድ ልበል ፦ ሰዎቹ በማመናቸው ወንጌልን ይሰብካሉ ፣ እግዚአብሔር ደግሞ ምልክቶቹን እያደረገ ቃሉን ያጸናል ማለት ነው። ነገርግን ሰዎች ምልክት የሚያደርጉትን ሰዎችን ይከተላሉ ማለት አይደለም ። ይህ ክፍል ሁሉንም ጸጋዎችን ያማከለ እና ልከተላቸው እንደሚችል የሚናገር ክፍል ነው፤ አንዷን የቋንቋ ስጦታ ብቻ አያመለክትም ፤ስለዚህም ለራሳቸው ሀሳብ የሚሆነው በመሳግ ማስተማር ልባምነት አይደለም ፤ በፍጹም ።
ሌላው ደግሞ ፦
“ጳውሎስም እጁን በጫነባቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው በልሳኖችም ተናገሩ፥ ትንቢትም ተናገሩ።”
— ሐዋርያት 19፥6
በዚህ ክፍል ላይ በሌሎች ቋንቋዎች መናገራቸውን ብቻ ሳይሆን ትንቢትንም መናገራቸውን ይገልጻል ። ከተጠቀሰ አይቀር ፦ ትንቢት መናገርንም መጠቅስ ነበረበት፤እንደ ቃሉ።
ትኩረቴ ከጸጋዎቹ ነጥለው አንዷን የቋንቋ ጸጋ መናገር ፥ "የመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ ማረጋገጫ ነው" መባሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንዳልሆነ ለማሳየት ነው ፤ ብሎም እግዚአብሔር እንደ ወደደ እንደየ ቦታው እና እንደየ ዘመኑ (ግዜው) ለሰዎች መዳን አስፈላጊ የሆነውን ያደርጋል የሚለውን ለማከልም ነው፤እውነታውም ነውና።
ምክንያቱም የሚንኮራበት ሐዋሪያው ጳውሎስ ከሁሉ አብዝቶ በሌሎች ቋንቋዎች እንደሚናገር ብገልጽም፥ ወዲያውኑ እንዳመነ በልሳን አልተናገረም ፤ባለመናገሩ አላመነም ልንል ነውን ? እንደዚህ አይባል።ቃሉ እንደሚል፦ “ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥”— ገላትያ 1፥15-16 ፤ሐዋ 9 ፤ 26 (ይነበብ )፤ በመንፈስ ተመርቼ ወጣው ያለው ጳውሎስ፥ "በመንፈስ አልተጠመቀም" የሚል ሰው ድንገት ብኖር ያስታዝባል።ጳውሎስ በመንፈስ የተመራው በመንፈስ ስለተጠመቀ ብቻ ነው።በመንፈስ ያልተጠመቀውን መንፈስ ወደ እውነት ሁሉ አይመራምና ። ጳውሎስ ወደ እውነት ተመራ ግን በቅጽበት በሌሎች ቋንቋዎች አልተናገረም፤ግን በአገልግሎት በኃላ መናገሩን ይገልጻል 1ቆሮ 14።
ሌላው ደግሞ ሁላችንም በልባምነታቸው የሚንጠቅሳቸው የቤሪያ ሰዎች በሐዋ 17 ላይ እንደተገለጸው ፣ "በጌታ አመኑ" ፥ግን ማመናቸው እንጂ በቅጽበት በሌሎች ቋንቋዎች እና ጸጋዎች መናገራቸውን መጽሐፍ ቅዱስ አያወሳም፤እና አልተናገሩምና አላመኑም እንላለን ? በፍጹም ።
ምንም እንኳን "በቅዱሱ መንፈስ መጠመቃቸውን የሚያሳየው በቋንቋ ጸጋ መናገር መቻላቸው ነው።" ብሉም ፤ በቋንቋ ጸጋ የሚትጠቀሰዋ የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ግን መንፈስ ቅዱስ ያዘነባት ፣ ስጋዊያን የሆነች ፣ በመንፈስ ያልሞላች ፣ ያልበሰለች፣አዕምሮ እንደ ጎደለ ሰው በሕፃን የተመሰለች ቤተክርስቲያን ናት 1ቆሮ 3።
በመንፈስ ከተጠመቅን ፣ መንፈስ ቅዱስ እለት እለት በራሱ ቁጥጥር ስሪ በማድረግ የማይታየው በሚታየው ሰው ይገለጣል፤ቃሉ እንደሚል አንደ የተጠመቀ ሰው በመንፈስ ቁጥጥር ስሪ ይሆናል ፤ ወደ ፈለገበት ይመራልም ፤ ዮሐ 3 ።መንፈስ ቅዱስ በውስጡ ስላለ የመኖሩ ምልክቱ ፦ የሚታይ የመንፈስ ፍሬ ነው።“የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው።”— ገላትያ 5፥22 ።
ስለዚህ ለቤተክርስቲያን እግዚአብሔር እንደወደደ እንደሚያደርግ ማንም ይወቅ፤ካላወቀ አይታወቅ።
“እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን...፥ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል።”— 1ኛ ቆሮንቶስ 12፥28 ።እንደሚል ፥ደግሞም ፦ “ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸውን? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጉማሉን?”— 1ኛ ቆሮንቶስ 12፥30፤ቃሉ እንደሚል ነው።
ስለዚህም ሁሉም በልሳን አይናገሩም ፤አይተረጎሙም ፤አይፈውሱም..። እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን ሕንፀት በሰጠው ስጦታ ብቻ ያገለግላሉ።እናም ወዳጆቼ ስንፍና አስወግዱ ።
........
እድሉ ዮሐንስ ጋምሳ
(ደቀመዛሙርቱ )
Comments
Post a Comment