ቅዱሳን ንንን
መግቢያ
ከአንዴ ወንዴም ጋር በመልካም መንፈስ በፊት ገጼ ፣በውስጥ መስመር "በጥያቄና መልስ ውይይት" መነጋገር
ጀምርን ። ምንም እንኳን የግል ማንነት ወደ መተዋወቅ ባንሄድም መልካም ውይይት አድርገናል ።ልክ በአካል እንደሚንተዋወቅ
ሰው። ብዙ ዓመት ጓደኛ እንደሆንን ሰዎች። ያለ ምንም ስድብ ፣ንቀት ፣ ሃሳብ አንሸራሽረናል።ይህ ዘመናዊነት ነው።ለዚህ
ጥበባዊ ውይይት አለማመስገን አልችልም ። ለሁላችንም ምሳሌ የሚሆን ነው።ርዕሱ ላይ ብቻ ትኩረት መስጠት ፣
የምናምነው ነገርን በየዋህት መንፈስ ማቅረብ ፣የመቀበልና ያለ መቀበል መብት በማክበር ተወያይተናል ፣ይህ የዘመናዊነት ጥግ
ነው። ስለ መልካም ምልልሳችን አመሰግናለሁ ።ክበርልኝ!
በውይይታችን የቀረበውን ሃሳብ በሁሉም ዘንድ ማንሸራሸር ስለፈለኩ ለሁሉም አጋርቼ ነበር።ቅዱሳን ሁለንም የማወቅ ጸጋ ፣
በሁለም ቦታ የመገኘት ጸጋ አላቸው የሚለውና ፣ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ የሚለውን ቃል ትርጓሜ ፣ የውይይታችን ቁልፍ ነጥብ
ነበር። በዚህም ላይ የብዙዎች እምነት ከእግዚአብሔር ቃል የወጣ እንደሆነ ተመለከትኩ ። ስለሆነም የተቻለኝን ሰፊ ማብራሪያ
ለማቅረብ ወደድኩ።ስለሆነም ከታች በተዘረዘሩት ነጥቦችን ላይ ጹሐፍ የማቀርብ ይሆናል፦
1.አምላክነት ምንድነው !?
2.የቅደሳን ሁለንም የማወቅ ጸጋ !
3.የቅደሳን በሁለ ቦታ የመገኘት ጸጋ !
4. "ጸጋ የሞላብሽ ሆይ " ማለት ምን ማለት ነው !?
4.የቅደሳን ጸሎትን የመስማት ጸጋ !
5.ያረፉ ቅደሳን ስለእኛ ምህረትን ይምናሉ !?
መልካም ምንባብ ይሁን !
ብዙ የሚታተርፉበት ይሁን !
1.አምላክነት ምንድነው !?
ስለ እግዚአብሔር አምላክነት ስናጠና ትልቁ መጽሐፍ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ ..”( ዮሐ 4፥24) ፣ይለናል ።ታዲያ መንፈስ የሆነውን የማይታየውን ፣ የማይጨበጠውን ፣ ረቂቁን አምላክ እንዴት ነው ማወቅም መግለጽም የምንችለው !? መጽሐፍ ስናገር አምላካችን "እኔ" የሚል ማንነት ያለው እንደሆነ ይገልጻል ዘፀ 3።
እግዚአብሔር አምላክ ራሱን "እኔ" ብሎ የሚናገር የሚገልጽ ከሆነ ፣ ባይጨበጥም ባይታይም "አካል" አለው ማለት ነው።አካል ማለት ስም ያለው የምጨበጥ የሚታይ ማንነት ያለው ማለት ብቻ አይደለም ። በእርግጥም ይኼ አንደኛው ትርጓሜው ነው፤ ሁለተኛው ትርጓሜውም ግን "እኔ ማለትም የሚገባ ዕውቀት ቀዋሚነት ላላቸው ለማይሞቱና ለማይጠፉ ለሦስት ብቻ ነው ፤ለአምላክ ፣ለመላአክ፣ለነፍስ ።."[1] ማለትም ነው።
አለቃ ኪዳኔ ወልዴ ክፍሌ እንዳሉት አካል ማለት እኔ ማለት የሚችሉት አምላክ ፣መላእክት ፣ነፍስም ናቸው በማለት ይገልፃሉ ።ስለዚህም አካል ማለት ስሜት ያለው፣ፈቃድ ያለው፣እውቀት ያለው ሆኖ ራሱን "እኔ" ብሎ የሚጠራው ነው ፤ ማለት ነው።
ይህንን በትምህርት ሦስትነት ላይ የኤፌሶን መጽሐፍ በመጠቀስ በአካል ትርጓሜ ባለማወቅ ውዥንብር በመፍጠር ለማምታታት የሚፈልጉ ወገኖች አሉ።እስኪ እንመልከት ፦
“በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤”ኤፌሶን 4፥4
በዚህ ክፍል ላይ አንድ አካል ይላልና ፣ እናንተ ሥላሴአዊያን ደግሞ ሦስት አካል ለአምላክ አለው ከሚለው ትምህርታችሁ ጋር ይጋጫል ይሉናል ።
በእርግጥም አንድ አካል ብሎ ለእግዚአብሔር የሚገለጽ ከሆነ መጀመሪያም እንዳልነው በቁሙ የሚታይ የሚጨበጥ የሚለው የአካል ትርጓሜ ለእግዚአብሔር አይሰራም ።ምክንያቱም እግዚአብሔር መንፈስ ነው።ስለዚህም በሁለተኛው የአካል ትርጓሜ መሠረት እንሄዳለን ማለት ነው።እግዚአብሔር እኔ የሚለው ማንነት አለው።አካል አለው።ይህም ማለት "እኔ" የሚል ማንነት አለው ፣ስሜት አለው፣ፈቃድ አለው፣እውቀት አለው ማለት ነው።
አብም ወልድም መንፈስ ቅዱስም የራሳቸውን እውቀት ፣ስሜት ፣ ፈቃድ አላቸው ።የሦስቱም ግን አንድ ስሜት ፣አንድ ፈቃድ ፣ አንድ እውቀት መኖሩ እግዚአብሔር አንድ ማንነት መኖሩን ያሳየናል፤ሕሳቡ 1*1*1*=1 እንደሚል ነው።(ማንም ሰው ከሦስቱ አካላት አንደኛውን በስማቸው እና በሥራቸው ካልተገለጹ በስተቀር ማወቅ አይችልም ።ምክንያቱም እግዚአብሔር አንድ ነው።መንፈስ ነው።ታዲያ የአምላክ ተፈጥሮ ምንድነው !?)
ሁሉንም ይችላል ፣በሁሉ ቦታም ይገኛል፣ሁሉንም ያውቃል፣ሁሉንም ፈጥሯል ፣ ከሁሉም የበላይ ነው፣ዘላለማዊ ነው፣አካል አለው፣መንፈስ ነው፣ጻድቅ ነው።
ይሄ የአምላክ ተፈጥሮ ነው፤ባህሪይ ነው። እግዚአብሔርን የምናውቀው በዚህ እንጂ እኛ በሰጠናቸው በአምስት ጣቶች ፣በሁለቱ ዓይኖችና ጇሮዎች እንድሁም በሁለቱ እግሮች አይደለም ።ይህ እኛ እግዚአብሔርን ስለማናውቅ ፣ስለማይገባን የሰጠናቸው መገለጫዎች እንጂ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ማንነት ያለው ።
___
[1]አለቃ ኪዳኔ ወልደ ክፍሌ መዝገበ ቃላት፣ገጽ 218
🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱
2. "የቅዱሳን ሁሉንም የማወቅ ጸጋ !"
በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ከማንም ጋር በሚያስማማ ነጥቦች ላይ በሙሉ ልብ በመቀበል እስማማለሁ ።ገና ለገና ከእኔ ውጪ የሆነ ተቋም አባል ነው በማለት በመጽሐፉ ላይ የሚያስማማውን ሳልስማማ አልተውም ።ምን እያልኩ ነው !? እንቀጥል ፦
ቅዱሳን ሁሉንም የማወቅ ጸጋ አላቸው ማለት በራሱ ስሁት ነው።ምክንያቱም ሁሉንም የማወቅ ጸጋ የሚባል ስጦታ የለም።የእግዚአብሔር ገንዘብ ብቻ ነው። እግዚአብሔርም ለማንም አልሰጠም ።ይህንን የኢኦተቤክ መምህር የሆነው ዲ.ያረጋል አበጋዝ እንዲህ በማለት ይገልጻሉ ፦
"የኢኦተቤክ መላእክት ሙሉእ በኩሉሄ ናቸው ብላ አታስተምርም፤ይኸ ከእርሷ ይራቅ! ሁሉ አዋቂነት (ማእመረ ኩሉ) ፣ሁሉን ቻይነት (ከሃሌ ኩሉ) ፣በሁሉ ቦታ መገኘት (ምሉእ በኩሉሄ) ፣ የሚባሉት ነገሮች ለእግዚአብሔር ብቻ የሚነገሩ ፣የእርሱ መገለጫዎች የሆኑ ነገሮች ናቸው እንጂ የፉጡራን ገንዘቦች አይደሉም ።ስለዚህም የኢኦተቤክ መላእክት በሁሉ ቦታ ይገኛሉ ብላ ታስተምራለች ማለት ፍጹም ስህተት ነው።" [1]
ርዕሰ ጉዳያችን ሁሉንም ማወቅ ስለሆነ በእሱ ላይ ትኩረት እናደርጋለን ።እንደ ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ አስተምህሮ ከሆነ ሁሉንም ማወቅ የእግዚአብሔር ተፈጥሮ ነው፤የእርሱ ገንዘብ ብቻ ነው፤ ሌላው ፍጡር ለማንም አላካፈለም ማለት ነው።ምክንያቱም የእግዚአብሔር ብቻ ናቸው ብሏልና።ያ ማለት በስጦታም መልክ ሁሉንም የማወቅ ጸጋ ለማንም አልተሰጠም ማለት ነው።
ሌላም ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ያለውን እንጨምር (ስለቅዱሳን እውቀት ስለማወቅ ከተናገርን አይቀር) ።ያረጋል እንዲህ ይለናል ፦
"ቅዱሳን.. እርሱ የገለጠላቸው ያህል ልያውቁ ይችላሉ እንላለን እንጂ ቅዱሳን ከሞቱ በኃላ በምድር ላይ የሚሰራውን ሁሉንም አንድ ባንድ ያውቃሉ አንልም ።"[2]
እንደዚህ መምህር አስተምህሮ ከሆነ እግዚአብሔር ከገለጠ ያውቃሉ ፣ ካልገለጠ አያውቁም ማለት ነው። ሁሉንም የማወቅ ጸጋ አላቸው የሚባለውም ስህተት ነው።ቅዱሳን በየትኛውም ቦታ ብሆኑ ጌታ መግለጥ ከፈለገ እንደሚገለጥና እንደሚጠቀም እንጂ ሁሉንም የማወቅ ጸጋ አላቸው የምል ትምህርት በኢኦተቤክም የለም ማለት ነው።ከመሠረቱ ጌታ ከገለጠ ፣መሥራት ከፈለገ የሚቃወመው ማን ነው !? ማንም ።ስለዚህም ሁሉንም የማወቅ ጸጋ የሚባል ጸጋም የለም ፣ቅዱሳንም ሁሉንም ያውቃሉ ማለቱ በራሱ ስህተት ነው።እያልኩ ወደ ማስተባቢያ ነጥቦች እመለሳለሁ ።
መጀመሪያ በውስጡ መስመር ስንነጋገር Orthodox Apologetic ያለኝን እነሆ ፦
"ድንግል ማርያም ሁሉን የማወቅ ጸጋ አላት ብላ ቤተክርስቲያን ታምናለች ታስተምራለች። ሆኖም ግን ድንግል ማርያም ሁሉን የማወቅ ጸጋ አላት ማለት ሌሎች ቅዱሳን ሁሉን የማወቅ ጸጋ የላቸውም ማለት አይደለም። "
ደግሞም ሁሉንም የማወቅ ጸጋ
ምንድነው!? ብል ስያብራራ ፦
"ሁሉን የማወቅ ጸጋ ማለት በሌላ አገላለጽ ሁሉን የማወቅ የስጦታ ብቃት ማለት ነው።" አለኝ።
ስለዚህም ከዚህ ሃሳብ ተነስቼ ልክ እንደ እግዚአብሔር ሁሉንም የማወቅ ብቃት ለቅዱሳን አላቸው ብሎ ያምናል ብል ስህተት ምኑ ነው !? ለማነኛውም ለማስተባበል የተሰጠውን ነጥብ ይዤ ፣እንደ ታረመ በመቁጠር ወደ ርዕሰ ጉዳይ አልፋለሁ ።(ዋናው መቀየር ነውና )
ቅዱሳን የአምላክ ብቸኛው ገንዘቡ የሆነውን ሁሉንም አዋቂነት ተካፋይ ሆኖዋል ያለኝ ወዳጄ አሁን ደግሞ ፦
"የቅዱሳን ሁሉ አዋቂነት ገደብ አለው በማለት ገደቡም ስለእኛ ጸሎት እና ሰለ ምድራዊ ድርግታችን ነው " የሚል ማስተባበያ አስቀምጧል ።ዞር አሉ ነው ነገሩ።ምክንያቱም ፦
<< ስለእኛ ጸሎት ካወቁ ፣
ስለእኛ ምድራዊ ድርግታችን ካወቁ፣ >>
#1.ምንድነው የማያውቁት !?
#2.ይህንን ያወቁት እግዚአብሔር ስገልጽ ስገልጽ ነው ወይስ አንዴ እንዲያዉቁ ብሎ የሰጣቸው ጸጋ ሰለሆነ ነው !?
#3.ሌላው ደግሞ ስለእኛ ጸሎት ስባል በተለያየ ቦታ ያሉት ሰዎችን የሚያጠቃልል ነው (ብዬ አስባለሁ)። በተለያየ አለም ክፍል ሆነው የሚጸልዩት ያውቃሉ !? ወደ እነሱ የተደረገውን ጸሎት ነው ወይስ ወደ እግዚአብሔር ቀጥታ የተደረገውን ጸሎት ነው የሚያውቁት !?(እንደ እምነታችሁ ) ፣
#4.ስለእኛ ጸሎት ያውቃሉ ስባል የጸሎታችን ይዘት ሙሉ ያውቃሉ ማለት ነው !? ስንናገር ወይም ሳንናገርም በልባችን ብንጸልይም ሁለም ያውቃሉ !?
#5.በልባችን ስንጸልይ የሁላችንን ጸሎት ካወቁ ከሰሙ ፣ ቅዱሳን እንደ እግዚአብሔር የሁሉንም ልብ ያውቃሉ !?
#6.በአፋችን እየተናገርን ስንጸልይ ድምጻችንን ከሰሙ ፣ የመስማታቸው ጥቅም ለእኛ ምንድነው !?ስለ እኛ ጸሎት ማወቃቸው ለእኛ ሕይወት ምን ይጠቅማል !? ያውቃሉ ማለታችንንስ ምን ይፈይዳል !?
#7.ያረፉ ቅዱሳን ለኀጥአን ምህረትን ይለምናሉ !?
___
[1]መድሎተ ጽድቅ ቅጽ 1፣ገጽ 38
[2]ዝኒከማሁ ገጽ 314
🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱
3.የቅዱሳን በሁሉ ቦታ የመገኘት ጸጋ !
<<..የሞቱ የቅዱሳን መናፍስት መንፈስ ስለሆኑ በቦታ እንደማይገደበ እሙን ስለሆነ በሁሉም ቦታ የመገኘት(ሁሉን የማወቅ) የጸጋ ብቃት እንዳላቸው ሲታወቅ ድንግል ማርያም ግን ሰውነቷ ከነብሷ ጋር እያለ ውስኑ ማንነቷ ወይም ስጋዋ ሳይገድባት ሁሉንም ማወቋ ወይም በሁሉም ቦታ መገኘቷ ከአእምሮ በላይ ስለሆነ ቤተክርስቲያን በዚህ ነገር ተደንቃለች። >> Orthodox Apologetic
የንግግራችን ዋና ነገር ይኼ ነው። ሃሳቡን ሳደራጅ ተመልከቱ ፦
የሞቱ ቅዱሳን መንፈስ ናቸው፣
መንፈስ ደግሞ በቦታ አይገደብም፣
ስለዚህም የሞቱ ሰዎች በሁሉም ቦታ ይገኛሉ።
(ድንግል ማርያም ግን ከእነ ሰውነቷ መንፈስ ብቻ ሳትሆንም በሁሉም ቦታ ትገኛለች የሚል ነው።ይሄ ነው የኢኦተቤክ አስተምህሮ ነው፣ ተብሎ የቀረበልኝ።)
በሁሉም ቦታ መገኘት ማለት በአንደ ከአንድ በላይ ቦታ መገኘት (የሌሉበት ቦታ የለም )ማለት ነው።በዚህ ላይ የኢኦተቤክ ምን ብላ ታስተምራለች የሚለውን እንመልከት ፦
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቂ የዕብራውያን ድርሳን ስተረጉመው እንዲህ አለ ፦
"ወልድ በተላከ ግዜ እንደ መላእክት ቦታውን ለቆ የሄደ አይደለም ፤መላእክት ስላኩ የነበሩበትን ቦታ ለቀው ይሄዳሉ ፣ወደ ተላኩበት ስፍራ ይደርሳሉ ።"[1]
በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቂ ትርጓሜ መሠረት አይደለም ሰው ፣ መላእክት እንኳን ስፈጠሩ መንፈስ የሆኑቱ ፣በአንደ በሁሉም ቦታ መገኘት ቀርቶ በሁለት ቦታም አይገኙም የሚል ነው።ይገርማል አባ መዓዛ በየኔታ ሚዲያ ቀርበው "በኢኦተቤክ ትምህርት የምቆጣጠር አካል የለም "ማለታቸው ትክክል ነው። ይኼ ትምህርት ራሱ በብዙዎች ልብ እንደተተከለ እኔው ራሴ አረጋግጫለሁ ።
ሌላ ማስረጃም እንጨምር ።ምክንያቱም የኢኦተቤክ ትምህርት ሳያውቁ እናውቃለን ፣መልስ እንሰጣለን ፣የእኔ ትክክል ነው ከማለት በፊት መማር ይቅደም። (ምንም ትክክለኛ ትምህርት ይሁን አይሁን እሱ ሌላ ነገር ነው ፣ግን መማር ይቅደም)። ትምህርት ዘር ነው። አዕምሮ የመቆጣጠር አቅም አለው፤የራሱ መንፈስ አለው።መጠንቀቁ ግን አይከፋምና ።ሌላ ማስረጃ ጨምረን እንመልከት ፦
የኢኦተቤክ መምህር ያረጋል አበጋዝ እንዲህ ይለናል ፦
"..እንደ እግዚአብሔር በሁሉ ስፍራ ትገኛለች ..የምል እምነት ሆነ አስተምህሮ የለም፤ በሁሉ ስፍራ መገኘት (ሙሉዕ በኩለሄነት) እና ሁሉን አዋቂነት .. የእግዚአብሔር የባህሪው ገንዘቡ ብቻ ነው " [2]
እንደ መምህር ያረጋል አበጋዝ በሁሉ ስፍራ መገኘት የእግዚአብሔር ባህሪ ብቻ ነው።አስተውሉ።ባህሪ ማለት ተፈጥሮ ማለት ነው።ስለዚህም የእግዚአብሔር ተፈጥሮ ብቻ ነው ማለት ፣ሌላ ለማንም አላካፈለም ማለትም በሁሉ ቦታ ወይም በአንደ ሁለት ቦታ የመገኘት 'ጸጋ' ሌላ ለማንም አልሰጠም ማለት ነው።የእግዚአብሔር ብቻ ነው።ልክ መፍጠር ።
ከመሠረቱ በሬ ወለደ የሆነ፣ አይንን በጨው ያጠበ ኑፋቄ እንጂ በሁሉ ቦታ የመገኘት የምባል ጸጋ የለም። እግዚአብሔር ብቻ ነው የሌለበት ስፍራ የሌለው ።ሃሌ ሉያ።ለዚህም ነው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቂ ወልድ ራሱ አምላክ ስለሆነ ፣ ወደ ድንግል ማርያም ማህፀን ስመጣ ፣ የመጀመሪያው ቦታውን አልለቀቀም ያለው ።ይህ ድንቅ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዘው መላእክት በሁሉም ቦታ ይገኛሉ ብሎኝ ነበር።"ማስረጃ!?" ስለው ፣ መላእክት መንፈስ ናቸው ስለዚህም በሁሉም ቦታ ይገኛሉ ብሎ መለሰልኝ ።በዚህ አረዳድ መሠረት መንፈስ ማለት በቦታ የማይገደብ በሁሉም ቦታ የሞላ ነው ማለት ነው። ያሳዝናል ።
*መንፈስ ማለት የማይታይ የማይጨበጥ ረቂቅ ማለት ነው [3] እንጂ በሁሉም ስፍራ መገኘት ማለት አይደለም ።' መንፈስ ማለት በሁሉ ቦታ መገኘት ነው ብዬ ብተረጉመው ምን ችግር አለው' የሚል መልስ ማቅረብ ለራስ ነፍስ አለማዘን ነው።በራስ ላይ መጨከን ነው።የእኛ ውይይታችን ወደ ማደግ ሳይሆን ስለእኛ ነጥባችን መጨነቅ የሚወስድ ከሆነ መጨረሻው ጥፋት ነው።እግዚአብሔር በሃሰት ትምህርት አይከብርበትም።ለዚያም ነው ቃሉ “ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ፥ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና።”
— ያዕቆብ 3፥1
ልትቀበል ብትወድ እውነቱ ቀርቧል!
(እግዚአብሔር ይርዳችሁ በዚህ ድንዛዜ ያላችሁ )
~
[1]ዮሐንስ አፈወርቂ እ.ድርሳን 3፣ቁ 155-156
[2]መድሎተ ጽድቅ ቅጽ 1፣ገጽ 38
[3]የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ 39
🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱
4. "ጸጋ የሞላሽ ሆይ " ምን ማለት ይሁን!?
በዚህ ቃል ላይ በውይይታችን ላይ ወንድሜ ያቀረበውን ትርጎሜ " አያስከድም" በማለት ምክንያታዊ ሃሳብ ብቻ በማቅረብ ትርጓሜው ስሁት መሆኑን ለማሳየት ጥረት አድርግያለሁ።ግን ክፍሉን አላብራራውም ነበር።ልበ ሰፊዎቹም ጠይቀውኛል ቃሉን ማብራራት ነበረብክ በማለት።የእኔም ትኩረት የOrthodox Apologetic ትርጓሜ እንደማያስከድ ማሳየት ነበረና እንደተሳካልኝ ተገናዝብያለሁ።እስኪ እኛም የተሻለ ለመረዳት ወንድሜ ያቀረበው ሃሳብ ለማስታወስ ብቻ እንያ ፦
<< ..ስለዚህ በቀላሉ በጥቂቱ ሐዋርያት ያለቸው ጸጋ በሙሉ ከድንግል ማርያም ይገኛል። ድንግል ማርያም ያላት ጸጋ በሙሉ ግን ከሐዋርያት አይገኝም ማለት ነው። የማርያም ጸጋ ይኼ ይኼ ነው ተብሎ ሊዘረዘር አይችልም። ጌታ በሙልአት ደረጃ ነው ስጦታውን #ሙሉ የሰጣት። የድንግል ማርያም ጸጋ ሙሉ ነው። ሁሉም የጸጋ አይነት በአይነቱ ከድንግል ማርያም ይገኛል። ..>> አለኝ
ይኸው ትርጓሜ አያሳከድም ብዬ አንድ ሁለት ብዬ ነበር ።ለማስታወስ ያክል ፦
" ሁሉም ጸጋ ካላት ፣ አንዳች የላትም የሚባል ጸጋ ከሌላት ፣ ልክ እንደሌሎቹ ሰዎች ከ120 ሰዎች መካከል አንደኛዋ ሆና ለምንስ ጸጋን ተቀበለች !? (ቃሉ እንደሚል ሐዋ 2 ላይ እያንዳንዱ ልዩ ልዩ የልሳን ጸጋ ተቀብሎአልና )። ሌላው ያነሳሁት ነጥብ ደግሞ ፦
“ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤”(1ኛ ቆሮንቶስ 12፥10 ) ፣በዚህ ቃል መሠረት አንድ ሰው ሁሉም ጸጋዎች አሉት ማለት አይቻልም የሚል ሃሳብ አንስቼ ነበር።ያው መልሱ ለማርያም ይህ ቃል እንደማይሰራ ነበር የተገለጸው።
[[ይህንን በልባችን ይዘን በእውነት "ጸጋ የሞላብሽ ሆይ" ማለት ሁሉም ጸጋ አላት ማለት ነውን !? ሁሉንም ታውቃለች ማለት ነውን !? በሁሉ ብታ ትገኛለች ማለት ነውን !? የሚለውን እናያለን ።]]
"ጸጋ ማለት "ካሪስ" የሚለው የግርክ ቃል የሚተረጉም ሲሆን፣3 የዕብራይስጥ ቃላትን ሃሳብ ይይዛል፤ እነርሱም ሞገስ ፣ፍቅር እና ቸርነት (ምህረት ) በተሰኙት የአማርኛ ቃል ይተረጎማል ።" [1]
በዚህ ትርጓሜ መሠረት ጸጋ ማለት ሞገስ፣ፍቅር፣ቸርነት ወይም ምህረት ማለት ነው።ሌላም መዝገበ ቃላትን እንጨምር ፦
"ጸጋ ማለት በቁሙ ፤ሃብት፤መልካም ፤ስጦታ፤ዕድል ፤ፈንታ ፤ትምርት፤ስርየት ፤ይቅርታ ፤ብዕል ክብር፤ሕዋስ፤ሞገስ፤የቸርነት ሥራ፤አለዋጋ የሚሰጥና የሚደረግ። " [2]
ስለቃሉ ትርጓሜ እንዲህ ካልን አሁን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንገባለን ፦
“መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ፦ ደስ ይበልሽ፥ #ጸጋ_የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት።” ሉቃስ 1፥28
ይህንን ቃል በደንብ ለመረዳት "ጸጋ የሞላብሽ ሆይ" የሚለውን ቃል ከመጀመሪያው ቋንቋ ቃል ጋር እናስተያያለን።በእንግሊዝኛው ትርጓሜው (K.James )፦
“And the angel came in unto her, and said, Hail, thou that art #highly_favoured, the Lord is with thee: blessed art thou among women.” Luke 1:28 (KJV)
አሁንም የበለጠ ግልጽ እንድሆን ይህንን ቃል ከbible strong dictionary በግሪኩ እናያለን ፦ χαριτόω የሚል ቃል ሲሆን አነባቡ khar-ee-to'-o የሚል ነው።ትርጓሜው charitóō ማለት ነው።ካሪቶ ማለት እጅግ በጣም ልዩ የሆነ መቀበልን መወደድን የሚያመለክት ነው ።( Make Accepted (በልዩነት መቀበል) ,be Highly favoured (በልዩ መወደድ መወደድ ማለት ነው።) ከሌሎች ክፍሎች አገባብ ጋር እንመልከት (" khar-ee-to'-o " ግን በአድስ ኪዳን በሁለት ቦታ ብቻ ይገኛል ) ፦
“To the praise of the glory of his #grace, wherein he hath made us #accepted in the beloved.”Ephesians 1:6 (KJV)
*በዚህ ክፍል ላይ khar-ee-to'-o Accepted ተብሎ ተተርጉሟል ።እግዚአብሔር በልዩ አቀባበል በልጁ እንደተቀበለን ለመግለጽ ።ልዩ መውደዱን የሚያሳይ ነው።
*ስለዚህም መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ማርያምን "ጸጋ የሞላብሽ ሆይ" ስል ማርያም ላይ የሐዋርያነት ጸጋ ፣የነቢይነት ጸጋ ፣የፈውስ ጸጋ ፣የልሳን ጸጋ፣ የአስተማሪነት ጸጋ ፣እውቀትን የመግለጽ ጸጋ ..ወዘተ አለ እያለ ሳይሆን ፣ በልዩ መወደድ ተወደሻል እያላት ነው።ለዚያውም ነው መደበኛ ትርጉም ላይ ቃሉን በቀጥታ "እጅግ የተወደድሽ ሆይ" ብለው የተረጓሙት።
*ስለዚህም እጅግ በጣም መወደድ ፣ ሁሉንም ማወቅ ፣በሁሉ ቦታ መገኘት ወይም ልዩ ልዩ የአገልግሎት ጸጋ አላት አያስብልም ።ምክንያቱም እኛም በዚያ ልክ ተወደናል " khar-ee-to'-o/ ካሪቶ/" ሆነናል።ደግሞም ለማርያም ሐዋሪያነት ጸጋ አላት ብሎ ማቅረቡ ያሳዝናል ።ኢየሱስ የሴት ሐዋርያ አልሾመም 13 ኛ ሐዋሪያ አልመረጠምና ስሁት ነው።ሐዋርያነት ትንብትን መናገር ወይም ልሳን መናገር ወይም መፈወስ ማለት አይደለም ።ሐዋሪያነት ሹመት ነው።ራሱን የቻለ ጥሪ ነው።
ልትቀበል/ሉ/ ብትወዱ እውነቱ ቀርቧል፣
(መቁፈር መልካም ነው)
______
[1] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ 265
[2] አለቃ ኪዳና ወልደ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ 743
በቀጣይ 'ቅዱሳን ጸሎትን የመስማት ጸጋ' ዶግ ዘጭ አመድ ይሆናል !
5. 'የቅዱሳን ጸሎትን የመስማት ጸጋ ! '
በዚህ ክፍል ላይ ያረፉ ቅዱሳን በምድር ሆነው ወደ እነርሱ የሚጸልዩትን ፣በእነሱ ስም ወደ እነርሱ የሚደረገውን ጸሎት ይሰማሉ ለሚለው በቂ የካበተ የመጽሐፍ ቅዱሳዊ መልስ እሰጣለሁ ።በመጀመሪያ ቅዱሳን የእኛን ጸሎት ይሰማሉ ለማለት የሚጠቀሰውን እንመልከት ፧
“ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን።”2ኛ ጴጥሮስ 1፥4
*Orthodox Apologetic ገጽ ልጅ ፣ይህንን ክፍል ስያብራራ የመለኮት ባሕርይ ተካፋይ መሆን ማለት የእግዚአብሔር ባሕርይ ተካፋይ መሆን ማለት ነው፤ እሱም ሁሉንም ማወቅ ፣በሁሉ ቦታ መገኘት፣ጸሎት መስማት .. በማለት ይተረጉማል ።ይህንን ክፍል "ቅዱሳን አማልክት ናቸው" ብሎ እንደ ቃል እምነት ኑፋቄአዊያን መተርጎሙ አስገርሞኛል ።በዚህ ከተቀጠለ "ቅዱሳን ይፈጥራሉ" የሚል የሚመጣ ይመስለኛል ።
እኛ እስኪ እንደ ባለ አዕምሮ ሰው የክፍሉን አውድ ጠብቀን እንተረጉመው ፦
#በቁ.3 ላይ “የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ #ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።”2ኛ ጴጥሮስ 1፥2-3
የመለኮት ኀይል በገዛ ኃይሉና በጎነቱ ጠርቶናል ፣
ለምን !? እርሱን እንድናውቅ ፣በማወቃችንም ሕይወትና እውነተኛ መንፈሳዊነት እንድኖረን ራሱ በመስጠት ። አስምርበት እርሱ የሰጠንን።ስለዚህም የመለኮት ባሕርይ የሰጠን እርሱን እንድናውቅና በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት እንድመስል ነው።
#ቁ.4 ላይ “ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን።”2ኛ ጴጥሮስ 1፥4
ከክፉ ምኛት አምልጣችሁ ፣ከዓለም ጥፋት (ዓለማዊነትም) አምልጣችሁ እንትድትሆኑ የመለኮት ባሕርይ ተካፋይ ሆናችኋል ።የክፍሉ አውድ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው።ጻድቅ ነው።ከኀጢአት ጋር አይተባበርም ።እናንተም በእርሱ ጥሪ ፣ይህንን ባህሪውን ተካፋይ ሆናችኋል የሚል ነው እንጂ እንደ እግዚአብሔር 'አምላክ /ልክት/ ሆናችኋል' የሚል በፍጹም አይደለም ።ደግሞም ሰው በሁሉ ቦታ ይገኛል ፣ሁሉንም ይሰማል ፣ ሁሉንም ያውቃል የሚልም አይደለም (ይህ የእግዚአብሔር ብቻ የሆነ ገንዘቡ ነው።)
ይህንን እንደዚህ ካስተዋልን ወደ ሌላኛው 'ድጋፍ ነጥብ 'እንሻገር።ቅዱሳን ሁሉንም ይሰማሉ ለማለት የሚጠቀሰውን እንመልከት ፦
"በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ #ፍጥረት_ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ #ሁሉ። በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ #ለበጉም_ይሁን_ሲሉ_ሰማሁ።" (የዮሐንስ ራእይ 5:13)
ይህንን ክፍል በመጥቀስ ፦" ስለዚህ በጸጋ ቅዱሳን ልክ ሐዋሪያው ዮሐንስ ፍጥረትን ሁሉ እንደሰማው፥ እነሱም #ጸልዩልን የሚሏቸውን ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ጸጋ ሁሉንም በአንድ ግዜ ሊሰሙ ይችላሉ። ምክንያቱም ራዕይን ከጌታ መቀበል ጸጋ ነውና። " (በዚህ ደግሞ አንጋፋዋ ማርያም ናት ይላሉ)
*ይህ ክፍል ያረፉ ቅዱሳን ፣በምድር በተለያየ ቦታ ሆነው ፣ ወደ እነርሱ የሚንጋጠጡትን ሰዎችን ልመና ይሰማሉ ለማለት የሚጠቀስ ነው።ግን አያስኬድም ።እንመልከት ፦
#1.በዚህ ክፍል ላይ ዮሐንስ ይመለከታል "አየሁ" ይለናል ።“በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከልም በሽማግሌዎችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ፥ ..።”(ራእይ 5፥6) ፣ የተመለከተው እነማንን ነው !? ዙፋኑን ፣አራቱ እንስሶች(ፍጥረታት በሙሉ)
ሽማግሌዎች( ቅዱሳን) ።በእነዚህ መካከል ኢየሱስን ቆሞ ይመለከታል ።አስተውሉ። ይህንን ክፍል በመጥቀስ ያረፉ ሰዎች በምድር ላይ ያለውን ያውቃል ፣ይሰማሉ ማለት ያስኬዳልን !? ሁሉም ነገር ሰማያዊ ነው።ያሉትም ሁሉ በሰማይ ናቸው ።ስለዚህም ዮሐንስ የተመለከተው በምድር ያሉትን ስላልሆነ ውድቅ ይሆናል ።
#2.ዮሐንስ ራዕይን ስመለከት ለራሱ ካረፉ ቅዱሳን መካከል አይደለም ።እሱ ያለው በሕይወቴ ሥጋ ነው።ስለዚህም ያረፉ ቅዱሳን ይሰማሉ ለማለት ክፍሉ አይጋብዝም።
#3.በዚህ ክፍል ላይ ሰዎች ሁል ግዜ ፣ወዳረፉ ሰዎች የሚደረግ ልመና ይሰማሉ ለማለት በፍጹም አያስኬድም ። ምክንያቱም ይህ አንድ ግዜ ግልጠት ነው።ዮሐንስ ራዕይን መመልከት ስያቆም የሚቆም ነው።
#4.ዮሐንስ የተመለከተው እና የሰማው ወደ ዮሐንስ የተደረገው ልመናና ጸሎት አይደለም ።ዮሐንስ በግልጠት የተመለከተው ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን ውዳሴ ነው።
#5.በዚህ ክፍል ዮሐንስ "ያረፈ ቅዱስ" አይደለም ፣የሚናገሩቱም በምድር ያሉት አይደሉምና በፍጹም አያስኬድም እንላለን ።
#6.ከተናገርነው ዋናው ነገር ይኸው ነው ፦ጸሎት ኢየሱስ እንዳስተማረን ወደ አባት ነው ማቴ 6።ወደ ሰዎች ጸሎት ማድረግን አላስተማረም ስለዚህም አናውቅም፤አናደርግም ።
*ስለዚህም በመጀመሪያ ጸሎት ወደ አባት ነው፣ስቀጥል ወደ ፋጡር ጸሎት አይደረግም ።ብደረግም የግል እምነት እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም ።ወደ ፉጡር የሚጸልዩት ሁሉም ወደ ጋናም ይገባሉ ።ከሕይወት ጎድለዋልና። ሕይወትን አላወቁምና። መጨረሻ ጥርስ ማፏጨት ነው።
ከአምልኮተ ባእድ ተጠበቁ!
6. ያረፉ ቅዱሳን ስለእኛ ምህረትን ይለምናሉ !?
በእውነት በሞኝ ጥያቄ ጀመርኩ።የስንፍና ትምህርት ለመተቸት ነውና።ያረፉ ቅዱሳን ስለእኛ ይጸልያሉ ለማለት የሚጠቅሷቸውን እየጠቀስን ሙግት እያቀረብን እናያለን ።
“አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ።”ራእይ 6፥9
ቅ/ዮሐንስ በግፍ የሞቱትን ፣ ስለስሙ መከራ ተቀብለው የተሰዉትን ነፍሳት ተመልክቷል።መመልከት ብቻ ሳይሆን የምሉቱን ጭምር በራዕይ ስምቷል።ቃሉ “በታላቅ ድምፅም እየጮኹ፦ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ።” (ራእይ 6፥10 )፣እንደሚል ነው።
ስለዚህም በዚህ ላይ ትምህርት ስያዋቅሩ ፣ያረፉ ሰዎች ሁሉንም ያውቃሉ ፣በሁሉም ቦታ ያለውን ይሰማሉ፣በሁሉም ይገኛሉ ፣የሁሉንም ጸሎት ይሰማሉ የሚል ነው።ሌሎችን ነጥቦች በቀደም ስላየን በዚህ ላይ ልዩ ትኩረት የምናደርገው "ቅዱሳን ስለእኛ ይጸልያሉ" ለሚለው መልስ ለመስጠት ይሆናል ።
የክፍሉ አሁድ የሚለውን በጥንቃቄ እየተመለከትን ፣ የቃሉን እውነት የምንገልጠው ይሆናል ።ተመልከቱ ፦
#1. በራዕይ 6፥10 እንደተገለጸው ለኀጥአኑ የሚገባቸው የዘላለም ስቃይ እንድደረግ ፣ በእግዚአብሔር ፊት እንድንቆም ፍትህ ይጠይቃሉ ።ምክንያቱም ፦
#2.ብዙ ግዜ ያረፉ ቅዱሳን አዛኝ ፣ የሚጸልዩልን ፣ምህረትን የሚያሰጡ አድርገን እናስባለን ።ነገሩ ወዲህ ነው።ቅዱሳን ከመሞታቸው በፊት ይቅርታን እንደሚለምኑ እንጂ ካረፉ በኃላ እንደሚጸልዩልን ምንም ማረጋገጫ የለም።
እንድሁም በዚህ ክፍል ላይ ሰማዕታት ሁሉ ፣ በአንድነት እግዚአብሔርን ፍረድልን ፣በምድር በሚኖሩት ላይ ፍረድ እያሉ ነው።ነገሩ ተቃራኒ ነው።ቅዱሳን አይደለም ለኀጢአተኛ መለመን ይቅርና ፣ቶሎ የዘላለም ስቃይ እንድደርስ ይለምናሉ፤ይጮሃሉ።ምህረትን አይለምኑም ፍርዶን እንጂ።
#3.ያረፉቱ ቅዱሳን በምድር ላይ ያለውን ሁሉንም ነገር ያውቃሉ የሚሉ ሰዎች ፣የቅዱሳን ማወቃቸው ጥቅሙ ምን ይሁን !? እነሱ የሚጮኹት ስለ ፍርድ ነው፤ ስለበቀል ነው። ቅዱሳን ምህረትን አይለምኑም የእግዚአብሔርን ፍትህን ይጠይቃሉ እንጂ።
#4.ቅዱሳን እግዚአብሔር ስፈርድ ቁጣውን ስያወርድ እልል ይላሉ እንጂ ምህረት ለኀጥአኑ አይለምኑም።ሌላ ማስረጃ ብንጨምር ፦
“ከአራቱም እንስሶች አንዱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ የሚኖር የእግዚአብሔር ቍጣ የሞላባቸውን ሰባት የወርቅ ጽዋዎች ለሰባቱ መላእክት ሰጣቸው።”ራእይ 15፥7
አራቱ እንስሶች ስባል በራዕይ መጽሐፍ ፍጥረታትን ሁሉንም ያመለክታል ፥በዚህ ክፍል ላይ ግን "አንዱ"እንደሚል ከፍጥረታት አንዱን ወካይን የሚያመለክት ነው ። (ከፍጥረታት አንዱ ተወክሎ እግዚአብሔር ቁጣውን እንድያደርግ እንደተስማሙ ያመለክታል ።)
ሌላም እንጨምር ፦ “ሦስተኛውም ጽዋውን በወንዞችና በውኃ ምንጮች ውስጥ አፈሰሰ፤ እነርሱም ደም ሆኑ።”(ራእይ 16፥4) ፣በተፈጥሮ ሃብት ፣በውሃ መመረዝ የማያምኑቱ ይሞታሉ!።
#ጌታ እንዲህ በመፍረዱ ቅዱሳን ፍጥረታት እንዲህ ይላሉ ፦ ራእይ 16
⁵ የውኃውም መልአክ፦ ያለህና የነበርህ ጌታ ሆይ፥ ቅዱስ ሆይ፥ እንዲህ ስለፈረድህ ጻድቅ ነህ፤
⁶ የቅዱሳንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ ደምን ደግሞ አጠጥተሃቸዋል፥ የሚገባቸው ነውና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።
⁷ ከመሰዊያውም፦ አዎን፥ ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፥ #ፍርዶችህ_እውነትና_ጽድቅ_ናቸው ብሎ ሲናገር ሰማሁ።
(ቅድምም ፍረድልን እንደሚሉ ፍትህን እንደሚጠይቁ ፣እግዚአብሔር በኀጢአተኛው ስፈርድ ቅዱሳን ሁሉ "ይገባቸዋል" ብለው ይደሰታሉ በእግዚአብሔር ፍትህ፤የሚቃወሙ አዛኝ አዛኝ የሚጫወት ፣የሚለምን የለም)
🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱
እድሉ ዮሐንስ ጋምሳ
(ደቀመዛሙርቱ )
Comments
Post a Comment