ክርስቶስ ሁለት ልደት አለው !?
ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ልደት አለውን !?
#ኢየሱስ ክርስቶስን ተዋህዶች "ሁለት ልደት አለው ብለው" ያስተምራሉ ፤""ቅድመዓለም ከአብ ያለእናት ድኅረ ዓለም ከድንግል ካለአባት ከድንግል የተወለደው ነው። "" በማለት ። ቅብአት የሚባሉት ደግሞ ሦስት ልደት ነው ይላሉ ፣ በሁለት ልደት ዕሳቤ ላይ ፣ " አብ ከድንግል ማርያም ማኅጸን በሥጋ ወለደው " ይህንን ሃሳብ በመጨመር ያምናሉ ።
የቅብአቶች አስተምህሮ በግልጽ ውድቅ የሆነ ስለሆነ ትኩረቴን በተዋህዶች አስተምህሮ ላይ አደርጋለሁ ።በተዋህዶች አስተምህሮ ላይ በስፋት የሚያትተው ሃይማኖት አበው መጽሐፍ ነው፤ከቀደምት አባቶች።
ይህንን የሚያነብ ሰው ጸሐፊው አባቶችን በስህተትነት ለመፈረጅ ሳይሆን ሰው መሠረታዊ ነገር እንዳይረዳ ያደረገ አገላለጽ ስለሆነ ፣ለማስገንዘብ እና የምናምነው እምነት የተጠቀምነው ቃላት ስለማይገልጹ ልዩ ትርጉም ስለሚሰጡ እርማት ለመስጠት በማሰብ ብቻ ነው ።ሃይማኖት አበው ላይ ብፁዕ ዘሄሬነዎስ ስለኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ይለናል ፦
"" በሰው ባህሪይ ሰው የሆነ እርሱ ነው ፣ከአብ የተወለደ ፣ ከባህሪይ አምላክ የተገኘ የባህሪይ አምላክ ፣ የዘለዓለም ንጉሥ እርሱ ነው።..""
ከዚህ ክፍል የሚንረዳው ኢየሱስ ፦
✍️ ሙሉእ ሰው እንደሆነ፣
✍️ከአብ እንደተወለደ ና
✍️ ከአብ የተገኘ አምላክ እንደሆነ ነው።
*ትኩረት የምናደርገው በኢየሱስ ከአብ መወለድ ላይ ነው።ስለዚህም ከአብ "እንዴት ተወለደ ? አምላክ ሆኖ ሳለ " ብባል መልሳቸው ፣ አብ በአፉ ቃል እንደወለደው ከመጽሐፉቱ እንረዳለን ፦ "ቃል ከአብ ያለ ድጋሚ ወጣ ፣ድንግልም ያለ ድካሚ ወለደችው "እንደሚል ነው (ው.ማርያም ) ። ስለዚህም አብ ወልድን በአፉ ቃል ("በቃሉ") ያለ እናት ወለደ የሚል ነው።የቅድመ ዓለም ልደት አስተምህሮው ።
ይህ አገላለጽ ብዙ ችግሮች አሉበት ።እግዚአብሔር አንድና አንድ ነው፥አንድ ብቻና ብቻ ነው። እግዚአብሔር ተቀዳሚና ተከታይ የለውም። ትምህርተ ሥላሴ የሚያስተምረው "አንዱ እግዚአብሔር ሦስት አካል አለው" በማለት ሲሆን አብ ወላጂ ፣ወልድን ደግሞ ተወላጂ በማለትና በማድረግ የሚያስተምር አይደለም ።
አብ ማለት አባት ማለት ሲሆን ወልድ ማለት ደግሞ ልጅ ማለት ነው።አብ አባት ወይም "አብ" የተባለው የሚወልድ ስለሆነ ወይም ስለወለደ አይደለም ።ወልድም ወልድ ወይም "ልጅ" የተባለው ስለተወለደ አይደለም ።አብ ለአንዱ ለእግዚአብሔር አካል የተሰጠ የማንነት ስም ነው፤ግብርን የሚገልጽ ። ወልድም ለአንዱ ለእግዚአብሔር ለአንደኛው አካል የተሰጠ የማንነት ስም ነው ፤ግብርን የሚገልጽ ።አብም አልወለደም፤ ወልድም አልተወለደም፤ያለተቀዳሚና ተከታይ ያሉ የአንዱ የእግዚአብሔር አካላት ብቻና ብቻ ናቸው (ወለደ እና ተወለደ የሚሉ ቃላት እምነታችንን አይገልጹም፤ ይልቁንም ሰዎችን በማወዛገብ "አብን ትልቁ አምላክ ወልድን ደግሞ ትንሹ አምላክ የሚያደርጉ ናቸው )።
በሌላ በኩል ይህ የኢየሱስ "ሁለት ልደት ነው" አስተምህሮ ኢየሱስን ፥ "የተወለደ ነው"ብቻ ብሎ አያቆምም ። ከአብ የተገኘ አምላክ ነው ወደ ማለት የሚወስድ ኑፋቄ ውስጥ የሚከት ነው።በአጭር ቃል አብም ወልድን አላስገኘም ፣ ወልድም በአብ አልተገኘም ። ተገኘ የሚለው ቃል በፍጹም የኢየሱስ ክርስቶስን ዘመን አይቆጠርለትን አይገልጸውም ።ይልቁንም አርዮሳውያን እንደሚሉቱ " አብ መጀመሪያ ልጁን ፈጥሮ ፣ በልጁ ሌሎችን ፈጠረ " ወደሚል ወደ ስሁት አስተምህሮ የሚወስድ ነው።በእርግጥም እግዚአብሔር አንድ ብቻ ከሆነ አብ ፦ኢየሱስ ክርስቶስን አላስገኘም ።በእርግጥም ትምህርተ ሥላሴ እውነት ከሆነ አንዱ አካል አንደኛውን አላስገኘም ። እግዚአብሔር አንድ ብቻ ካልሆነ ወይም ትምህርተ ሥላሴ ስህተት ከሆነ አሮሳዊያን ትክክል ናቸው ። ምክንያቱም ኢየሱስ በአብ የተገኘ ከአብ የሚያንስ አምላክ ነው ብለው እንደሚያስተምሩት ነውና፤ እንጠንቀቅ ።ኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን የማይቆጠርለት ነው እንጂ የተገኘና የተወለደ አይደለም ።
የኢየሱስ ክርስቶስ ልጅነት ለመግለጽ ኢየሱስን ተወለደ ማለትና የአብን አባትነት ለመግለጽ "ወለደ" የሚሉ ገለጻዎች አስፈላጊ አይመስሉኝም ።ይልቁንም አደገኛ ናቸው!
(ዶክተር ተስፋዬ ሮቤል "ትምህርተ ሥላሴን ሰዎች እንዳይረዱት አወዛጋቢ የሚያደርገው ትምህርቱን ለመግለጽ የሚንጠቀማቸው ምሳሌዎችም ናቸው" ይለናልና ፤እኔም በተጨማሪ ቃላቶቹንም እንጠንቀቅ እላለሁ)
...
ልደት ማለት ሰው ስወለድ የሚከበር ሥርዓት ነው ።(መጽሐፍ ቅዱስ መ.ቃ)
አብ ክርስቶስን ልጄ ይለዋል ።ወልድም አባቱን አባቴ ይለዋል።ይህ ስም ነው ፤ማንነት ነው። ጅማሮ ሆነ ፍጻሜ የለውም። መወለድንም መውለድንም አይገልጽም ።አባት የሆነው በተፈጥሮ ነው።ወልዶ አስገኝቶ አይደለም። ወልድም ልጅ የተባለው ተወልዶ ተገኝቶ አይደለም።አብ አባት በመሆኑና በመባሉ እንደስሙ ግብር ያወጥናል ያዛል ፤ወልድም እንደስሙ ግብር ለአባቱ ይታዘዛል ይፈጽማል ።ነገርግን እንደ እኛ አባት እና ልጅ አይደለም። የተፈጥሮ ነው ።የእግዚአብሔር ስም ማንነት ነው ።
በአባቶች እምነት መግለጫ "ስህተት የለም፤ፍጹማን ናቸው" ማለት በእውነቱ ጨዋነት ነው። ለምሳሌ እነኚ አባቶች ኢየሱስ፦
""..ሞተ ወደ ሲኦል ወረደ ከሲኦልም ነፍሳትን አወጣ ."" በማለት እምነታቸውን ገልጸዋል ።
ነገርግን ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም ።መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመሆኑን እኔ ብናገር ግር ማለታችሁ አይቀርም ።ግን ሁላችንም የሚንወደው ወንድማችን ሰባኪ ጳውሎስ ፈቃዱ ፦ ኢየሱስ ወደ ሞቱት ነፍሳት ወደ ሲኦል አለመውረዱን በተንቀሳቃሽ ምስል ገልጿል (ከጠንካራ ምንባባት ዝግጅት) ወደ ዩቲዩብ ገባ በሉ። (እንዲሁም ዘላለም መንግሥቱም )
'*ኢየሱስ ከአብ ተወልዶ የተገኘ ነው' ለማለት የሚጠቀሰውን የመጽሐፍ ክፍል እንመልከት ፦
“ትእዛዙን እናገራለሁ፤ እግዚአብሔር አለኝ፦ አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ።”መዝ 2፥7
ከዚህ ክፍሎ ተነስተው እግዚአብሔር አብ ወልድን ቅድመዓለም አስገኘ ወይም ወለደ ይላሉ።እንደ እነርሱ ትርጓሜ ከሄድን "ዛሬ ወለድሁ" ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘው ወይም የተወለደው መዝሙረኛው ዛሬ በሚል ቀን እንደሆነ ነው። ስለሆነም ክፍሉ በፍጹም ቅድሜ ዓለም ልደትን አያሳይም እላለሁ ።ምክንያቱም የክፍሉ አውድ የሚለው ፦
#1.ክርስቶስ ከዳዊት ጋር በተደረገው ቃል ኪዳን መሠረት የተገኘ "ንጉሥ" "የተቀባ" መሆኑን የሚያሳይ ነው፣
#2."እኔ ዛሬ ወለድሁ " የሚለው ቃል ቅድሜዓለምን አያሳይም፤ "ቀንን"ብገልጽ እንኳን የሚገልጸው መዝሙረኛው ዛሬ የሚለውን ቀንን ነው፤ግን አይደለም ፣
#3."ልጄ" ፣ "አባቴ" በሚለው ቃል ንጉሠ ነገስቱ ከሥሩ ከሚገኙት ነገሥታት ጋር ያለውን ግንኙነትን ለመግለጽ የሚጠቀሙበት አባባል ነው ፤አገልጋይነትን ለመግለጽ ነው (መ.ትርጉም ማጥኛ ይመ.)፣
#4."ዛሬ ወልድሁ" የሚለው ቃል የክርስቶስን ንግሥናውን ፣ ትንሳኤውን ፣ ድል አድራግነትን የሚገልጽም ነው፤ለመግለጽ የዋለ ቃል ነው ሐዋ 13፥33፣
#5."ዛሬ ወለድሁ" የሚለው ቃል ክርስቶስ ሰው ሲሆን ከመላእክት በጥቅቱ ብያንስም አሁንም የከበረ ንጉሥ መሆኑን የሚገልጽ ነው ዕብ 1፥5 ፣
#6."ዛሬ ወለድሁ" የሚለው ቃል ክርስቶስ በሊቀ ካህናትነት መክበሩን መንገሡን ለመግለጽ ውሏል ፤አገልግሎቱን ለመግለጽ ዕብ 5 ፣
ስለዚህም እግዚአብሔር አብ ኢየሱስ ክርስቶስን "ዛሬ ወለድሁ" ማለቱ የከበረ ንጉሥ መሆኑንና የእርስበርስ ግንኙነትን ፣ አገልጋይነትን ለመግለጽ የዋለ ቃል እንጂ በአፉ ቃል ወልጃለሁ ወይም አስገኘሁ ለማለት በፍጹም አይደለም ።ምክንያቱም እግዚአብሔር አንድ ነው ሥሉስ ቅዱስ የሆነ፤ ለዘላለሙም ። አምላክን የሚያስገኝም የሚገኝም አምላክ የለኝም!
(ትምህርተ ሥላሴ ያለ ፍልስፍና ማስተማር ይቻላል ፤አባቶች ያወጡት መግለጫ ደግሞ ዝም ብለን የመቀበል ግዴታ የለብንም ፤አልያ የኀጢአት ሥርየት በውሃ ጥምቀት ይገኛል የሚለውን የቁንጥንጥንያ እምነት መገለጫ መቀበል ግድ ይላል ፤ለማሸማቀቅ አትሞክሩ በቃሉ ብቻ ሞግቱኝ 🙏)
...
ወልድ ወልድ የተባለው ከአብ ስለተወለደ ፥ ስለተገኘ አይደለም ።አብም አብ የተባለው ወልድን ስላስገኘ /ስለወለደ/ አይደለም ።ደጋግሜ እላለሁ ።
ሃይማኖተ አበው ዘዲዮናስዮስ ፦
"" እኛም አብ እንዳልተወለደ አስገኝም እንደሌለው ፈጽመን እናምናለን ፣ እናስተምራለን ፤አባትነቱም አይፋለስም ፣አይለወጥም ፣ ከማንም አልተወለደም ፣ ለመገኘቱ ምክንያት የሆነ ማንም ማን የለም፤በዚህ ግዜ ተገኘ አይባልምና ፤ .""
በአባቶቹ እምነት አብ ያልተገኘ ያልተወለደ ሲሆን ስለ መገኘቱ ምክንያት የሆነ አካል የለም የሚል ነው ።ትክክል ነው።በተቃራኒው ደግሞ ወልድ በአብ የተገኘ /የተወለደ/ ፣ስለመገኘቱ ምክንያት የሆነ አካል አብ ነው"" የሚል ነው። ስለዚህም አባቶች የሚሉት ወልድ ምንም እንኳን ከአብ ብገኝም ፣ አሪዮሳዊያን እንደሚሉት ከአብ በምንም አያንስም።ከአብ ጋር እኩል ነው "" የሚል እምነት ነው።
እኔ በበኩሌ የማምነው ፦ እግዚአብሔር አንድ ነው ብዬ ነው።አንዱ እግዚአብሔር ዘላለማዊ ነው። እግዚአብሔር ሥላሴ የሆነው አንደኛው አካል ሌላኛውን አካል በማስገኘት ነው ብዬ አላምንም ።እግዚአብሔር ሁሌም ሥላሴ ነው።ሥስት አካላት አሉት።አንዱ አካል ራሱን ወደ ሦስት አካልነት እንደሠራ አልቆጥርም ፤ አላምንም ። በአጭር ቃል አብ ወልድን አይቀድምም፤አላስገኘም ።ወልድም ከአብ አልተገኘም ።መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ ነው።
የእግዚአብሔር ስም
ይህንን በቀላሉ ለመረዳት "የእግዚአብሔር ስም" ማለት ምን ማለት እንደሆነ መረዳቱ በቂ ነው።""የእግዚአብሔር ስሞች ባህሪውን ይገልጣሉ ፤ እንደ ስሞች እንደሚሠራ ያረጋግጣሉ ።(ዘጸ 6፥3 ፤15፥13 ) ።"" [የመጽሐፍ ቅዱስ መ.ቃ]
ስሞቹ ባህሪውን ማንነቱን /ተፈጥሮውን/ ይገልጻሉ ፤ እንደ ስሞቹም እንደሚሰራ ያረጋግጣሉ ።ለምሳሌ አብ የሚለው ስም ከሥላሴ አካላት የአንዱ አካል ስም ነው፤ ማንነቱን እና ሥራውን ያሳየናል ።የወልድም እንዲሁ ።
አብ በሚለው ስም ወልድም መንፈስ ቅዱስም አይጠሩም ።ምክንያቱም የአንዱን አካል ማንነቱን የሚገልጥ እና ሥራውን የሚያሳይ ነው።ለምሳሌ ኢየሱስ ከድንግል ማርያም የተወለደው በመንፈስ ቅዱስ ተጸንሶ ነው። ማለትም ያስጸነሰው መንፈስ ቅዱስ ነው። ከሥላሴ አንዱ አካል ።ኢየሱስ ክርስቶስ ከመንፈስ ቅዱስ ብወለድም "አባቴ መንፈስ ቅዱስ ነው" አላለውም ።መንፈስ ቅዱስም የክርስቶስ አባቱ ነኝ አላለም።ምክንያቱም የአምላክ ስም ባህሪውን የሚገልጽ ነው። የማይለዋወጥ ።
ሌላው ምሳሌ እኛ ዳግም የተወለድነው ከቅዱሱ መንፈስ ነው።ግን አንድም ቦታ መንፈስ ቅዱስ "አባት" አልተባለልንም። ምክንያቱም አባትነት የአብ ማንነት ነው። (የበለጠ ለመረዳት የእግዚአብሔር ልጅ የሚለውን የጳውሎስ ፈቃዱን መጽሐፍ ያንብቡ ፤ሃሳብ ከዚያ የተወሰደ ነው)
ኢየሱስ ክርስቶስ ከመንፈስ ቅዱስ ተወልዶ የመንፈስ ቅዱስ ልጅ ተብሎ አለመጠራቱና የእኛም ዳግም ውልደት ከመንፈስ ቅዱስ ሆኖ ሳለ ፣ የመንፈስ ቅዱስ ልጅ አለመባላችን የሚያሳየው ፥ የእግዚአብሔር ስም ለባህሪው የተሰጠ የተፈጥሮ ስም መሆኑን ነው።
ስለዚህም እውነቱ ምንድነው !?መንፈስ ቅዱስ እኛን ዳግም ወልዶን "አባት" ያልተባለው ወይም ኢየሱስም በመንፈስ ተጸንሶ "ልጁ" ያልተባለው ፣ የአብ አባትነት "ስም" ማንነቱና ግብሩ ለአብ ብቻ ስለሆነ ነው።ምን እያልኩ ነው።አብ "አብ "ተብሎ የተጠራው ወልዶ ወይም አስገኝቶ አይደለም ።የተፈጥሮ የማንነት ስሙ ስለሆነ ነው።ወልድም "ወልድ" የተባለው ተወልዶ ወይም ተገኝቶ አይደለም ።አብም ወልድም የአካላቱ ስም እንደሆነ ይታወቅ።
አብን በሥጋ አዕምሮ አስበን ወላጂ እና አስገኚ አልነው፤ወልድንም የተወለደ እና የተገኘ አልነው እንጂ የአብ አባትነቱ የሚገለጸው በማንነቱ በግብር ሥራው ነው፤የወልድም እንድሁም።ማለትም የአብ አባትነት በመወለዱ ሳይሆን ሃሳብን በመወጠን ፣ በማዘዝ... የሚገለጽ ሲሆን ፣ የወልድም ስምም በመላክ እና በመፈጸም የሚገልጽ ነው ፤ ከአብ በመገኘቱ አይደለም ። ከእኛ እንዲያ ያለ ሃሳብ ይራቅ።
ኢየሱስ 'ከአብ የተወለደ ነው' ለማለት የተጠቀሰውን ክፍል ከተመለከትን እጨርሳለሁ ፦
“ከውቅያኖሶች በፊት፣ የውሃ ምንጮች ከመፍለቃቸው በፊት #ተወለድሁ፤”ምሳሌ 8፥24 (አዲሱ መ.ት)
ክፍሉ የሚናገረው ስለ ጥበብ ነው።ጥበብ ደግሞ "ኢየሱስ ክርስቶስ ነው" በማለት ፥ "ኢየሱስ ከአብ ተወልዷል" ለማለት ይጠቅሳሉ፤ጆሆባዎቹም ይጠቅሱታል ።ኢየሱስ የእግዚአብሔር ጥበብ ተብሎ በመጽሐፍ የተገለጠ ብሆንም ፣ አውዳዊ ትርጓሜው የሚያሳየው ግን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አለመሆኑን ነው።ምክንያቱም ከፍ ብለን ስናነብ በሴት አንቀጽ ጥበብን ይገልጸዋል ምሳሌ 8፥1-3።ኢየሱስ ደግሞ ወንድ ነው። (የበለጠ ለመረዳት መደበኛ ትርጉም ማጥኛ እና ዶክተር ተስፋዬ ሮቤል ለጆሆባዎች የሰጠውን መልስ ይመልከቱ ከዩቲዩብ)
"መጽሐፍ ቅዱስ የጉባኤያትን መግለጫ ይመዝናል እንጂ በጉባኤያት መግለጫ አይመዘንም"
እኔ የማምነው እንዲህ ነው ፦ እግዚአብሔር አንድ ነው።አንዱ እግዚአብሔር ግን ሁሌም ሥሉስ ቅዱስ ነው።ለሥሉስነቱ ጅማሮ የለውም። የተገኘም ያስገኘም አካል የለም።ምክንያቱም "እግዚአብሔር ሁሌም ሥሉስ ቅዱስ ነው። "ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ነው ፤ወልድ ተብሎ የሚጠራ ፤ በሥጋ ከድንግል የተወለደ ፤ ሰው የሆነ ፤ በሌላ አካል ያልተገኘ ፤ጅማሮ ሆነ ፍጻሜ የሌለው የነገሮች ሁሉ ጅምር፤አስገኝ። እርሱ ዘላለማዊ አምላክ ነው፤ያለና የሚኖር ያህዌ ፤ እግዚአብሔር ነው።እንዲህ አምናለሁ ።
...
ሥላሴን አብ አልሠራም !?
"" አብ ያልተገኘ ነው ፥ ያልተወለደ ነው፥ስለመገኘቱ ምክንያት የሆነ አካል የለውም ።"ብለህ ፣ ወልድንም መንፈስ ቅዱንም እንዲያ ፦ "ያልተገኘ ነው" ማለት ካልቻልክ ፣ በእውነቱ አብ በምን ሂሳብ ነው ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል የሚባለው !? እንደውም "ሥላሴን አብ ሠራው" ማለት አይደለምን !?
"ወልድ በመለኮቱ ከአብ የተገኘ ነው ግን የተፈጠረ አይደለም" የሚለው ገለጻ ድኩም ነው፤ እንድሁም ስሁት ነው።ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮቱ ከማንም የተገኘ /የተወለደ/ አይደለም ።ሥላሴ በአብ የተሠራ አይደለም ።እግዚአብሔር ሁለም ሥሉስ ቅዱስ አምላክ ነው ። "መለኮት የተገኘ ነው እንጂ የተፈጠረ አይደለም " ማለት ሰውን ማወናበድ ነው። በጨዋነት ሃሳባቸውን ለመረዳት ይህንን አገላለጽ እንኪ እንያ ፦ስለ ወልድ መገኘት ግን ስለ አለመፈጠር እንደ አባባላቸው ለመረዳት ፦
እግዚአብሔር አብ ወልድን ከራሱ የወለደ /ያስገኘ/ ነው ግን ወልድን አልፈጠረም ማለት ለእኛ በልካችን ካለልኩ የወረደውን ታላቁን ጌታን ፣ ጭራሽ ምጥጥዬንም እንዳናውቅ የሚያደርግ የሚጋርድ ነው። መጽሐፍ ስናገር “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።“ (ዘፍ 1፥27 ) ፣ይለናል።
የተፈጠረው አንድ ሰው ነው።አንዱ አካል ብቻ ፤በአንዱ አካል ሴቷ እና ወንዱ አሉ ፤ አዳም ተብለው ይጠራሉ። "ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው" እንደሚል። ።እግዚአብሔር ፍጥረታትን አበጃጅቶ ከጨረሰ በኃላ አረፈ ። የተፈጠረውን ሰው ለፍጥረታቱ ስም እያወጣ ነበር ፤ ብቻውም ነበር።ከእርሱ ጋር የተፈጠረችው ሴቷ በውስጡ ናት።ነበረች። “እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት #እንፍጠርለት።”(ዘፍ 2፥18 ) ፣አለ። እግዚአብሔር ሴቷን ከአዲስ አፈር አልፈጠረም ፤አልሰራም ።መጀመሪያም ሰርቷት ስለነበር ካለችበት አወጣት። “እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት #ሴት_አድርጎ_ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት።” (ዘፍጥረት 2፥22 ) ፣እንደሚል።
ስለዚህም ሴቷ መጀመሪያም ከአዳም ጋር የተሠራች ብትሆንም ፣ ከአዳም ውስጥ እስኪትወጣ ድረስ የራሷ ፈቃድ እና አካል አልነበራትም ። እግዚአብሔር መጀመሪያም ከአዳም ውስጥ የነበረችውን ፣ ያለችውን ሴት ፣ ከአዳም ውስጥ በማስገኘቱ ፈጠራት ፣ ሰራት ተብሎ ተገለጸ ።ምክንያቱም ስለመገኘቷ ምክንያት አለ፤ መጀመሪያ ከነበረችበት ፣ ካለችበት ፥ አሁን ልዩ የሆነ የራሷ ህልውና ኖሯታልና። የሰዎቻችን አገላለጽ እንዲያ ያለ ነው፣ ወልድ በመለኮቱ ከአብ "ተገኘ" ማለታቸው ።
ወልድ መጀመሪያም የነበረ ያልተፈጠረ ነው ፣ ግን ከአብ ነው የተገኘው ማለት ፥ ሴቷ ከአዳም ውስጥ ከነበረችበት ፣ አሁን በራሷ ህልውና እንደተገኘች እንደሚገልጽ ነው። ሴቷ ያልነበረችና አዲስ የተፈጠረች አይደለችም ፤ ወልድም ያልነበረ አዲስ የተፈጠረ አይደለም ።ነገርግን "ሴቷ ከአዳም እንደተገኘች ወልድም ከአብ የተገኘ ነው" የሚል አንድምታ ያለው ነው።
ወልድ በመለኮቱ የተገኘ አይደለም ። ከየት ነው የሚገኘው !? ፥ "ያልተፈጠረ ነው ግን የተገኘ ነው" ማለት ወደ ክህደት የሚያመራ ነው።ወልድ በመለኮቱ አልተገኘም ። መጻሕፍትም ተገኘ አይሉም።ወልድ ያለና የሚኖር ያህዌ ነው።ስለመገኘቱ ምክንያት የሆነ ማንም የለም።እርሱ እግዚአብሔር ነው።
ነገሩን በጨዋነት ስነረዳ " ከአብ የተገኘ ነው" ማለታቸው "አልተፈጠረም" የሚል አንድምታ ይሰጥ ይሆናል ።ነገርግን መጀመሪያ በራሱ ህልውና ያልነበረ መሆኑን የሚያሳይ ነው።ያ ደግሞ ክህደት ነው ።ለምሳሌ ሃይማኖት አበው ዘአትናቴዎስ ፦
""ከአብ ባህሪይ የተገኘ #ወልድ_ከራሱ_ባህሪይ_የተገኘ አይደለምና።አልተወለደም እንደሚን ይሉታል !?"" ይለናል።
ስለዚህም በግልጽ እንደሚያሳየው የአባቶቹ እምነት ወልድ በመለኮቱ በራሱ ህልውና ያልነበረ ፣ በመለኮቱ ከአብ የተገኘ ነው የሚል እምነት እንደሆነ ነው።ይህንን እኔ መቼም አልቀበልም ።ለእግዚአብሔር ሥሉስ ቅዱስነት ጀማሮ ከሌለው የተገኘም ፤ያስገኘም አካል የለም።ልኖርም አይችልም ።እግዚአብሔር እግዚአብሔርን አያስገኝም።
ሰዎች ያልተረዱት ነገር ወልድ እግዚአብሔር መሆኑን ነው።ያህዌ መሆኑን ነው ፤ያለና የሚኖር መሆኑን ነው ፤ማንነቱን ነው፤ አምላካችን ሁሌም ሥሉስ ቅዱስ መሆኑን ነው።ወደ ስህተት የገቡት "እግዚአብሔር ወልድ" ተብሎ አንዱ አካል ስለሚጠራ ፣ ስለሚባል ከአብ የተወለደ የተገኘ በማለት በመተርጎም እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያ አይልም። ለምሳሌ ስሙ "እግዚአብሔር ወልድ" ስለተባለ የተገኘ ነው፤የተወለደ ነው ካስባለ ፣ ስሙ "የእግዚአብሔር ቃል" መባሉ የእግዚአብሔር ንግረት ፤ንግግር ነው ፣ ወልድን የማያስብልበት ምክንያት የለም። እንዲያ አይሁን ።የእግዚአብሔር ስም ማንነት ገላጭ ነው፤ በግብሩ የሚገለጽ ።መለኮት መለኮትን አላስገኘም ።አብ ራሱን ኮፒ አላደረገም። በኢየሱስም !
የእኔ ኢየሱስ ያህዌ ነው 😢
የማልሸማቅቅበት እውነተ።
....
መዝ 110 ወልድ ከአብ በመለኮቱ ተወልዶ እንደተገኘ ይናገራልን !?
“እግዚአብሔር ጌታዬን፣ “ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ፣ እስከማደርግልህ ድረስ፣ በቀኜ ተቀመጥ” አለው።” መዝሙር 110፥1
*እግዚአብሔር (ያህዌ) ጌታዬን (አዶንን) "___" አለው። በዚህ ላይ ተናጋሪው "ያህዌ" ነው፤አብ ነው። አብ የዳዊትን "ጌታን" በቁኙ እንድቀመጥ ተናገረው፤ በክብር በቀኙ እንድቀመጥ ፤በሥልጣንና ክብር እንድሆን።
ከክፍሉ እንደሚንረዳው ያህዌ (አብ) የጌታ (የክርስቶስን) ጠላቶቹን ለማድቀቅ ፈልጓል። የክርስቶስ ጠላቶቹ እኔ ማን ናቸው !? ለምንስ ክርስቶስን ይቃወማሉ !?
*ኢየሱስ ክርስቶስ "መስዋዕት አቅራቢ ካህን ነው" ።መስዋዕቱን ካቀረበ በኃላ የራሱን ተግባር በፍጹምነት ስለተወጣ ፣በአብ ቀኝ ተቀምጧል፤በክብር።በአብ ቀኝ ተቀምጦም የተቃወሙትንን አብ እንዲበቀልለት ይጠብቃል። አሁንም እየጠበቀ ነው። (ዕብ 1 ፥ 11-12)፣ መጽሐፍ አሕዛብን ይረግጣቸዋል እንደሚል (ራዕ 12 ) ። ለመርገጥ ፣ለማድቀቅ ይጠብቃል ገና የሚፈጸም ትንቢት ነው። ወዮ ላላመኑት።
“እግዚአብሔር ብርቱ በትርህን ከጽዮን ወደ ውጭ ይሰዳል፤ አንተም በጠላቶችህ መካከል ሆነህ ትገዛለህ።”መዝ 110፥2 (አዲሱ መ.ት)
*የክርስቶስ መንግሥት በጽዮን ብቻ ተወስኖ አይቀርም ።ይሰፋል ።ክርሰቶስም ይገዛቸዋል ፤የተቀበሉትን ፤"ጌታዬ ነው" የሚሉትን ።
“ለጦርነት በምትወጣበት ቀን፣ ሰራዊትህ በገዛ ፈቃዱ በጐንህ ይቆማል፤ ከንጋት ማሕፀን፣ በቅዱስ ግርማ ደምቀህ፣ የጐልማሳነትህን ልምላሜ እንደ ጠል ትቀበላለህ።” መዝ 110፥3 (አዲሱ መ.ት)
*የክርስቶስ ሠራዊት ለክርስቶስ ነፍሱን በፈቃዳቸው ለመስጠትም ዝግጁ እንደሆኑ ይገልጻል ፣
*"ከንጋት ማህፀን" በጧቱ ሁሌ እንደሚታየው "ጠል" ጎልማሳዎቹ ለመዋጋት ሁሌም ይጎርፋሉ ።የክርስቶስ መንግሥት የቆመው በወንጌል ነውና፤ሳይታከቱ ወንጌሉን ይሰብካሉ ማለት ነው። (ይህንን ክፍል ስለ ክርስቶስ መለኮቱ ተወልዶ ስለመገኘት ለማስተማር ያስጠቀሳቸው የ1953 ትርጉም ሳይሆን አይቀርም) ። "ወለድሁህ" የሚለው ቃል ። ቃሉን እስኪ እንመለከት ፦
“Thy people shall be willing in the day of thy power, in the beauties of holiness from the womb of the morning: thou hast the dew of thy #youth.”Psalms 110:3 (KJV)
*የክፍሉ አውድ በአጭሩ የሚለው ፦ የክርስቶስ ሰዎች ፣በፈቃዳቸው ፣በክርስቶስ በኃይሉ ቀን፣ በቅድስና በውበት ተመልተው ፣ በንጋት ጠል እንደማይጠፋ ፣የክርስቶስ ተከታዮችም ለወንጌል ፣ ራሳቸውን ለመስጠት ይሽቀዳደማሉ ፤ያለመታከት የሚል ነው።
በ1953 ዓም ትርጉም ምናልባት "ወለድሁህ" የሚለው ቃል የተወለደ የተገኘ ለማለት ሳያሳብቅ አይቀርም ፤ትርጉሙ ለእኔም ግልጽ አይደለም (ነገርግን ቃሉ " Youth" ወጣቶች ጎልማሶች ፣ ሴት ወንድ ልጆች ፣ ተብሎ የሚተረጉም ነው)። እንዲህ ያለ ነገር ስገጥመን ሌሎች አማራጫ ትርጉሞችን መመልከት አግባብ ነው፤ወይም Bible Interlinear መጠቀም እንችላለን። Bible Strong Dictionary ስመለከት ፦
*ቃሉ በእብራይስጥ יַלְדוּת የሚል ሲሆን ፣ ስነበብ yal-dooth' የሚል ነው።ጎልማሶች ወጣቶች ሴት ወንድ ልጆች ማለት ነው።መክ 11፥9። በአንዳንድ ቅጂዎች Your Youth (yal·ḏu·ṯe·ḵā ) የሚል ትርጉም ያለው ቃል እንደሆነ ተቀምጧል ። ሰዎች እንደሚሉቱ ወለድሁ ለማለት ብሆን ፣ yaw-lad' ተብሎ ይቀመጥ ነበር (መዝ 2) ማለት ነው።
*ስለዚህም መደበኛ ትርጉም ስለ መሲሕ ንጉሥና ካህን ይናገራል እንዳሉት ነው እንጂ ስለ ልደት (ተወልዶ ስለ መገኘት) የሚናገር ክፍል በፍጹም አይደለም ።
...
መጽሐፍ ክርስቶስን "የእግዚአብሔር ልጅ ነው" ስል ምን ማለቱ ነው !?
ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ማለት ፣ ከአብ ተወልዶ የተገኘ ነው ማለት ነውን !?
በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት በሊቃውንቱ አተረጓጎም መሠረት "ልጅ" የሚለው ቃል የሚወክለው ፦
<< #1.ከብዙ ዘመን በኃላ በትውልድ ሐረግ የሚገኝ ፤ሚል 3፥6 ። #2. የሥራ ወይም የትምህርት ተከታይ ፤ 2ነገ 2፥3 ፡5 ። #3. በሃይማኖት የተወለደ ፤1ጢሞ 1፥2 ። #4.በዕድሜ የበታች የሆነ ፤1ሳሙ 3፥6 ። #5.የአገር ወይም የአከባቢ ተወላጅ ፤ ሴ.አ 4፥2 ። #6. የችሎታ ፣የጠባይ ፣ የጥበብ ..ወዘተ ባለቤት ፤ሉቃ 10፥6 ። #7. በሌላ አሳዳጊ ሥር ያለ ሉቃ 2፥48። >>
ከላይ እንዳየነው በዚህ አተረጓጎም መሠረት ምንም እንኳን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ብሆንም ፣ ልጅነቱን ልገልጽ እና ልወክል የሚችል ትርጓሜ የለውም ። ታዲያ መጽሐፍ ክርስቶስን የእግዚአብሔር ልጅ ነው ስል ምን ማለቱ ነው !?
"ባህሪይ ማለት ፦ የቋሚ ነገር ሁሉ ምክንያትና መሠረት ።ባህሪይ የሚገለጠው በአካል ነው" የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንደሚል ባህሪይ ቋምነትን ይገልጻል ።ለምሳሌ የውሃ ቋም ባህሪይ መፍሰስ ነው ፤ፈሳሽነት ነው ፥ የድንጋይ ባህሪይ ጠጣሪነት ነው።ይህ ቋሚ የማይለወጥ ተፈጥሯዊ መገለጫው ባህሪይ ይባላል ። የፍጥረታት ባህሪይ ቋሚ ስለመሆኑ ምክንያት እና መሠረት አለ። ለእግዚአብሔር ባህሪይ ግን "ጥንት ምክንያት የለውም"።
የእግዚአብሔር አምላኪነትን የሚያሳዩትን ባህሪያትን ፣ የእግዚአብሔር ብቻ ቋሚ ገንዘብ የሆኑትን ፣በሌሎች ፍጡሮቹ ፈጽሞ የማይገኙትን ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይዘረዝራል ፦
#1. ሁሉን ቻይነት ።እግዚአብሔር ለባሕርዩ መነሻ የለውም ፤ከዚህ ተገኘ አይባልም ።ራሱ በራሱ የነበረ ያለ ፤ ያህዌ ነው ዳን 4፥ራዕ 4 ዮሐ 5። #2.አለመለወጡ።..መዝ 33፤ሚል 3 ፤ዕብ 6 ። #3. አለመወሰኑ ። ..መዝ 145 ..።
#4. አለመከፋፈሉ ።..ከፍጥረቱ የተለየ ነው ። ዮሐ 4፥24 ።.. >>
ከላይ እንዳየነው ለእግዚአብሔር ለባሕሪው መነሻ የሆነውና ያስገኘው አካል የለውም ፤ እንደሌለውም ተመልክተናል ። ስለዚህም መጽሐፍ ፦ የእግዚአብሔር ቃል ፣ ወልድ ፣ ክርስቶስ ፣ጌታ ..ብሎ የገለጠው አካል አምላክ ነው።እግዚአብሔር ነው ዮሐ 1። በአምላክነቱ ተወልዶ የተገኘ አይደለም።ልክ እንደ አብ ወልድም በመለኮቱ ከሌላ አካል ተወልዶ የተገኘ አይደለም ።ከሌላው መገኘት የአምላክ ማንነት አይደለምና ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት በገጽ 108 ላይ እንዲህ ይላል "ለእግዚአብሔር ባህሪው ጥንት ምክንያት የለውም" እንደሚል ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መባሉም የባህሪይ ልጅነት እንጂ ተወልዶ መገኘት አይደለም ።ምክንያቱም የባህሪይ ልጅ ነው የተባለው እግዚአብሔር ነው፤ወልድ ነው፤ ቃል ነው። ስለዚህም ለልጅነቱ ምክንያት የሆነ ( የወለደ ያስገኘ ) አካል የለም።በሌላ በኩል አብም አባት የተባለው በባህሪው እንጂ መለኮትን ፦ ወልዶ ወይም አሠሪፆ አስገኝቶ አይደለም ።የባህሪ አባት መባሉ ለአባትነቱ ምክንያት ጅማሮ ጥንት የለውም ፤ የማይለወጥ ነው ማለት ነው። አንዱ እግዚአብሔር ሁሌም ሦስት አካላት አሉት ።
አይሁዳውያን እንደሚረዱት ኢየሱስ ክርስቶስ፦ አብ አባቴ ነው ፤ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስል ፣ የሚገባቸው ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ነኝ ፥ አምላክ ነኝ ማለቱ እንደሆነ ነው።እኛም በዚህ ልክ ተረድተን ብሆን ብዬ እመኛለሁ ።[“እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ፦ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር።’’ ዮሐንስ 5፥18፤ 10፥34 ይመ.።]
ስለዚህም ኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛው አንዲያው የባህሪይ ልጅ ነው። ልጅ ለመባሉ ምክንያት እና ጥንት የለውም።ልጅ በመባል ያገኘው ስልጣን የለውም።ለዚያም ነው ኢየሱስ ስናገር ከሐዋርያት ጋር ራሱን ደምሮ አብን ፣ #አባታችን የማይለው ።ይልቁንም "አባቴና ወደ አባታችሁ" በማለት ፍጹም ልዩነትን በግልጽ አሳይቷል ። ( አባቴ ያለው ከእኛ ራሱን ነጥሎ ነውና )
#ስደመድመው|| ክርስቶስ በመለኮቱ << ከአብ የተወለደ የተገኘ ነው ፥ አብ ደግሞ ስለመገኘቱ ምክንያት የሆነ አካል የለውም ፤ያልተወለደ ያልተገኘ ነው >>ማለታቸው ፥ የክርቶስን መለኮትነት ይደብቃል እላለሁ ። ምንም እንኳን ለዚህ ትርጓሜ ማስረጃ ባይኖርም ፣ ነገርግን "አባት " ከሚለው ስም ተነስተው 'የወለደ ያስገኘ' እንዳሉትና ፣ ወልድ ከሚለው ስም ተነስተው 'የተወለደ የተገኘ' ማለታቸው ይታወቃል[ መንፈስ ቅዱስ ከሚለው ስም ተነስተው ከአብ የሠረፀ የተገኘ ነው ብለዋልና] ። ግምታዊ ትርጓሜ መሆኑን ያሳያል።መንፈስ ቅዱስ ከአብ ሠሪፆ እንደተገኘ አይነግረንምና።
አብ ወልዶ አባት አልተባለም ፣
ወልድም ተወልዶ ተገኝቶ ወልድ አልተባለም ፣
መንፈስ ቅዱስም ሠርፆ ተገኝቶ አልተባለም ፣
ወልድ ራሱ አምላክ እስከሆነ ድረስ አልተገኘም በመለኮቱ ፣መንፈስ ቅዱስም አምላክ እስከሆነ ድረስ አልተገኘም በመለኮቱ ።እላለሁ ።አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ አምናለሁ ።
መጽሐፍ ቅዱስ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደሚፈታ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ስባል ምን ማለት እንደሆነ ከቃሉ ለማሳየት ጥረት አደርጋለሁ ፦
ዮሐንስ 9
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁵ ኢየሱስም ..፦ አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን? አለው።… ³⁸ እርሱም፦ #ጌታ_ሆይ፥ አምናለሁ አለ፤ ሰገደለትም።
#ኢየሱስን የእግዚአብሔር ልጅ ነው ብሎ ማመን በኢየሱስ አምላክነት ማመን ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ፤አብ አባቴ ነው ስል ፣ አይሁዳውያን የሚረዱት "ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ነኝ" ፣ "አምላክ ነኝ" እንዳለ ነበር ።ዕውቀታቸው ይገርማል ባይቀበሉትም ።ዮሐ 5፥ 18
#ለእኛም ይህንን እውነት ማወቅና ማመን ይሁንልን!
..
ሥላሴ ስም ነው !?
<< #1. ሥላሴ ስም ነው ወይም የሙያ ቃል ነው !? #2. የአምላክ ስም ነው !?#3.ከስሞች ሁሉ የበላይ ስም ነው !? >> ለመምህር ኢንጂነር ታርኩ አበራ ና...።
"" ሥላሴ የሚለው ስም እንዲያው የመጣ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በአንድነቱና በሦስትነቱ የሚጠራበት የከበረና #ከስም_ሁሉ_በላይ_የሆነ_ስም ነው፡፡ "" (መምህር ታርኩ አበራ ከፊት ገጹ የተወሰደ።)
መምህር ታርኩ አበራ በሚስጥረ ሥላሴ ጹሑፉ "" #ሥላሴ_የሚለውን_ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ፣ ያለና የሚኖረውን አምላክ ለመግለጽ የተጠቀመው የአንጾኪያው ቴዎፍሎስ ነው በ169 ዓ.ም ፡፡"" በማለት ሥላሴ በሰው የወጣ ቃል እንደሆነ ገልጸዋል ።እንዲያ ብገልጹትም በመጨረሻው ድምዳአቸው ላይ ""ዝም ብሎ የወጣ ስም አይደለም ።ከስም ሁሉ የበላይ ስም ነው"" በማለት ወደ ስህተት ትርጓሜ ገብተዋል ።
ሥላሴ ወይም Trinity የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ግዜ በቴዎፍሎስ ፣ የእግዚአብሔር ሦስት አካልነት ለማስተማር ጥቅም ላይ ውሏል (አባት ፣ ቃል ፣ ጥበብ በማለት ገልጾታል) ። በኋላ በጠርጡልያን በኩል በ220 AD (አባት ፣ ልጅ ፣ መንፈስ ቅዱስ ) ተብሎ የእግዚአብሔር ሦስት አካልነት ለማስተማር ጥቅም ላይ ውሏል ።
እንግዲህ ታርኩ አበራ ራሱ እንደገለፀውም ቃሉን የሠሩት ሰዎች ናቸው ። ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም።ግን ትምህርቱ አለ። እነዚህ አባቶች ትምህርቱን ለማስተማር ብለው ይህንን ቃል በእውቀታቸው ቀመሩት ። ስለዚህም ሥላሴ ወይም ሦስትነት የሚለው ቃል የእግዚአብሔርን ሥስት አካልነት ለማስተማር የወጣ የሙያ የአስተምህሮ ቃል ነው እንጂ ስም አይደለም ።የአምላክ ስም አይደለም ። መምህር ታርኩ አበራ ግን በሰዎች ለትምህርት የወጣ ቃል ብሆንም ፣ ስም ነው፤እንዳውም ዝም ብሎ የመጣ ስም አይደለም ፤ ከስሞች ሁሉ የበላይ ስም ነው በማለት ገልጾታል ።ይህ ደግሞ ትልቅ ስህተት ነው።
እነዚህ የእምነት አባቶች የቀመሩት ቃል "ቃል" እንጂ የእግዚአብሔር ስም አይደለም ። ስም ማውጣት የበላይነት ሥልጣንነትን ያሳያልና ። ለምሳሌ አዳም "እነዚህን ሁሉ ግዛ" ከተባለ በኃላ ፣ ስም ማውጣት ጀመረ ።ምክንያቱም ይህ ሥልጣን ነው።እነዚህ ሰዎች የቀመሩትን ቃል የእግዚአብሔር "ስም ነው" ማለት በእግዚአብሔር ላይ የሰዎች ሥልጣንን የሚያሳይ አንድምታ ስለሆነም ትክክል አይደለም ። (የበለጠ ለመረዳት በመምህር ጌታቸው ተረፈ የተጻፈውን መልህቅ ቅጽ.1 ይመ.)
እግዚአብሔር ስሙን ያውጃል ፤ለእኛ ያስታውቃል እንጂ እኛ አናወጣለትም። ምክንያቱም በእግዚአብሔር ላይ ሥልጣን የለንም።ይህንን ስል የሳምራውያን ሰዎች ኢየሱስን "መዲህነ ዓለም" ወይም የዓለም መዳንት ነው ማለታቸው በአዕምሮአችን መጥቶ ይሆናል ፣ ይህ ስም ማውጣት አይደለም እንዴ !? ከዚህ ተነስተን ሰዎች "ስም" አወጡለት ልንል አንችልም ወይ !? ብባል አዎን አንችልም እላለሁ። ነገርግን ኢየሱስ የዓለም መድኀኒት መሆኑ በስሙ የመጀመሪያም የተገለጠ ነው።እግዚአብሔር አዳኝ በመባል።የሳምራውያን አጠራር "ስም ማውጣት" ሳይሆን ምስክርነት ነው።ልክ እንደ ዘካሪያስ የመዳን ቀንድ ፣ ልክ እንደ አረጋዊ ስሞኦን "የሕዝብ ሁሉ ብርሃን" እንዳሉት ምስክርነት ነው።እኛ ግን መድኀኔዓለም ብለን ስለምንጠቀም እንደ አምላክ ስም ጥቅም ላይ ውሏል ።እንጂ የምስክርነት ቃል ነው።ሥላሴ ማለትም የአስተምህሮ ቃል ብቻ ነው። [Triangle ስለ ሦስት ማዕዘን ትምህርት ፣ ለሦስት አካልነትም ትምህርት Trinity ይባላል ። ስለዚህም ሥላሴ የአምላክ ስም ፈጽሞ አይደለም ።]
መምህር ታርኩ አበራ "ሥላሴ" የሚለውን ቃል ፣ከሙያ ወይም ከአስተምህሮ ቃልነት አሳድጎ ፣ አኮትኩቶ ፣ ለአምላክ ስምነት አብቅቷል ።ማብቃት ብቻ አይደለም "ከሁሉም ስሞች የበላይ ነው" የሚል የተጣመመ ትርጓሜም እስከ መስጠት ተዳርሷል ። መጀመሪያ ሥላሴ ስም አይደለም እንዳልኩት የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላቱን በማስመልከት ሃሳቤን አጸናለሁ ፦
"" ሥላሴ ሦስትነት ማለት ነው። ከቃሉ ምስጢር በቀር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም ።እውነተኛና ሕያው የሆነ አንድ አምላክ ብቻ አለ።ይህ አንዱ አምላክ በሦስት አካላት ስለሚኖር #ሥላሴ_የሚለው_ቃል የአንዱን አምላክ የአካል ፥ የስምና የግብር ሦስትነት ያሳያል ። ""
ስለዚህም በአጭር ቃል ሥላሴ የሚለው ቃል ለአካላት ስም መኖሩን ያመላክታል እንጂ በራሱ ስም አይደለም ። ከስም ሁሉ የበላይ ስምም አይደለም ።ምክንያቱም ፦
ፊልጵስዩስ 2 ፥ ⁹ በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤¹⁰ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ #በኢየሱስ_ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥
ሥላሴ የሆነ አምላክ እንጂ ሥላሴ ተብሎ የሚጠራ አምላክ የለም።ከስምም ሁሉ የበላይ ስም ኢየሱስ የሚል ስም ነው።እግዚአብሔር ማንነቱን የገለጸበት ስም። ሃሌ ሉያ ።
..
ተባረኩ በስፋት እመጣለሁ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ።
እድሉ ዮሐንስ 2015
Comments
Post a Comment